'ከሞት የተነሳው' ኬንያዊ ጉዳይ እያነጋገረ ነው

አስክሬን ማቆያ ክፍል

የፎቶው ባለመብት, SHUTTERSTOCK

በኬንያዋ ኪሪቾ ግዛት አንድ ግለሰብ ድንገት ተዝለፍልፎ ከወደቀ በኋላ በጤና ባለሙያዎች ሕይወቱ አልፏል ከተባ በኋላ መተንፈስ መጀመሩ አነጋጋሪ ሆኗል።

ግለሰቡ በመኖሪያ ቤቱ ሳለ ነበር ድንገት ተዝለፍልፎ የወደቀው፤ ከዚያም ወደ ሆስፒታል የተወሰደ ሲሆን በሆስፒታሉ ያሉ የሕክምና ባለሙያዎች ግለሰቡ ሕይወቱ ማለፉን ካስታወቁ በኋላ አስክሬኑ ሊገነዝ ሲዘገጃጅ ድንገት መተንፈስ ጀምሯል ተብሏል።

የ32 ዓመቱ ፒተር ኪጀን በሆስፒታል ሠራተኞች ሕይወቱ አልፋለች ተብሎ ስለታመነ አስክሬኑ ወደ ሬሳ ማቆያ እንዲገባ መደረጉን መገናኛ ብዙሀን ጨምረው ዘግበዋል።

ፒተርን ወደ ሆስፒታል ይዞት የመጣው ታናሽ ወንድሙ ለስታንዳርድ ጋዜጣ ሲናገር ''ነርሷ ወንድሜ ድንገተኛ ክፍል ውስጥ ከመድረሱ በፊት ሕይወቱ ማለፉን ነገረችኝ'' ብሏል።

ነገር ግን እንደ ሆስፒታሉ ዋና ኃላፊ ከሆነ ቤተሰቦቹ የሞቱ ማረጋገጫ ወረቀት ሳይወስዱ አስክሬኑን በራሳቸው ፈቃድ ወደ ሬሳ ማቆያ ወስደውታል።

ፒተር ኪጀን ወደ ሆስፒታል ሲወሰድ ከባድ የጤና እክል ገጥሞት የነበረ ሲሆን ከሞት ከተረፈ በኋላ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረገው ቆይታ ከዚህ በኃላ ሙሉ ሕይወቴን በሐይማኖታዊ ስራ ነው የማሳልፈው ብሏል።

በወቅቱ የሬሳ ማቆያ ክፍል ሰራተኞች አስክሬኑን ለማዘገጃጀት በሚጣደፉበት ወቅት ድንገት መተንፈስ መጀመሩ በእጅጉ ነበር ያስደነገጣቸው።

''የአስክሬን ክፍሉ ሰራተኛ ስልክ ደወለችልኝና ስሄድ አንዳንድ የወንድሜ የሰውነት ክፍሎች ሲንቀሳቀሱ ተመለከትን። ሁላችንም በጣም ደነገጥን። ሞቷል ተብሎ ሬሳ ማቆያ ክፍል ውስጥ የገባ ሰው እንዴት ሊንቀሳቀስ ይችላል? ለማመን የሚከብድ ነበር'' ብሏል ታናሽ ወንድሙ።

ፒተር በበኩሉ ሞቷል ተብሎ መወሰኑ እና ወደ አስክሬን ክፍል መወሰዱ አስደንግጦኛል ብሏል።

''ድንገት ስነቃ የት እንዳለሁ እንኳን አላውቅም ነበር። ነገር ግን ፈጣሪ ሕይወቴን ስላተረፈልኝ በጣም ደስተኛ ነኝ። ከዚህ በኋላ ሕይወቴን ሙሉ እሱን በማገልገል ነው የማሳልፈው'' ብሏል።

ሞቷል የተባለው ፒተር ከአስክሬን ማቆያ ወደ ህክምና ክፍል ከተወሰደ በኋላ በጥሩ ጤንነት ላይ ይገኛል። በቅርብ ቀናት ውስጥ ከሆስፒታል እንደሚወጣም ይጠበቃል።