ፖፕ ፍራንሲስ ለተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ጥምረት ድጋፍ አሳይተዋል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች "ጥምረት እንዲመሰርቱ" ሊፈቀድላቸው ይገባል ብለዋል።
ፖፑ ይህንን አስተያየት የሰጡት በህይወታቸው ዙሪያ በሚያተኩረረው አንድ ጥናታዊ ፊልም ላይ ነው።
በተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትም ላይ ግልፅ ያለ አስተያየት የሰጡበት እንደሆነም አስተያየት ሰጭዎች ይናገራሉ።
"የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ቤተሰብ የመሆን መብት አላቸውም" ሲሉ ረቡዕ ዕለት በተመረቀው ፊልም ተሰምተዋል።
"እነሱም የአምላክ ልጆች ናቸው እናም ቤተሰብ የመመስረት መብት አላቸው። ማንኛውም ሰው ቢሆን በዚህ ምክንያት ስቃይ ሊቀበልም አያስፈልግም፤ ሊጣሉም አይገባም" ብለዋል።
አክለውም " የሚጣመሩበት ህግ ሊኖር ይገባል። በዚህም ሁኔታ ህጋዊ ሽፋንም ያገኛሉ" ብለዋል።
በቦነስ አይረስ ኤጲስ ቆጶስ በነበሩበትም ወቅት ይህንን አቋም ይደግፉ እንደነበርና ምንም እንኳን በህግ የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ መፈቀዱን ቢቃወሙም ጥምረታቸው ህጋዊ ሽፋን እንዲኖረው እንደሚደግፉ አስረድተዋል።
ፍራንቼስኮ የተሰኘው ፊልም በፖፕ ፍራንሲስ ህይወትና ስራ ዙሪያ የሚያጠነጥን ሲሆን የሮም ፌስቲቫል አካልም ሆኖ ተመርቋል።
ፖፑ የተመሳሳይ ፆታ ጥምረትን በተመለከተ ከሰጡት ድጋፍ በተጨማሪ ሁለት የተመሳሳይ ፆታ ጥንዶችና ሶስት ልጆቻቸው በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲሳተፉ ሲያበረታቱም ይታያሉ።
የፖፕ ፍራንሲስን የህይወት ታሪክ ፀሃፊ ኦስተን ኢቨረይግ የፖፑ አስተያየት እንዳለስደነቀው ለቢቢሲ ተናግሯል።
"በቦነስ አይረስ ኤጲስ ቆጶስ እያሉ አቋማቸው ይሄ ነበር። የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻን ቢቃወሙም የተመሳሳይ ፆታ ጥምረት ድጋፍ እንዲደረግና ጥምረታቸውም ህጋዊ ሽፋን እንዲኖረው ቤተ ክርስትያናቸው ድምጿን ልታሰማ እንደሚገባ እምነት አላቸው" ብሏል።
በካቶሊክ እምነት አስተምህሮትና ህግ መሰረት የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት "ነውረኛና አግባብ የሌለው ባህርይም" ስለሆነም ትቃወማለች።
በጎሮጎሳውያኑ 2003 የቫቲካን ህግ እንዳሰፈረውና ለካቶሊክ እምነት ቀናኢ የሆኑትም ሊከተሉት የሚገባው ብሎ የደነገገው "ለተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ክብር አይገባም ምክንያቱም ይህም የነሱን ተግባራት ከመፍቀድ ጋር እንዲሁም ህጋዊ እውቅና ወደ መስጠት ስለሚያሸጋግግር ነው" ይላል።












