የታንዛንያ ዋነኛ ተቃዋሚዎች ምርጫው ዳግም መካሄድ አለበት አሉ

የታንዛኒያ ፕሬዝደንት ጆን ማጉፉሊ

የፎቶው ባለመብት, Gettyimages

የምስሉ መግለጫ, የታንዛንያ ፕሬዝደንት ጆን ማጉፉሊ

የታንዛንያ ሁለት ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጫው ተጭበርብሯል በማለት ዳግም ምርጫ እንዲካሄድ አሳሰቡ።

ቻዴማ እና ኤሲቲ-ዋዛሌንዶ የተሰኙት ሁለቱ ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ የፊታችን ሰኞ የሚካሄድ ሰልፍ በመላው አገሪቱ ጠርተዋል።

ተቃዋሚዎቹ ተጭበርብሯል ባሉት ምርጫ ታንዛንያን እየመሩ የሚገኙት ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ በሰፊ ደምጽ በድጋሚ ማሸነፋቸው ታውጇል።

ብሔራዊ የምርጫ ኮሚሽን ስለምርጫው መጭበርበር የተነሱ ጥያቄዎችን ውድቅ አድርጎ ነበር።

ኮሚሽኑ እንዳስታወቀው በምርጫው ፕሬዚዳንቱ 84 በመቶ ድምጽ ሲያገኙ የማጉፉሊ ዋነኛ ተቀናቃኝ ቱንዱ ሊሱ ደግሞ 13 በመቶ ደምጽ አግኝተዋል ብሏል።

ቱንዱ ሊሱ በረቡዕ ምርጫ የድምጽ መስጫ ቆሮጆዎች መጭበርበራቸውን እና የፓርቲያቸው ወኪሎች ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እንዳይገቡ መከልከላቸውን ተናግረዋል።

“በቅድሚያ በተቻለ ፍጥነት ዳግም ምርጫ እንዲካሄድ እናሳስባለን። ጥያቄያችን ምላሽ እስከሚያገኝ ድረስ በመላው አገሪቱም ሰላማዊ እና ቀጣይነት ያላቸው ሰልፎችን እንጠራለን” ብለዋል ሁለቱ ፓርቲዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ።

የቻዴማው ዕጩ የነበሩት ቱንዱ ሊሱ ውጤቱን እንደማይቀበሉ ገልጸው ነበር።

ምርጫው "በታንዛንያም ሆነ በዓለም አቀፍ ህጎች መሠረት የተካሄደ አይደለም። አንዳንዶች የመንግሥትን ሃብት ያለአግባብ በመጠቀም ስልጣን ላይ ለመቆየት ያደረጉት ሂደት ነው" ሲሉ ምክንያታቸውን አስቀምጠዋል።

የብሔራዊ ምርጫ ኮሚሽን ኃላፊ ሴሚሰቶክለስ ካኢጃጌ፤ ድምጽ መስጫ ኮሮጆዎች ተጭበርብረዋል የሚለው ክስ በማስረጃ የተደገፈ አይደለም ብለዋል።

የምስራቅ አፍሪካ አገራት ተወካዮች ምርጫው “አግባብነት ባለው መልኩ የተካሄድ ነው” ያሉ ሲሆን በታንዛኒያ የአሜሪካ ኤምባሲ ግን ምርጫውን ተከትሎ የተመዘገው ውጤት ላይ ጥያቄ አንስቷል።

ኤምባሲው "አግባብ ያልሆኑ የምርጫ አሠራሮች እና በምርጫው ውጤት ላይ ከፍተኛ የድምፅ ልዩነት መኖሩ በውጤቱ ተዓማኒነት ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬን ይፈጥራሉ። የታንዛንያ መንግሥት ለዴሞክራሲያዊ እሴቶች ያለው ቁርጠኝነትም ያሳስባል" ብሏል።

ማጉፉሊ ከእአአ 2015 ጀምሮ ታንዛኒያን በፕሬዝዳንትነት ሲመሩ ቆይተዋል። ፓርቲያቸው ሲሲኤም ደግሞ ከ1961 የታንዛኒያ ነጻናት ጀምሮ አገሪቱን ሲያስተዳድር ቆይቷል።