የግሪክ ስደተኞች፡በስደት ልጁ ሰምጦ የሞተበት አፍጋኒስታናዊ ክስ ተመሰረተበት

ግሪክ ጥገኝነት የጠየቀውን አፍጋኒስታናዊ አባት የስድስት አመት ልጁ በስደት መሞቱን ተከትሎ ክስ መስርታበታለች።
ህፃኑ ቱርክን ሲሻገሩ ጀልባው ሞልቶ በማጋደሉ ሰምጦ እንደሞተም ተገልጿል።
አፍጋኒስታናዊው አባት የልጁን ህይወት አደጋ ውስጥ በመክተት የተከሰሰ ሲሆን እንዲህም አይነት ክስ ሲቀርብ በአገሪቷ ታሪክ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።
ጀልባዋ ሳሞስ በተባለች ደሴት የሰመጠችው ከአስር ቀናት በፊት ሲሆን አባትየው የባህር ዳርቻ ላይ ደርሶ እርዳታ ቢያገኝም የህፃኑ ልጅ አስከሬን በነጋታው ተገኝቷል።
መነሻቸውን ከቱርክ ያደረጉ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችም በባለፈው አመት ግሪክ ገብተዋል ተብሏል።
ከ1 ሺህ 400 በላይ ስደተኞችም ሳሞስ ደሴት እንደደረሱ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።
የ25 አመቱ አፍጋኒስታናዊ አባት ልጁን አደጋ ውስጥ ከቷል በሚለው ክስ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘም የስድስት አመት እስር ይጠብቀዋል።
የግለሰቡ ጠበቃ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሌሊት ላይ ለጠረፍ ጠባቂዎች የድረሱልኝና የእርዳታ ጥሪ ቢያደርግም፤ አስከሬኑን ለመፈለግ ከስድስት ሰዓታት በኋላ ልከዋል ብሏል።
እርዳታው ይህንን ያህል ሰዓታት እንደዘገየም ፖሊስ ምርመራ ሊያደርግ እንደሚገባም ጠበቃው ተናግረዋል። አባትየው እርዳታ ለመፈለግ ከተማውን ሲያስስም እንደነበር ያስረዱት ጠበቃው በዚህም ሊቀጣ አይገባም ይላሉ።
የጠረፍ ጠባቂዎች ቃለ አቀባይ በበኩላቸው ወቅቱ ጨለማ በመሆኑ ስራቸው ላይ እክል እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ።
በአፍጋኒስታንና ሶርያ የተፈጠረውን ግጭት በመፍራት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በቱርክ አድርገው አውሮፓ ለመድረስ መጉረፍ የጀመሩት ከጎሮጎሳውያኑ 2015 ጀምሮ ነው።
በመቶዎች የሚቆጠሩትም የግሪክ ደሴቶችን ሊሻገሩ በሚሞክሩበት ወቅት ሰምጠው ሞተዋል።
ከአመት በኋላም ስደተኞች ወደ አውሮፓ እንዳይሻገሩ ለማድረግ ቱርክ የተስማማች ሲሆን ስደተኞች በዚያው በቱርክ እንዲወሰኑም ከፍተኛ የሆነ ገንዘብም ለመስጠትም የአውሮፓ ህብረት ቃል ገብቶ ነበር።
ነገር ግን በአውሮፓ ህብረትና በቱርክ ያለውን ውጥረት ተከትሎ እንዲሁም ቃል የተገባውም የእርዳታ ገንዘብ በቂ ባለመሆኑ ቱርክ ከግሪክ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር በተወሰነ መልኩ ከፍታለች።
መስከረም ወር ላይ በግሪክ፣ ሌዝቦስ ደሴት የስደተኞች መጠለያ ካምፕ በእሳት በመቃጠሉ 12 ሺህ የሚሆኑ ስደተኞች ቤት አልባ ሆነዋል።
አራት አፍጋኒስታናውያን ስደተኞችም እሳቱን በማቀጣጠል ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል።












