ዝነኛዋ ሞዴል ሐሊማ በሃይማኖት ምክንያት ከፋሽን ዓለም ራሷን አገለለች

ዝነኛ ሞዴል ሐሊማ አደን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዝነኛ ሞዴል ሐሊማ አደን

ከሶማሊያዊ ቤተሰብ የተገኘችው አሜሪካዊቷ ዝነኛ ሞዴል ሐሊማ አደን በሃይማኖት ምክንያት በፋሽን ኢንዱስትሪው ላለመቆየት ወስኛለሁ ስትል አስታወቀች።

ለዚህ ውሳኔ ያበቃት የፋሽን ሥራ ከሃይማኖቴ እሴቶች ጋር ስለሚቃረን ነው ብላለች። የ23 ዓመቷ ሐሊማ በዝነኛዎቹ የብሪታኒያ ቮግ፣ የአረቢያ ቮግና አሉር መጽሔቶች ሽፋን ላይ ለመውጣት የበቃች ገናና ሞዴል ነበረች።

በኢኒስታግራም ሰሌዳዋ ላይ ለአድናቂዎቿ በተወችው ማስታወሻ እንዳለችው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ቤት እንድትውል ባደረጋት ጊዜ ከራሷ ጋር ስለሕይወቷ ለማሰላሰል እንደቻለች ጠቅሳ “እንደ አንዲት ሙስሊም የኔ እሴቶች ምንድናቸው?” በሚል አእምሮዋ ጥያቄ ማንሳቱን አውስታለች።

ከሃይማኖቷ አስተምህሮ የሚቃረኑ የሞዴሊንግ የሥራ እድሎች ሲቀርቡላት መቀበሏ የራሷ ጥፋት እንደሆነና በዚህ ረገድ ማንንም መውቀስ እንደማትሻ አብራርታለች።

ሒጃብ የምትለብስ ሙስሊም ሞዴል የሚገጥማትን ፈተናዎችን በማስታወሻዋ ጠቃቅሳለች። በኢንዱስትሪው የሙስሊም ሴት ሞዴል እጥረት መኖሩን ጠቅሳ ይህ መሆኑ ደግሞ ሒጃብ መልበስ ለአንዲት ሙስሊም ያለውን ትርጉሙ በፋሽን ኢንዱስትሪው የሚረዳ ሰው እንዳይኖር አድርጓል ትላለች።

የኢኒስታግራም መልእክቷን ተከትሎ በርካታ አስተያየቶች የተሰነዘሩ ሲሆን ዝነኞቹ ሞዴሎችና የሥራ ባልደቦቿ ቤላ፣ ጂጂ ሐዲድ እና ሪሐና አበረታተዋታል። ሐሊማ የተወለደችው በኬንያ ስደተኞች ካምፕ ውስጥ ሲሆን ከሶማሊያ ስደተኛ ቤተሰቦች ነበር የተገኘችው።

በ6 ዓመቷ ወደ አሜሪካ አቅንታለች። በ18 ዓመቷ የሞዴል ወኪል ግዙፉ አይኤምጂ ኩባንያ ለሞዴልነት መልምሏታል። በኋላም ለወይዘሪት ሜኔሶታ የቁንጅና ውድድር ላይ የመጨረሻ ዙር መድረስ ችላ ነበር።

በቁንጅና ውድድሩ ታሪክ ሒጃብ ለብሳ የተወዳደረች የመጀመርያዋ ሴት ስለነበረችም ትልቅ ትኩረት መሳብ ችላ ነበር። ከዚያ በኋላ በትልልቅ የፋሽን መድረኮች በመቅረብ ከሒጃብ ጋር እምብዛም ገላጣ ያልሆኑ ወግ ያላቸው (modest) አለባበሶችን በማስተዋወቅ እውቅናን አትርፋለች።

የአቀንቃኟን ሪሐና “ፌንቲ ቢዩቲ” እንዲሁም የካንዬ ዌስትን “ዩዚ” ብራንዶችን ያስተዋወቅችውም ሐሊማ ነበረች፤ በዚህም ዝናዋ ጨምሮ ነበር። በኢኒስታግራም መልእክቷ ሪሐና ለሰጠቻት ድጋፍና ሒጃብ ለብሳ እንድትሰራ ስላበቃቻት ምስጋናዋን አቅርባላታለች።

ሞዴል ሐሊማ በፋሽን ኢንዱስትሪው ቆይታዋ ከሃይማኖታዊ አስተምህሮቷ ሊያሰናክሏት የሚችሉ በርካታ አጋጣሚዎች እንደነበሩ ጠቅሳለች። ከነዚህም መሐል ሂጃብ ሳትለብስ ፋሽን ሞዴሊን ለመስራት መስማማትና በቀን አምስት ጊዜ ጸሎት ለማድረስ አለመቻሏ ናቸው።

ከህሊናዋ የማይታረቁ ተግባሮች ውስጥ በመሳተፏ ሆቴል ውስጥ ገብታ ብቻዋን ታለቅስ እንደነበር ጠቅሳለች። “እውነቱ በፋሽን ኢንዱስትሪ ቆይታዬ ደስተኛ አልነበርኩም” ስትል ደምድማለች።