የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት በአዲስ አበባ እና በጋምቤላ ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት በአዲስ አበባ እና በጋምቤላ ውስጥ ከሌሎች አካባቢዎች በተሌ ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ።
የፌደራል የኤችአይቪ ኤድስ የመከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነትና ኮምንኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል በትረ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ ከፍተኛ የቫይረሱ ስርጭት የተመዘገበው በሁለቱ አካባቢዎች መሆኑን አመልክተዋል።
እንዲሁም በሶማሌ ክልል፣ ደቡብ ክልል፣ ኦሮሚያ ክልል እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ውስጥ ደግሞ የቫይረሱ የስርጭት መጠን በአንጻራዊነት ዝቅተኛ እንደሆነ ተገልጿል።
አቶ ዳንኤል ጨምረው እንዳሉት፤ በአሁን ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ከ669 ሺህ በላይ ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፤ የቫይረሱ አገር አቀፍ የስርጭት መጠን ደግሞ 0.93 በመቶ ነው።
የኤችአይቪ/ኤድስ የስርጭት ሁኔታ ከክልል ክልል የተለያየ እንደሆነው ሁሉ ልዩነቱ በከተሞችና በገጠር አካባቢዎች ይስተዋላል። በዚህም መሠረት በከተሞች አካባቢ የበሽታው ስርጭት ከፍተኛ ነው።
አቶ ዳንኤል እንዳሉት የበሽታው ስርጭት መጠን በከተማና በገጠር ሲነጻጸር፤ በከተማ 3 ከመቶ ሲሆን በገጠር ደግሞ 0.4 በመቶ ነው።
የስርጭት መጠኑ ከአንዱ ክልል በሌላው እንዲሁም በየማኅበረሰቡ እንደሚለያይ የገለጹት አቶ ዳንኤል፤ "በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ፣ የረዥም ርቀት አሽከርካሪዎች እና ተንቀሳቃሽ ሠራተኞች አካባቢ የስርጭት መጠኑ ከፍተኛ ነው" ብለዋል።
በኢትዮጵያ የኤችአይቪ ስርጭት ከዓመት ዓመት የመቀነስ አዝማሚያ ቢኖረውም በተለያየ አካባቢ የተለያየ የስርጭት መጠንና ሁኔታ እንዳለውም ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ እና የጋምቤላ ሁኔታ
ስርጭቱ ከፍተኛ ከሆነባቸው ከተሞች አንዷ አዲስ አበባ ናት። ለዚህም ምክንያት ተብለው ከተቀመጡት አንዱ ከተማዋ ብዙ ሰዎችን ከውጪ አገር እና ከክልል ከተሞችም የምታስተናግድ መሆኗ ነው።
ሌላው ምክንያት ደግሞ አዲስ አበባ የንግድ ልውውጥ ማዕከልነቷ ነው ሲሉ አቶ ዳንኤል ተናግረዋል።
"በአዲስ አበባ አጋላጭ የሆኑ ምክንያቶች በርካታ ናቸው። ጋምቤላ ግን ትልቁን ተጽዕኖ የሚፈጥረው ባህሉ ነው። የተለያዩ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አሉ" ሲሉ ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ ለበሽታው የሚሰጠው ትኩረት እየቀነሰ መምጣቱ ይነገራል። ኤችአይቪ ኤድስን በመከላከል ረገድ የሚሠራው ሥራ ከዓመት ዓመት ማሽቆልቆሉም ተያይዞ ይጠቀሳል።
አቶ ዳንኤል እንደሚሉት፤ ባለፉት ዓመታት በቫይረሱ ምክንያት የሚመዘገበው የሞት መጠንና አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መቀነሱ መዘናጋት ፈጥሯል።
በአገር አቀፍ ደረጃ እአአ በ1991 የቫይረሱ የስርጭት መጠን 1.97%፣ በ1997 ደግሞ 3.16% ደርሶ ነበር። ይህም ከፍተኛ የሚባል ነበር። ከዚያ በኋላ የስርጭት መጠኑ እየቀነሰ መጥቶ በ2010 ላይ 1.38 በመቶ አሁን ደግሞ 0.93% ደርሷል።
ይህንን ቁጥር በማጣቀስ "የስርጭቱ መጠን ከዓመት ዓመት እየቀነሰ መምጣቱ አንዱ አዘናጊ ምክንያት ነው" ብለዋል።
ሁለተኛው ምክንያት ቫይረሱን ለመከላከል ከተለያዩ የውጪ አገሮች የሚመጣው ድጋፍ መቀነሱ ነው።
ድጋፉ ሲቀንስ መከላከልን በተመለከተ የሚሠሩ የሚዲያ ቅስቀሳና ሌሎችም ንቅናቄዎች ቀንሰዋል።"በተጨማሪም የአመራር ቁርጠኝነት ይጠይቃል። አመራሩ እንደ አጀንዳ ካልያዘው ለውጥ ማምጣት አይቻል" ሲሉም ዳይሬክተሩ አክለዋል።
ኤችአይቪ ኤድስ እና ኮቪድ-19
ኮቪድ-19 በዓለም አቀፍ ደረጃ ካስከተለው ማኅበራዊ፣ የምጣኔ ሀብታዊና መሰል ቀውሶች ውስጥ ጤናም ተጠቃሽ ነው።
አብላጫው ትኩረት ለወረርሽኙ መሰጠቱ ሌሎች ህመሞች እንዲዘነጉ፣ ህሙማንም አገልግሎት ለማግኘት እንዲቸገሩ ምክንያት ሆኗል።
በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ ከሚሞቱ ሰዎች መካከል የኤድስ በሸውታን የሚያስከትለው ቫይረስ በደማቸው የነበረ ሰዎች ይገኙበታል።
ነሐሴ አካባቢ በኮሮናቫይረስ ከሞቱ ሰዎች መካከል 28 በመቶ በደማቸው ቫይረሱ የነበረባቸው እንደሆኑና አሁን ላይ ግን አጠቃላይ ሪፖርት እንዳልተሰራ አቶ ዳንኤል ተናግረዋል።
"በአብዛኛው መገለልና መድልዎን በመፍራት መድኃኒታቸውን ራቅ ካለ ቦታ የሚወስዱ ቫይረሱ ያለባቸው ዜጎች በኮቪድ-19 ሳቢያ ትራንስፖርት ሲቋረጥ መድኃኒት ማግኘት አልቻሉም" ሲሉም ምክንያቱን አስረድተዋል።
በሌላ በኩል የጤና ተቋሟት ሙሉ አቅማቸውን ኮቪድ-19ኝን ወደ መከላከል በማዞራቸው ለኤችአይቪ ኤድስ የሚሰጠው ትኩረት ተቀዛቅዟል።
ዓለም አቀፉ የኤችአይቪ ኤድስ ቀን ኢትዮጵያ ውስጥ 'ኤችአይቪን ለመግታት ዓለም አቀፋዊ ትብብር የጋራ ኃላፊነት' በሚል መሪ ቃል ትናነት ተከብሯል።















