እስራኤል 'ለአዲሷ ወዳጇ' ሱዳን ስንዴ ልትልክ ነው

እስራኤል ለሱዳን ስንዴ ልትልክ መሆኑ ተነገረ። ይህን ያለው የጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ጽህፈት ቤት ነው።
የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽህፈት ቤት በትዊተር ገጹ ላይ 5 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ስንዴ "ለአዲሷ ወዳጃችን" ሱደን እንልካለን ብሏል።
ሱዳን ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል ዝግጅት ላይ ትገኛለች።
አሜሪካ፣ ሱዳን እና እስራኤል በጋራ ባወጡት መግለጫ መሠረት፤ የሁለቱ አገራት መሪዎች በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ ተገናኝተው የሰላም ስምምነታቸውን በፊርማቸው ያጸድቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ ጨምሮም ለሱዳን ፖለቲካዊ ሽግግር ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁሟል።
ከዚህ ቀደም በዋሽንግተን ዲሲ በተከናወነ ስነ ስርዓት ላይ ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ እና ባህሬን ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግነኙነት ለመፈጠር መስማማታቸው ይታወሳል።
አፍሪካዊቷ አገር ሱዳን ከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት አጋጥሟታል።
ሱዳን ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት ለመድረስ ከተስማማች በኋላ የፕሬዝደንት ትራምፕ አስተዳደር ሱዳንን ሽብርን ከሚደግፉ አገራት ዝርዝር ማስወጣቱ ይታወሳል።
ሱዳን ከዝርዝሩ የምትወጣው ከእስራኤል ጋር ግነኙነቷን ስታድስ እና በሽብር ጥቃት ቤተሰቦቻቸውን ላጡ አሜሪካውያን ካሳ ስትከፍል ነው የሚሉ ቅድመ ሁኔታዎች ተቀምጠው እንደነበረ ይነገራል።
በቅርቡም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሱዳን በሽብር ጥቃት ቤተሰቦቻቸውን ላጡ አሜሪካውያን 335 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ከከፈለች ሽብርን ከሚደግፉ አገራት ዝርዝር ውስጥ እንደምትሰረዝ ተናግረው ነበር።
ሱዳን የቀድሞ መሪዋ ኦማር አል-በሽር በህዝብ አብዮት ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ፖለቲካዊ ለውጥ ውስጥ ትገኛለች።














