ስደት፡ ሕይወት ከአሰቃቂው የሳዑዲ አረቢያ እስር ቤት በኋላ

ከሳኡዲ ተመላሾች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የ39 ዓመቷ ዘውድነሽ በቀለ በ2013 ዋዜማ ከሳኡዲው የስደተኞች እስር ቤቶች ወደ ኢትዮጵያ ከሚመለሱ 147 ሴቶች እና ሕፃናት መካከል አንዷ መሆኗን ስታውቅ ደስታውን መቆጣጠር አልቻለችም ነበር። ይህን ያክል እደለኛ መሆኔንም አላመንኩም ነበር ትላለች።

ጥሪት ቋጥራ ባትሸጉጥም፤ እንደ ውጥኗ ድህነትን ድል ባትነሳም፤ ባዶ እጇን ቢሆንም ወደ አገር ቤት የመመለስ ጉዟዋ ደስታ እንዲፈጠርባት ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ቀዳሚው ያለፉትን ስድስት ወራት በሳዑዲ እስር ቤት ያሳለፈችበት ሰቆቃ ነው

"እግዚያብሄር የተመሰገነ ይሁን ለአገሬ በቅቻለሁ፤ ለልጆቼም በህይወት ገብቻለሁ" ትላለች ለቅሶ ባጀበው ድምፅ።

ከመቶ በላይ ሰዎች በአንድ ላይ በታጎሩበት የእስር ቤት ቆይታዋ "ብዙ የታመሙ አሉ፤ ብዙ ያበዱ አሉ። የአዕምሮ ጭንቀት [የገጠማቸው] አሉ። በሕገ-ወጥ መንገድ እየሄዱ፤ ሕገ-ወጥ ደላላ እየወሰዳቸው።"

ዘውድነሽ ከሰባት ዓመት በፊት ሕጋዊ በሆነ መንገድ ነበር ሕይወቷን ልታቀና ወደ ሳዑዲ አረቢያ ያቀናችው።

ቆይታዋ ግን ቀድማ እንደተመኘችው፤ ተስፋም እንዳደረገችው አልጋ በአልጋ አልሆነላትም። ከመነሻው የቋንቋ ማነቆ ነበረባት፤ የቤት ሠራተኛነት ከምታገለግላት ቀጣሪዋ ጋር መስማማት አልቻለችም፤ በደልንም ማሰተናገደን ያወቀችው ገና ከማለዳው ነበር።

የሥራ ፈቃዷ ካለቀም በኋላ እዚያው የቆየችው ዘውድነሽ ከሥራ ሥራ ተዟዙራቸለች፤ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሳለች፤ በየመንገዷም እንግልትን ቀምሳለች።

"ሕፃን ልጅ ዳልዬ ላይ በጩቤ ሁሉ ወግቶኛል" ትላለች። "በቃ በሽተኛ ሆኛለሁ።"

ባለፈው ዓመት አጋማሽ ገደማ ግን የባሰው ዱብ ዕዳ ተከሰተ። በርካታ ኢትዮጵያዊያን ስደተኛ ሠራተኞች ተጋርተው የሚኖሩበት ቤት በሳዑዲ የፀጥታ ኃይሎች ተከበበ።

"ገላዬን ታጥቤ በፒጃማ ነበር ያለሁት። ልብስ መቀየሪያ እንኳን ሳልይዝ አፋፍሰው ወሰዱን።"

ዘውድነሽ በሳዑዲ ፖሊስ ከተያዘች በኋላ የተወሰደችው በሰብአዊ መብቶች ጥሰት እና በአያያዝ ጉድለት ወደሚታወቀው እስር ቤት ነበር።

መገናኛ ብዙሃን እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዘውድነሽ የነበረችበት እስር ቤት ውስጥ የሚፈጸሙ በደሎችን አጋልጠው ነበር። በእነዚህ እስር ቤቶቹ ውስጥ ድብደባ ይፈፀማል፤ ታሳሪዎች በሰንሰለት ይታሰራሉ፤ ከመጠን በላይ ይተፋፈጋሉ የሚሉ ወቀሳዎች በመገናኛ ብዙሃን እና የሰበዓዊ መብት ተሟጋቾች ቀርቦ ነበር።

የሳኡዲ መንግስት ትችቶቹን ተከትሎ ጉዳዩን እየመረመርኩ ነው ማለቱ ይታወሳል።

ዘውድነሽ (ቀኝ) እና ጓደኛዋ ዝናሽ
የምስሉ መግለጫ, ዘውድነሽ (ቀኝ) እና ጓደኛዋ ገነት

ዘውድነሽ የነበረችበት እስር ቤት አስከፊ እንደነበር ትጠቅሳለች። ከመጠን ባላይ ከመታጨቅም በላይ፤ ለታማሚዎች የሚደረግ በቂ የህክምና አገልግሎት አልነበረም ትላለች። ከእንክብካቤ ንፈገቱ የተነሳም በእስር ቤቱ ውስጥ የሞተች ስደተኛ እንደነበረች ታወሳለች።

ስለዚህም አዲስ አበባ የሚመልሳት አውሮፕላን ውስጥ ስትገባ ደስታዋ ወደር አልነበረውም።

አዲስ አበባ ከደረሰች በኋላም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለአስራ አንድ ቀናት ያክል በአንድ የዩኒቨርስቲ ካምፓስ ውስጥ እራሷን ለይታ እንድትቆይ ተደርጋ ነበር።

ከለይቶ ማቆያው ስትወጣ የመጓጓዣ ወጭ 250 ብር ተሰጥቷት ወደ መኖሪያ ተጉዛለች።

ይህ ከሆነ ከአንድ ወር በኋላ ዘውድነሽ የድጋፍ ያለህ ትላለች።

ሥራ ማግኘት አልቻለችም። ህይወቷን ዳግም ለመገንባትም በአዲስ አበባ ምስራቃዊ ጫፍ በሚገኘው የእናቷ ቤት ውስጥ ኑሮን ጀምራለች። ከአካባቢዋ ወረዳ ድጋፍ እንደሚደረግላት ቃል ተገብቶላት ጥሪ እንድትጠብቅ ተነግሯታል። ጥሪው ግን እስካሁን አልመጣም።

የባንክ ደብተር ቁጥሯን እንድትሰጥም እንዲሁ ተነግሯት እርሱን ሰጥቻለሁ ትላለች።

ለተመላሽ ስደተኞች የሚደረገው የማቋቋሚያ ድጋፍ ፍፁማዊ ነው ባይባልም ባለፉት ዓመታት መሻሻል ታይቶበታል የሚሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድዔታ ፅዮን ተክሉ ናቸው።

"ስለ ሳኡዲ አረቢያ ካወራን [እ.ኤ.አ] ከግንቦት 2017 ጀመሮ እስከ መጋቢት 2020 ድረስ ወደአራት መቶ ሺህ ኢትዮጵያዊያንን መልሰናል" ይላሉ ሚኒስትር ድኤታዋ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ።

"እነዚህ በሙሉ ነፍስ ወከፍ ግለሰቦች ናቸው ብለህ ከጠየቅከኝ አይደሉም ነው የምለው፤ ምክንያቱም ከመካከላቸው አስር ጊዜ አስራ አምስት ጊዜ የተጓዘ ሰው ታገኛለህ። ስለዚህ ማድረግ የምትችለው ጉዞዎቹን መቁጠር ነው።"

ይህን የድግግሞሽ ጉዞ ለማስቀረት ስነ ህይወታዊ መረጃ መሰብሰብ መጀመራቸውን ይገልፃሉ።

ተመላሽ ስደተኞቹ አዲስ አበባ በሚደርሱበት ወቅት መጠነኛ የስነ ልቦና ህክምና እንደሚደረግላቸው የሚናገሩት ሚኒስትር ድኤታዋ፤ "ከዚያ በኋላ ከክልል ቢሮዎች ጋር እንሰራለን" ይላሉ።

ከጤና ሚኒስቴር፣ ከሰላም ሚኒስቴር እና ከሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም መንግሥት በዚህ ክንውን አጋር ከሚላቸው ከአፍሪካ ኅብረት፣ ከአውሮፓ ኅብረት እና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በመሆን ተመላሾቹን መልሶ ወደማኅበረሰብ ለመቀላቀል እንዲሁም ሕይወታቸውን ዳግም እንዲገነቡ ለማድረግ እንሠራለን ሲሉ ያስረዳሉ።

"መሻሻል ታይቷል? አዎ። ሥራውን እንከን አልባ ፍፁም ነው? አይደለም። [ተመላሾቹን] ወደማኅበረሰብ በመቀላቀል ጉዳይ የበለጠ መስራት አለብን" ይላሉ ፅዮን።

በርካቶቹ ተመላሾች በሳዑዲ አረቢያ ካጋጠማቸው ሰቆቃ አሻራ ጋር እንደሚኖሩ ከሚያስረዱት ተመላሾች መካከል ገነት ታከለ አንዷ ናት።

ገነት ለአስራ ዓመታትን ያህል በሳዑዲ አረብያ ቆይታለች። የመጨረሻዎቹን ሦስት ወራት አሰቃቂ ነበር ባለችው እስር ላይ ነው ያሳለፈችው። እንደ ዘውድነሽ ሁሉ እርሷም የጳጉሜ 2012 ተመላሾች መካከል አንዷ ናት።

በእስር ቤት ከተዋወቀቻት ዘውድነሽ ጋር አሁን የቀረበ ወዳጅነትን መስርታለች።

በእስር ቆይታዋም በሽታ እንዳጋጠማት ትናገራለች። "እግሬን መሽመቀቅ [ጀምሮኛል]። ጊዜው ደግሞ የብርድ ሰዓት ነው" ትላለች። በተመለሰች ከአንድ ወር በኋላ ለቢቢሲ በሰጠችው ቃለ መጠይቅ። "የሚለበስ ደግም ምንም የለም። እዚያ [ገብተው] ጥለውት የሄዱት ካለ እንጅ። አንድ ብርድ ልብስ ነበር፤ ስሚንቶ ላይ ነው የምንተኛው።"

በእስር ቤቱ ውስጥ ወደአስር አካባቢ ክፍሎች እንደነበሩ የምታስታውሰው ገነት፤ አንደኛው ክፍል ውስጥ ብቻ ከስድሳ በላይ ሕፃናት ነበሩ ትላለች። "አኔ የነበርኩበት ክፍል ውስጥ አስራ ሁለት ልጆች አሉ።"

ከተመለሰች በኋላ ወደህክምና መስጫ ስፍራ አዘውትራ ማቅናቷን የምትናገረው ገነት፤ ሻል እያላት ቢመጣም ጨርሶ አለመዳኗንም ጨምራ ትገልፃለች።

እንደ ዘውድነሽ ሁሉ ገነት ከኮሮናቫይረስ ለይቶ ማቆያ ስትወጣ ለመጓጓዣ የሚሆን ነው ተብሎ ጥቂት መቶ ብሮች እንደተሰጣት ለቢቢሲ ትናግራለች። ከዚያ በኋላ ግን የድጋፍ ቃል ኪዳን ካልሆነ በስተቀር በተጨባጭ ያገኘችው ነገር ያለመኖሩን ታስረዳለች።

እርሷ እና መሰል ተመላሾች ምናልባትም ቀደም ብለው ሳኡዲ አረቢያ እያሉ እየላኩ ያስቀመጡት ገንዘብ ወይንም ጥሪት ከሌላቸው በስተቀር ህይወትን ከዜሮ መጀመር ግድ እንደሚላቸው ነው የምትገልፀው ገነት።

እርሷም ሆነች ገነት ዳግም ወደመካከለኛው ምስራቅ የመጓዝ ኃሳብ ጨርሶም የለንም ይላሉ፤ ነገር ግን የገንዘብም ሆነ የሙያ ስልጠና አሊያም በአንዳች መልኩ እንዲደራጁ የሚደረግበትን መፍትሄ ይናፍቃሉ።

መጪው ጊዜ ምን ይዞ እንደሚመጣ እርግጠኞች አይደሉም፤ ቢያንስ ለአሁኑ ግን ከወዳጅ ቤተሰብ ጋር የመገናኘትን እንደሁም የደህንነታቸው መጠበቅን ትሩፋት እያጣጣሙ ይገኛሉ።