ኤርዶጋን ዜጎቻቸውን የፈረንሳይ ምርትን አትጠቀሙ አሉ

የቱርክ ፕሬዝደንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቱርኩ ፕሬዝደንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን ቱርካውያን የፈረንሳይ ምርትን ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ጥሪ አቀረቡ። በቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው በፈረንሳይ በሚገኙ ሙስሊሞች ላይ ጫና እየደረሰ ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ኤርዶጋን የፈረንሳዩን ፕሬዝደንት የአዕምሮ ጤና ምርመራ ያስፈልጋቸዋል ማለታቸው ይታወሳል። ኤርዶጋን ይህን ያሉት ፕሬዝደንት ማክሮን ጽንፈኛ እስላማዊነትን ለመዋጋት ቃል መግባታቸውን ተከትሎ ነው።

ፈረንሳያዊው መምህር አወዛጋቢውን የነብዩ መሐመድን የካርቱን ምስሎች ክፍል ውስጥ በማሳየቱ አንገቱ ተቀልቶ መገደሉን ተከትሎ ፕሬዝደንት ማክሮን በጉዳዩ ላይ ጠንከር ያለ አቋም እየንጸባረቁ ይገኛሉ።

የፈረንሳይ መንግሥትም የአንድን ማህበረሰብ ወይም እምነት ተከታዮችን ስሜት ለመጠበቅ ሲባል የሰዎች የመናገር መብት ሊገደብ አይደባም የሚል ጠንካራ አቋም ይዟል።

ፈረንሳይ በያዘችው አቋም ማክሮን ላይ የሰላ ትችት የሰነዘሩት ኤርዶጋን ብቻ አይደሉም። የፓኪስታን ጠቅላይ ሚንስትር ''ማክሮን እስልምናን እያጠቁ ነው'' ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረው ነበር።

እንደ ኩዌት፣ ኳታር እና ጆርዳን ባሉ አገራት የፈረንሳይ ምርቶች ከመደብር መደርደሪያዎች ላይ ተነስተዋል። የቱርኩ ፕሬዝደንት “ማክሮን የሚባለው ግለሰብ ከእስልምና እና ሙስሊም ጋር ያለው ችግር ምንድነው?” ማለታቸውን ተከትሎ በቱርክ የፈረንሳይ አምባሳደር ወደ ፓሪስ መጠራታቸውን ተዘግቧል።

ይህ የኤርዶጋን አስተያየት በፈረንሳይ እና ቱርክ መካከል ያሉ ልዩነቶች እየሰፉ ስለመምጣታቸው አንዱ ማሳያ ነው ተብሏል። ሁለቱም የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል አገራት ይሁኑ እንጂ የማይሰማሙባቸው ጉዳዮች በርካታ ናቸው።

በሊቢያ እና ሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ሁለቱ አገራት በተቃራኒ ጎራ ተሰልፈው ይገኛሉ። በአርሜኒያ እና አዘርባጃን ግጭት ውስጥም የሁለቱ አገራት ፍላጎት የተለያየ ነው።