ማክሮን “የአዕምሮ ጤና ምርመራ” ያስፈልጋቸዋል ሲሉ የቱርኩ ኤርዶጋን ተናገሩ

የቱርክ ፕሬዝደንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኤማኑኤል ማክሮን "የአዕምሮ ጤና ምርመራ" ያስፈልጋቸዋል ማለታቸውን ተከትሎ ፈረንሳይ የቱርክ አምባሳደሯን ጠራች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኢማኔኤል ማክሮን እና ታይፕ ኤርዶጋን

የቱርክ ፕሬዝደንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኤማኑኤል ማክሮን “የአዕምሮ ጤና ምርመራ” ያስፈልጋቸዋል ማለታቸውን ተከትሎ ፈረንሳይ የቱርክ አምባሳደሯን ጠራች።

ኤርዶጋን የፈረንሳዩን ፕሬዝደንት የአዕምሮ ጤና ምርመራ ያስፈልጋቸዋል ያሉት ፕሬዝደንት ማክሮን ጽንፈኛ እስላማዊነትን ለመዋጋት ቃል መግባታቸውን ተከትሎ ነው።

ፈረንሳያዊው መምህር አወዛጋቢውን የነብዩ መሐመድን የካርቱን ምስሎች ክፍል ውስጥ ማሳየቱን ተከትሎ አንገቱ ተቀልቶ መገደሉን ተከትሎ ፕሬዝደንት ማክሮን በጉዳዩ ላይ ጠንከር ያለ አቋም እየንጸባረቁ ይገኛሉ።

የፈረንሳይ መንግሥት የአንድን ማህበረሰብ ወይም እምነት ተከታዮችን ስሜት ለመጠበቅ ሲባል የሰዎች የመናገር መብት ሊገደብ አይደባም የሚል ጠንካራ አቋም ይዟል።

ፈረንሳይ የሰዎች የመናገር መብትን መገደብ የፈረንሳይን አንድነት ጥያቄ ውስጥ ይጥላል የሚል አቋም አላት። ማክሮን ይህን የፈረንሳይ እሴትን ለመጠበቅ ዘመቻ ላይ ናቸው።

የቱርኩ ፕሬዝደንት በዚህ ላይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ፤ “ማክሮን የሚባለው ግለሰብ ከእስልምና እና ሙስሊም ጋር ያለው ችግር ምንድነው?” ሲሉ ጠይቀዋል።

“ማክሮን የአዕምሮ ጤና ሕክምና ያስፈልገዋል” ሲሉም ጨምረዋል። የቱርኩ ፕሬዝደንት ይህን ማለታቸውን ተከትሎ በቱርክ የፈረንሳይ አምባሳደር ለምክክር ወደ ፓሪስ መጠራታቸውን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል አንድ የፈረንሳይ ከፍተኛ ባለስልጣንን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

አምባሰደሩ ከማክሮን ጋር ተገናኝተው ይነጋገራሉ ተብሏል። እኚህ የፈረንሳይ ከፍተኛ ባለስልጣን “የፕሬዝደንት ኤርዶጋን አስተያየት ተቀባይነት የለውም” ስለማለታቸው ኤኤፍፒ ጨምሮ ዘግቧል።

ይህ የኤርዶጋን አስተያየት በፈረንሳይ እና ቱርክ መካከል ያሉ ልዩነቶች እየሰፉ ስለመምጣታቸው አንዱ ማሳያ ነው ተብሏል። ሁለቱም የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል አገራት ይሁኑ እንጂ የማይሰማሙባቸው ጉዳዮች በርካታ ናቸው።

በሊቢያ እና ሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ሁለቱ አገራት በተቃራኒ ጎራ ተሰልፈው ይገኛሉ። በአርሜኒያ እና አዘርባጃን ግጭት ውስጥም የሁለቱ አገራት ፍላጎት የተለያየ ነው።