ትራምፕ መሸነፋቸው አምነው ሊቀበሉ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጆ ባይደን መሸነፋቸውነ ሊቀበሉ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጡ።
ትራምፕ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ "ጆ ባይደን በ 'ኤሌክቶራል ኮሌጅ' የአሜሪካ ፕሬዝዳንት መሆኑ ከተረጋገጠ መሸነፌን ልቀበል እችላለሁ" ብለዋል።
"ኤሌክቶራል ኮሌጅ" የሚባለው ከየግዛቱ የተወከሉ የዲሞክራት ፓርቲ ተወካዮች በአንድ ተሰብስበው በመደበኛ ሁኔታ ለተመራጩ ፕሬዝዳንት ድምጽ የሚሰጡበት ኩነት ነው።
እንደሚታወቀው አሜሪካዊያን ድምጽ የሚሰጡት በቀጥታ ለፕሬዝዳንት እጩዎች ሳይሆን ለግዛት ወኪሎች ነው። የግዛት ወኪሎች ቁጥር የሚወሰነው ደግሞ በግዛቱ የሕዝብ ብዛት ነው።
እነዚህ የግዛት ወኪሎች በየግዛቱ ሕዝብ የሰጣቸውን ድምጽ በአንድ ተሰብስበው ለተመረጠው ፕሬዝዳንት ሲሰጡ የተመራጭ ፕሬዝዳንቱ ፕሬዝዳንት መሆን ፍጻሜ ይሆናል።
የግዛት ምርጫ ተወካዮች ግን የግድ ሕዝብ ምረጥልኝ ብሎ የሰጣቸውን ድምጽ መከተል አይገደዱም።
ትራምፕ ትናንት ሐሙስ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ በኖቬምበር 3 የተደረገውን ምርጫ ውጤት መቀበል ቀላል እንዳልሆነ ደጋግመው ተናግረዋል።
ምርጫው ድብን ያለ መጭበርበር የነበረበት ነው ሲሉም በመረጃ ያልተደገፈ ክሳቸውን በድጋሚ አስተጋብተዋል።
በኖቬምበሩ ምርጫ ጆ ባይደን 306 የግዛት ወኪሎችን (ኤሌክቶራል ኮልጅ) ድምጽ በማግኘት ዶናልድ ትራምፕን በማያሻማ ልዩነት አሸንፈዋል። ዶናልድ ትራምፕ ያገኙት ኤልክቶራል ኮሌጅ ድምጽ 232 ብቻ ነው።
ሆኖም ይህ የአሐዝ ልዩነት ሁለቱ ተፎካካሪዎች በየግዛቶቹ የነበራቸውን ተቀራራቢ ድምጽ አያሳይም።
ይህም የሆነው በአሜሪካ ምርጫ አካሄድ በአንድ ግዛት በርካታ ቁጥር ያገኘው እጩ ሁሉንም ለግዛቱ የተመደቡ የወኪሎችን ድምጽ ቁጥሮች ጠቅልሎ ስለሚወስድ ነው። ይህን አሰራር የማይከተሉት የአሜሪካ ግዛቶች ሁለት ብቻ ናቸው።
አንድ እጩ አሸናፊ ለመሆን የሚያስፈልገው ኤሌክቶራል ድምጽ 270 ነው።
የግዛት ወኪሎች (ኢሌክተርስ) በሚቀጥለው ወር ተገናኝተው የምርጫ ሂደቱን መርሐግብር የሚያሟላውን ኩነት ይፈጽማሉ፤ ይህም በአንድ ቦታ ተገናኝቶ የግዛታቸው ሕዝብ የሰጣቸውን ድምጽ ለተመራጩ ፕሬዝዳንት መስጠት ነው።
ትራምፕና ጠበቆቻቸው እንደ ፔንሲልቬኒያ ባሉ ወሳኝ ግዛቶች ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል የክስ ፋይል ሲከፍቱ ነበር የሰነበቱት። ሆኖም በአብዛኛዎቹ ግዛቶች የትራምፕና ጠበቆቻቸው ክሶች "ውሀ የሚቋጥሩ አይደሉም" በሚል ውድቅ ተደርገውባቸዋል።
በዚህ ሳምንት መጀመርያ ነበር ትራምፕ ለመጀመርያ ጊዜ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ወደ ዋይት ሐውስ የሚገቡበት ሂደት እንዲጀመር ይህንኑ ሥራ ለሚያቀላጥፈው መሥሪያ ቤት ይሁንታን የሰጡት። በሚሊዮን የሚቆጠር በጀትም ለዚሁ መሥሪያ ቤት ለቀዋል።
ይህ ዘግይቶ የመጣው የትራምፕ መለሳለስ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአገር ምስጢር የሚባሉ መረጃዎችን በየሰዓቱ እንዲያገኙ የሚያስችላቸው ሆኗል።
ሐሙስ ዕለት ትራምፕ ከጋዜጠኞች የተነሳላቸው አንዱ ጥያቄ የግዛት ወኪሎች (ኤሌክቶሬትስ) ለባይደን ድምጽ ከሰጡ ዋይት ሐውስን ይለቃሉ ወይ የሚል ነበር። ትራምፕ ሲመልሱም፥ "እንዴት አለቅም፣ እለቃለሁ እንጂ፣ እናንተም ይህን ታውቃላችሁ" ብለዋል።
ሆኖም ትራምፕ ይህን ካሉ በኃላ አስከትለው፣ "የግዛት ወኪሎቹ ግን ለባይደን ድምጽ ከሰጡት ስህተት ነው የሚሆነው" ሲሉ እርስ በእርሱ የሚጋጭ ነገር ተናግረዋል።
"ሽንፈቴን መቀበል የከበደኝ ምርጫው በስፋት መጭበርበሩን ስለዋውቅ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
በጆ ባይደን የፕሬዝደንታዊ ክብረ በዓል ይገኙ እንደሆነ ተጠይቀው ትራምፕ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
በአሜሪካ ታሪክ አንድ ተሸናፊ ፕሬዝዳንት ሽንፈትን ውጦ ለመቀበል ሲያንገራግር ትራምፕ ምናልባትም የመጀመርያው ሳይሆኑ አይቀርም።












