የጀርመን ቄሶች ሕፃናት ላይ የፈፀሙት በደል ይፋ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጀርመን ሮማን ካቶሊክ ቤተክርስትያን ቀሳውስት ከፈረንጆቹ 1946-2014 ባለው ጊዜ 3600 ገደማ ሕፃናት ላይ ፈፅመውታል የተባለው ጭቆና ይፋ ሆኗል።
ጥናቱን ያካሄደው የጀርመን ሮማን ካቶሊክ ቤተክርስትያን ኦፊሴላዊ ውጤቱን መስከረም 25 ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
ዘገባው እንደሚጠቁመው 1670 ገደማ የቤተክርስቲያኒቱ ሰዎች 3677 ሕፃናት ላይ ፆታዊ ጥቃት አድርሰዋል።
የቤተክርስትያኒቱ ቃል አቀባይ የሆኑ ግለሰብ በውጤት 'እጅግ ማፈራቸውን እና ጭንቀት ውስጥ መግባታቸውን' ተናግረዋል።
ጥናቱ 'ግፍ ፈፃሚ ቀሳውስት አሏት' እየተባለች ለምትታማው የሮማን ካቶሊክ ቤተክርስትያን ሌላ መዘዝ ይዞ ብቅ ብሏል።
ከጥቃት አድራሽ ቀሳውስት መካከል 38 በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው ቅጣት የተጣለባቸው የሚል ዘገባም ብቅ ብሏል፤ ከስድስት አንድ ብቻ ናቸው ለፍርድ የሚቀርቡት።
ጥቃት ከደረሰባቸው ሕፃናት መካከል በርካቶቹ ወንዶች እንደሆኑ ሲነገር ዕድሜያቸው ደግሞ ከ13 ዓመት በታች ነው ተብሏል።
ጥናቱን ያካሄዱት ሦስት የጀርመን ዩኒቨርሲቲዎች ሲሆኑ 38 ሺህ ያህል መዝገቦች አገላብጠዋል፤ በርካታ መዝገቦች እንደተደመሰሰ ቢጠረጠርም።
የቤተክርስቲያኒቱ ቃል አቀባይ የሆኑት ቢሾፕ ስቴፋን አከርማን «የጥናቱ ዓላማ በቤትክርስትያናችን እየተፈፀመ ያለውን ግፍ ማስቆም ነው» ብለዋል።
የሮማን ካቶሊክ ቤ/ክ ዋና መቀመጫ የሆነችው ቫቲካን ስለጉዳዩ እስካሁን ምንም ባትልም ሊቃ ጳጳሳት ፖፕ ፍራንሲስ ግን ስለጉዳዩ ለመምከር ለወርሃ የካቲት ቀጠሮ መያዛቸው እየተነገረ ነው።












