የፓኪስታኑ መሪ ፌስቡክ እስልምናን የሚያጥላሉ ይዘቶችን እንዲያግድ ጠየቁ

ጠቅላይ ሚንስትር ኢምራክ ከሀን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚንስትር ኢምራክ ከሀን

የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚንስትር ኢምራክ ከሀን እስልምናን የሚያጥላሉ ይዘቶች ከፌስቡክ እንዲታገዱ ለፌስቡክ ኃላፊ ማርክ ዙከርበርግ ደብዳቤ ጻፉ።

"እየተባባሰ የመጣው የእስልምና ጥላቻ፤ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ ጽንፈኝነት እና ግጭትን እያባባሰ ነው" ብለዋል በደብዳቤው።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ትላንት የፈረንሳይ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን "እስልምናን እያጥላሉ ነው" ብለው መተቸታቸው ይታወሳል።

ፌስቡክ የጥላቻ ንግግርን ከገጹ የማንሳት መርህ አለው። ፌስቡክ በጥላቻ ንግግር የሚመድበው ዘር፣ ብሔር፣ ዜግነት፣ ሃይማኖትን መሠረት አድርጎ ሰዎችን ማጥላላት ወይም ጎጂ መድልዎ ማድረግን ነው።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባወጡት ደብዳቤ፤ የሆሎካስት እልቂት እንደተከሰተ የማያምኑ ወይም መረጃውን የሚያዛቡ ጽሑፎች ከፌስቡክ እንዲነሱ በቅርቡ መወሰኑን አጣቅሰው፤ ሙስሊም ጠል የሆኑ ጽሑፎችም እንዲታገዱ ጠይቀዋል።

"ሙስሊሞች በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ እየተዋረዱ፣ ጥቃት እየደረሰባቸውም ነው። ሆሎካስትን በተመለከተ ያወጣችሁትን እገዳ እስልምናን በሚያጥላሉ ጽሑፎች ላይም እንድትተገብሩ እጠይቃለሁ" ብለዋል።

አያይዘውም "ማንኛውም የጥላቻ ንግግር መታገድ አለበት" ሲሉ በደብዳቤው ገልጸዋል።

ኢማኑኤል ማክሮን፤ የነብዩ መሐመድን የካርቱን ሥዕል ለተማሪዎቹ በማሳየቱ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለው ፈረንሳያዊ የታሪክ መምህር "የተገደለው ኢስላሚስቶች ነጋችንን መቀማት ስለሚፈልጉ ነው" ብለዋል።

ንግግራቸውን ተከትሎ እየተተቹ ነው። ከተቺዎቻቸው አንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ኢምራን ናቸው።

"ማክሮን ጥቃቱን ያደረሱ ሽብርተኞችን ሳይሆን እስልምናን መተቸታቸው ያሳዝናል" ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትሩ ትዊት አድርገዋል።

በሌላ በኩል በመካከለኛውም ምሥራቅ አገራት አንዳንድ መደብሮች የፈረንሳይ ምርቶችን ከመደርደሪያ ማንሳት ጀምረዋል።

የነብዩ መሐመድን እንዲሁም የአላህን ምስል ማሳየት በእስልምና የተከለከለ ነው።

ፈረንሳይ ከሃይማኖት ጣልቃ ገብነት ነጻ የሆነች አገር እንደሆነች ትገልጻለች። የአንድ ማኅበረሰብን ስሜት ላለመጉዳት በመጠንቀቅ ውስጥ የንግግር ነጻነት መገደብ የለበትም የሚል አቋም ታንጸባርቃለች።

የፈረንሳይ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ባወጣው መግለጫ "ምርቶች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የተደረገው ጥሪ መሠረተ ቢስ ነው። ይህ ጥሪና በጥቂት አክራሪዎች የሚጫሩ አገሪቱ ላይ የሚቃጡ ጥቃቶች መገታት አለባቸው" ብሏል።

ፓኪስታን የፌስቡክ ጽሑፎችን በተመለከተ ለድርጅቱ ቅሬታ ስታቀርብ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

እአአ 2017 ላይ የቀድሞው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር "አግባብ ያልሆኑ" ያሏቸውን ጽሑፎች ፌስቡክ እንዲመረምር ጠይቀው ነበር።

ጽሑፉ ነብዩ መሐመድን ወይም ቁርዓንን የሚያጥላላ እንደሆነ ይታመናል።