በመዝገበ ቃላት ፡ 2020 በርካታ አዳዲስ ቃላት በመዝገበ ቃላት ላይ የተመዘገቡበት ዓመት ተባለ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ታዋቂው የመዝገበ ቃላት አዘጋጅ ኦክስፎርድ ዲክሽነሪስ የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝን ጨምሮ ብዙ ክስተቶችን ባስተናገደው የዘንድሮው የአውሮፓውያኑ ዓመት በርካታ ያልተጠበቁና ያልተገመቱ አዳዲስ ቃላት የተመዘገቡበት ዓመት እንደሆነ አስታውቋል።
በ2020 በአዲስ መልኩ የተመዘገቡት ቃላት የሰዎችን አኗኗር በአግባቡ ለመግለጽ ወሳኝ በመሆናቸው ነው ተብሏል።
በዘንድሮው የኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት ከተካተቱት አዳዲስ ቃላት መካከል ኮቪድ-19፣ ሎክዳውን (የእንቅስቃሴ ገደብ)፣ ብላክ ላይቭስ ማተር (ለጥቁሮች ህይወት ጥበቃ የሚደረገው እንቅስቃሴ) እና ኪ ወርከርስ (ወሳኝ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች) ይገኙበታል ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪ ወረርሽኝ የሚለውን ቃል የሰው ልጅ ከዚህ በፊት ይጠቀምበት ከነበረው በ 57000% ጨምሮ ጥቅም ላይ እንዳዋለው ኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት ገልጿል።
የኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት ፕሬዝደንት ካስፐር ግራትዎል እንደሚሉት እንደዘንድሮ በርካታ ቃላት በአንድ ጊዜ ሲመዘገቡ አላዩም።
''የኦክስፎርድ ቡድን በመቶዎች የሚቆጠሩ በርካታ ጠቃሚ አዳዲስ ቃላትን ሲለይና ሲመረምር ነበር። በዚህ ዓመት ከተፈጠሩት በርካታ ነገሮች አንጻር ቡድኑ ሥራ በዝቶበት ነበር።''
''ያልተጠበቀና ትንሽ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው። ቃላት እስኪያጥረን ድረስ ያስጨነቀን ዓመት መጠናቀቂያ ላይ እንደዚህ አይነት አዳዲስ ቃላት በመዝገበ ቃላት ውስጥ መካተታቸው ይህንን ዓመት ልዩ ያደርገዋል'' ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
የሚዲያ አርታኢው አሞል ራጃን እንደሚለው ሁሉም ቋንቋዎች ያድጋሉ፤ ከሚፈጠሩ ነገሮች አንጻር እራሳቸውን ያሻሽላሉ።
በዚህ መሰረት ከመጠን በላይ መረጃ በተለያዩ መንገዶች ለሰዎች በሚደርሱበት በዚህ ዘመን፤ መገናኛ ብዙሃን ያለ ገደብ መረጃዎችን በሚያሰራጩበት በዚህ ወቅት አዳዲስ ቃላት ጥቅም ላይ መዋላቸውና የነበሩትም እየተሻሻሉ መሄዳቸው የሚጠበቅ ነገር ነው።
ምንም እንኳን ኮሮናቫይረስ የሚለው ቃል ከዚህ በፊት ይታወቅ የነበረ ቢሆንም ኮቪድ-19 የሚለው ግን በስፋት ጥቅም ላይ የዋለው በዚህ የፈረንጆቹ ዓመት ነው።
ዜናዎች አዳዲስ ቃላትና አዳዲስ አጠቃቀሞችን ማስተዋወቃቸው ለእኔ አስገራሚ ነበር ይላል አሞል።
ብላክ ላይቭስ ማተር - ምንም እንኳን ብላክ ላይቭስ ማተር የሚለው ሐረግ ከጆርጅ ፍሎይድ ግድያ በፊትም ጥቅም ላይ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ግን በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል።
በሌላ በኩል ደግሞ እንደ 'ብሬግዚት' ያሉት ቃላት መጀመሪያ አካባቢ ላይ በመላው ዓለም በዜናዎችና በማኅበረሰቡ ዘነድ በስፋት ጥቅም ላይ ሲውሉ የነበረ ቢሆንም ከኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ ዜና በኋላ ግን ሰዎች ቃላቱን የመጠቀም ፍላጎታቸው 80 በመቶ መቀነሱ ተስተውሏል።
''አንዳንድ ታሪካዊ ቃላት በድጋሚ ጥቅም ላይ መዋል መጀመራቸውን አስተውለናል። ሌሎች ደግሞ እንደ ድሮው ጥቅም ላይ እየዋሉ አይደለም። ዘንድሮ የተስተዋለው የጤና፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ የእንግሊዝኛ ቋንቋ በፍጥነት እንዲያድግ አድርጎታል'' ይላል አሞል።
የኮቪድ-19 ቋንቋ
የኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት ሪፖርት እንደሚጠቁመው ኮሮናቫይረስ የሚለው ቃል ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው በፈረንጆቹ 1960ዎቹ አካባቢ ሲሆን በብዛት ጥቅም ላይ የሚውለው በተመራማሪዎችና በጤና ባለሙያዎች አካባቢ ብቻ ነበር።
ነገር ግን ከሚያዝያ ወር ጀምሮ ኮሮረናቫይረስ በዓለማችን እጅግ ታዋቂውና በብዛት ጥቅም ላይ የዋለው የእንግሊዝኛ ቃል መሆን ችሏል። ነገር ግን የኮሮናቫይረስ ታዋቂነት ለአንድ ወር ብቻ ነበር የቆየው፤ ግንቦት ወር ላይ ደግሞ ኮቪድ-19 መጥቶ የኮሮረናቫይረስን ቦታ ተረክቧል።
ምንም እንኳን በመላው ዓለም ኮሮረናቫይረስ የሚለው ቃል አሁንም በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ቢሆንም ኮቪድ-19 ግን የአንደኝነቱን ቦታ ይዟል።
የካቲት ወር ላይ የዓለም ጤና ድርጅት ከፍተኛ ኃላፊዎች በኮሮናቫይረስ ሳቢያ የሚከሰተውን ወረርሽን ኮቪድ-19 ብለን ሰይመነዋል ሲሉ አስታውቀዋል።
በጄኔቫ ለተሰበሰቡት ጋዜጠኞች "ለበሽታው ስያሜ አግኝተንለታል፤ ኮቪድ-19 ተብሎ ይጠራል" ያሉት የዓለም ጤና ድርጅት የበላይ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ነበሩ።
አዲሱ ስያሜ "ኮሮና"፣ "ቫይረስ" እና "ዲዝዝ" (በሽታ) ከሚሉት ቃላት እንዲሁም ከተከሰተበት ዓመተ ምህረት 2019 የተወሰደ መሆኑ ታውቋል።
ከዚህ በተጨማሪ ከኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በርካታ ቃላት ከዚህ በፊት የነበሩትም ሆነ አዳዲሶቹ በስፋት ጥቅም ላይ እንደዋሉ የኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት ሪፖርት ይገልጻል።
በዚህም መሰረት እንደ ሎክዳውን፣ ፌስ ማስክ (የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ)፣ ፒፒኢ (የሕክምና ባለሙያዎች የመከላከያ አልባሳት)፣ ሜዲክስ (የሕክምና ባለሙያዎች) እንዲሁም ኢሴንሻል ወርከርስ (ወሳኝ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች) በብዛት ጥቅም ላይ ከዋሉት መካከል ይገኙበታል።
ከመጋቢት ወር ጀምሮ ደግሞ ወረርሽኙን ተከትሎ ከ 300% በላይ ዕድገት ያሳዩት ሁለት ቃላት 'ሪሞት' (ሩቅ) እና 'ሪሞትሊ' (በርቀት) ናቸው። የዙም ስብሰባዎች በዚህ ዓመት በአጠቃቀም ረገድ ከፍተኛ ጭማሪ ማድረጋቸው ምንም አያስደንቅም።
ከዚህ በተጨማሪ ለአየር ንብረት ለውጥ የተሰጠው የሚዲያ ሽፋን እና ተያያዥ ቃላት ጥቅም ላይ የዋሉበት መጠን በዚህ ዓመት በወረርሽኙ ምክንያት መቀነሱን የኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት ሪፖርት ጠቁሟል።















