ኢራን በሳይንቲስቱ ግድያ እጃቸው አለበት ያለቻቸውን አሰረች

ኢራን በሳይንቲስቱ ግድያ እጃቸው አለበት ያለቻቸውን አሰረች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በኢራኑን የኒውክሌር ሳይንቲስት ሞህሰን ፋክሪዛሄድ ግድያ እጃቸው አለበት የተባሉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢራን ፓርላማ አማካሪ ገለጹ።

ሁሴን አሚር አብዱላሂን፤ ለደህነት ሲሉ ዝርዝር መረጃ መስጠት እንደማይችሉ ቢናገሩም፤ ወንጀለኞቹ ከፍርድ አያመልጡም ሲሉ ለአል-አላም ቴሌቭዥን አስታውቀዋል።

በግድያው የእስራኤል እጅ እንዳለበት የሚጠቁም መረጃ እንዳገኙም ተናግረዋል።

እስራኤል ግን እስካሁን ክሱን አልካደችም፣ አላመነችምም።

ጉምቱው ሳይንቲስት ቴህራን አቅራቢያ የተገደሉት ጥቅምት 27 ነበር።

የኢራን ባለሥልጣኖች ሳይንቲስቱ እንዴት እንደተገደሉ እርስ በእርሱ የሚጣረስ መረጃ አውጥተዋል።

የመከላከያ ሚንስተሩ እንደሚሉት፤ ሳይንቲስቱ በተገደሉ እለት ጠባቂዎቻቸው ከታጣቂዎች ጋር ተኩስ ተለዋውጠዋል።

የዓይን እማኞችን ያጣቀሰ ሪፖርት ከሦስት እስከ አራት የሚደርሱ አጥቂዎች መገደላቸውን ይጠቁማል።

የአብዮት ጥበቃው ከፍተኛ ኮማንደር እሑድ እንዳሉት፤ በሳተላይት ቁጥጥር የሚደረግበት መሣሪያ የሳይንቲስቱ መኪና ላይ ተኩሷል።

በሰው ሠራሽ ልህቀት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) የተዘወረው መሣሪያው በጭነት መኪና ላይ እንደነበረና ሳይንቲስቱ ላይ አነጣጥሮ እንደተተኮሰባቸው ብ/ጀ አሊ ፋዳቪ ተናግረዋል። አጠገባቸው የነበሩት የሳይንቲስቱ ባለቤት ግን ጉዳት አልደረሰባቸውም።

ይህንን በገለልተኛ አካል ማጣራት አልተቻለም። እንዲያውም የዘርፉ ባለሙያዎች የሳይንቲስቱ አሟሟት ተብሎ የተገለጸውን አላመኑበትም።

በኢራን ብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ አል-አላም የቀረቡት ሁሴን አሚር አብዱላሂን፤ "በግድያው የተሳተፉ ጥቂት ሰዎችን በደህንት መዋቅራችን በኩል ደርሰንባቸዋል። በቁጥጥር ስርም አውለናቸዋል" ብለዋል።

እስራኤል ከግድያው ጀርባ ስለመኖሯ የሚጠቁሙ ማስረጃዎች እንደተገኙም አስረድተዋል።

"ጽዮናውያን [እስራኤሎች] ለብቻቸው ይህንን ጥቃት ፈጽመዋል ማለት አይቻልም። ምናልባት ከአሜሪካ ደህንነት ጋር ተባብረው ይሆናል" ሱሉ ለጣቢያው ተናግረዋል።

የእስራኤል መንግሥት ስለ ሳይንቲስቱ ግድያ እስካሁን አስተያየት አልሰጠም።

የኢራኑ ሳይንቲስት በሰው አልባ መሣሪያ ነው ሲል መንግሥት አሳወቀ

የፎቶው ባለመብት, EPA

አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ ባለሥልጣን ሳይንቲስቱ ከተገደሉ ከሁለት ቀን በኋላ ለእስራኤል ቴሌቭዥን ጣቢያ "የሞህሰን ፋክሪዛሄድ ተግባር መገታት ነበረበት። እሱ የሌለባት ዓለም የተሻለች ናት" ብለዋል።

ሳይንቲስቱ የኢራን "ኦርጋናይዜሽን ኦፍ ዲፌንሲቭ ኢኖቬሽን ሪሰርች" ኃላፊ ነበሩ።

እስራኤል እንዲሁም የምዕራቡ ዓለም የደህንነት ሠራተኞችም ሳይንቲስቱ ለኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም የጀርባ አጥንት ነበሩ ይላሉ።

የፊዚክስ ባለሙያው ሞህሰን ፋክሪዛሄድ ኢራን እአአ በ1989 ከመሠረተችው "ፕሮጀክት አማድ" የተባለ ስውር ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ስማቸው ይነሳል።

ፕሮጀክቱ የኒውክሌር ቦምብ ማበለጸጊያ እንደሆነ ይነገራል።

2003 ላይ ፕሮጀክቱ እንደተዘጋ ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ተናግሯል። ሆኖም የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ ሞህሰን ፋክሪዛሄድ ፕሮጀክቱን እንዳስቀጠሉ የሚጠቁም ሰነድ 2018 ላይ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟ ሰላማዊ እንደሆና የኒውክሌር መሣሪያ ለመሥራት ሞክራ እንደማታውቅ ትከራከራለች።