በነቀምቴ ‘የአባ ቶርቤ’ አባላት ናቸው የተባሉ 4 ወጣቶች ተገደሉ

ነቀምቴ ከተማ

ከትናንት በስቲያ በኦሮሚያ ክልል ነቀምቴ ከተማ ‘የአባ ቶርቤ’ አባላት ናቸው የተባሉ አራት ወጣቶች ላይ የመንግሥት ጸጥታ ኃይል በወሰደው እርምጃ መገደላቸው ተገልጿል።

የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ “የጸጥታ ኃይሉ ከሕዝብ ጋር በመቀናጀት ባካሄደው ጠንካራ ኦፕሬሽን ከፍተኛ አደጋ ለማድረስ ሲዘጋጅ በነበረ የታጠቀ የሽፍታ ኃይል ላይ እርምጃ ወስዷል” ብሏል።

የክልሉ መንግሥት እንደሚለው አራቱ ወጣቶች በተከራዩበት የግለሰብ ቤት ውስጥ በቀጣይ ለሚፈጽሙት ጥቃት ዝግጅት እያደረጉ ሳሉ የጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ሊያውሏቸው ሲሉ ተኩስ በመክፈታቸው ተገድለዋል።

“እጅ አንሰጥም አሉ . . . በኃይል ሲተኩሱመረ ነበረ። ሽጉጥ እና ቦምብ ጨምሮ የተለያዩ መሳሪያዎች ነበሯቸው” ሲሉ የነቀምቴ ከተማ ልዩ ኃይል ኃላፊ ኮማንደር ግርማ አብዲሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል። በነበረው የተኩስ ልውውጥ በፖሊስ አባላት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩንም ተናግረዋል።

ከተገደሉት አራት ሰዎች መካከል ራጉኤል ኃይሉ በመባል የሚጠራው በነቀምቴ ከተማ አባ ቶርቤ የሚፈጽማቸውን ጥቃቶች በበላይነት ይመራ የነበረ ነው ሲል የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል።

ከአንድ ሳምንት በፊትም አባ ቶርቤ በመባል የሚታቀው ቡድን ሁለት የፖሊስ አዛዦችን መገደሉን ኮማንደር ግርማ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ኮማንደር ግርማ እርምጃ ከተወሰደባቸው የአባ ቶርቤ አባላት ላይ ሁለት ቦምብ፣ ሶስት ሸጉጦች፣ ድምጽ አልባ መሳሪያዎች እና የቀድሞ የአገር መከላከያ ሠራዊት አልባሳት ተገኝተውባቸዋል ሲሉ ለፋና ተናግረዋል።

አባ ቶርቤ አባላት ናቸው ከተባሉት ላይ ሁለት ቦምብ፣ ሶስት ሸጉጦች፣ ድምጽ አልባ መሳሪያዎች እና የቀድሞ የአገር መከላከያ ሠራዊት አልባሳት ተገኝተውባቸዋል ተብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Oromia Comm Bureau

የምስሉ መግለጫ, የአባ ቶርቤ አባላት ናቸው ከተባሉት ላይ ሁለት ቦምብ፣ ሶስት ሸጉጦች፣ ድምጽ አልባ መሳሪያዎች እና የቀድሞ የአገር መከላከያ ሠራዊት አልባሳት ተገኝተውባቸዋል ተብሏል።

ነዋሪዎች ምን ይላሉ?

ከሟቾቹ መካከል አንዱ ጓደኛው እንደሆነ የሚናገረው እና ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገው የነቀምቴ ከተማ ነዋሪ፤ የተገደሉት ወጣቶች እድሜያቸው በ23 እና 24 መካከል የሚገኝ ነው ይላል።

“በጣም ልጆች ናቸው። ሰው አክባሪ ናቸው። ተምረው የተመረቁም ይገኙበታል። ሕይወታቸው በአጭሩ ተቀጨ'' ይላል። ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ ደግሞ ወጣቶቹ የግለሰብ መኖሪያ ቤቱን የተከራዩት ከአንድ ሳምንት በፊት መሆኑን ይናገራሉ።

“ወጣቶቹን በአካል አውቃቸዋለሁ፤ እንደተባለው አይነት ሰዎች አይደሉም” የሚሉት እኚህ ነዋሪ፤ ወጣቶቹ ቤቱን የተከራዩት በ1000 ሺህ ብር መሆኑን ይናገራሉ። “5፡30 ላይ በአምስት ፓትሮል መኪና ከመጡ በኋላ ቤቱን ከበቡ” የሚሉት ነዋሪው የጸጥታ ኃይሉ እርምጃ ከወሰደ በኋላ ወጣቶቹ በተከራዩበት ግቢ ውስጥ አስክሬን ማየታቸውንም ይናገራሉ።

አባ ቶርቤ ማነው?

“አባ ቶርቤ” አፋን ኦሮሞ ቃል ሲሆን የአማርኛ ትርጉሙ “ባለ ሳምንት” ማለት ነው። ይህ ቡድን በምዕራብ ኦሮሚያ ታጥቆ ከሚንቀሳቀሰው አካል ጋር ግንኙነት እንዳለው የክልሉ ባለስልጣናት ይናገራሉ።

የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና ፀጥታ ኃላፊ አቶ ጅብሪል መሐመድ "አባ ቶርቤ ማለት የአሸባሪው ሸኔ የከተማው ክንፍ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር። ሸኔ በጫካ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ኃይል አለው።

በከተማ ደግሞ 'አባ ቶርቤ' እና 'ሶንሳ' ተብሎ የሚጠራ ቡድን አለው። እነዚህ ቡድኖች በተቻላቸው መጠን ግድያ በመፈጸም ሽብር ለመፍጠር የሚሞክሩ ናቸው ሲሉ ተናግረው ነበር። አቶ ጅብሪል መሐመድ እንደሚሉት የዚህ ቡድን አባላት ምንም አይነት የተለየ ስልጠናም ሆነ መሳሪያ የላቸውም።

የሚጠቀሙት ስልት፤ ማህበረሰቡን በመምሰል፤ ድንገት ነው አደጋ የሚያደርሱት። ለማምለጥ በሚያመቻቸው ቦታ በድንጋት አደጋ አድርሰው ይሰወራሉ" ብለው ነበር አቶ ጅብሪል።

የኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ አባ ቶርቤ የሚባለው ቡድን በነቀምቴ ከተማ በመንግሥት ባለስልጣናት፣ የጸጥታ ኃይል አባላት እና ንሑሃን ዜጎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲያደርስ መቆየቱን ገልጿል።

እስካሁንም ቡድኑ በነቀምቴ ከተማ ብቻ 35 ሰዎችን ገድሏል ይላል። በዚህ ሳምንት በሥራ ላይ የነበሩ ሁለት የፖሊስ አባላትንም መግደሉን የኮሚዩኒሸኬን ቢሮው አስታውቋል።