ሕንዳውያኑ ለሠርጋቸው ‘በጣም’ ተቃቅፈው በተነሱት ፎቶ ተወገዙ

የፎቶው ባለመብት, AKHIL KARTHIKEYAN
ለኪሽሚ እና ህሩሺ መስከረም ላይ ነበር የተጋቡት። ሠርጋቸውን በወረርሽኙ ሳቢያ በጥቂት ሰው ብቻ ነበር ያከናወኑት።
ጥንዶቹ ከሠርጉ በኋላ ፎቶ ለመነሳት ተስማሙ።
ለኪሽሚ እና ህሩሺ ነጭ ብርድ ልብስ አድርገው ሲሳሳቁ እንዲሁም ተቃቅፈው ፎቶ ተነስተው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ለቀቁ።
ከዛም ተቃቅፈው የተነሷቸው ፎቶግራፎች የማኅበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ሆኑ። ብዙዎችም ተቿቸው። ጥንዶቹ ግን ፎቶዎቹን ከማኅበራዊ ሚዲያ ገጻችን አናነሳም ብለዋል።
ለኪሽሚ በቅርቡ ነው በምህንድስና የተመረቀችው። ህሩሺ ደግሞ ለቴሌኮም ድርጅት ይሠራል።
አምና ቤተሰቦቻቸው ካስተዋወቋቸው በኋላ በፍቅር እንደወደቁና ለመጋባት እንደወሰኑ ለኪሽሚ ትናገራለች።
ድል ባለ ሠርግ እንጋባለን ብለው ሲጠብቁ ወረርሽኙ ተከሰተ።
ኮላም በተባለችው የለኪሽም ትውልድ ከተማ በሚገኝ ቤተ አምልኮ 50 ሰው ብቻ ጋብዘው ተሞሸሩ።
ሠርጋችን እንዲህ በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም ብለውም በተለያዩ የሕንድ ግዛቶች ድንቅ ፎቶዎች ለመነሳት ተነጋገሩ።
ህሩሺ ፎቶዎቹ ፍቅራቸውን የሚያሳዩ እንዲሆን ይፈልግ ነበር።
ስለዚህም ከሆቴላቸው ነጭ ብርድ ልብስ ተውሰው ወደ ሻይ እርሻ አቀኑ።
“በጣም እየተዝናናንና ስንስቅም ነበር” ትላለች ለኪሽሚ።
ጥንዶቹ በከፊል እርቃናቸውን ሆነው፣ በነጩ ብርድ ልብስ ተሸፍነው ተቃቅፈው የተነሷቸው ፎቶዎች ፌስቡክ ላይ ሲወጡ አነጋጋሪ ሆኑ።
አንዳንዶች አሳፋሪ ሌሎች ደግሞ ሀፍረተ ቢስ አሏቸው። ‘የኮንዶም ማስታወቂያ ይመስላል’ እንዲሁም ‘ይህን አይነት መተቃቀፍ እዛው ቤታችሁ’ ሲሉ አስተያየት የሰጡም አሉ።
ለሁለት ቀናት ያለማቋረጥ ሰው እንደሰደባቸው ጥንዶቹ ይናገራሉ።
ለኪሽሚ፤ “ከነጩ ብርድ ልብስ ስር ልብስ አድርጋችኋል? እያሉ ጠይቀውናል። የሰው ትኩረት ለመሳብ ነው ፎቶውን የተነሳችሁትም ተብለናል” ስትል የገጠማቸውን ተናግራለች።
አብዛኛው ሰው ትኩረቱን ያደረገው ላኪሽሚ ላይ ነበር። ከባለቤቷ ይልቅ የተብጠለጠለችው እሷ ነበረች።
“ይሰድቡኝ የነበሩት ሴቶችም ጭምር ነበሩ። ያለ መዋቢያ የተነሳኋቸውን የድሮ ፎቶዎች እየለጠፉ ‘እንዴት እንደምታስጠላ ተመልከቱ’ ሲሉ ነበር” ትላለች።
ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን ጥንዶቹን የሚደግፉ ሰዎች ድምጻቸውን ማሰማት ጀመሩ። ፎቶዎቹ ቆንጆ እንደሆኑና ጥንዶቹ የሚሰድቧቸውን ሰዎች ችላ እንዲሏቸው ያበረታቷቸው ጀመር።
ለኪሽሚ የሚደግፏቸው ሰዎች መኖራቸው እንዳስደሰታት ትናገራለች።
መጀመሪያ ላይ ቤተሰቦቻቸው በፎቶዎቹ ግራ ተጋብተው ነበረ። ጥንዶቹ ለምን ፎቶዎቹን መነሳት እንደፈለጉ ሲነግሯቸው ግን ተረድተዋቸዋል።
አንዳንድ ዘመዶቻቸው ግን “ባህላችንን የሚጻረር ፎቶ ነው” ብለው ለኪሽሚ እና ህሩሺና ከቤተሰብ የዋትስአፕ ቡድን አስወጥተዋቸዋል።
ሆኖም ግን ጥንዶቹ ፎቶዎቹን ከማኅበራዊ ሚዲያ ላለማንሳት ቆርጠዋል።
“ፎቶዎቹን ካጠፋናቸው አጥፍተን ነበር ብሎ እንደማመን ነው። እኛ ግን ምንን ስህተት አልሠራንም። ትችቶቹ ከባድ ቢሆኑም ማኅበረሰባችንን ስለምናውቀው አንገረምም” ብላለች ለኪሽሚ።












