ፍትህ፡ የጎልያድና የዳዊት ፍልሚያ ነው የተባለለት የፍርድ ቤት ክርክር

ፓርቲና አሰሪዋ ሊየው ሙን ሊዮንግ

የፎቶው ባለመብት, Parti Liyani/Getty

የምስሉ መግለጫ, ፓርቲና አሰሪዋ ሊየው ሙን ሊዮንግ

ኢንዶኔዥያዊት የቤት ሠራተኛ ናት፤ ለተሻለ ኑሮም ቀዬዋን ለቃ ኑሮዋን በሲንጋፖር አደረገች።

በናጠጡ የሲንጋፖር ቱጃር ቤተሰቦች ተቀጥራም ትሰራ ነበር። በየወሩም ስድስት መቶ ዶላር (23 ሺህ ብር ገደማ) ይከፈላታል።

አሰሪዋ በአገሪቱ ውስጥ አሉ የሚባሉ ሃብታም ሲሆን፤ የተለያዩ ኩባንያዎችን መስራች፣ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅም ናቸው።

ዕቃ ሲጠፋ የቤት ሠራተኞችን መወንጀል በብዙ ቦታዎች እንደሚያጋጥመው ሁሉ የዚህ ግለሰብ ቤተሰብም እቃዎችን "ሰርቀሻል፣ ዘርፈሽናል" አሏት።

ዘርፈሽናል ብለው ብቻ አልቀሩም፤ ፓሊስ ደውለው ጠሩ። የፍርድ ሂደቱም ባልታሰበ ሁኔታ የሚዲያዎችንም ሆነ የሕዝቡን ቀልብ የገዛና ታሪካዊ መሆን ችሏል።

ፓርቲ ሊያኒ ውድ የእጅ ቦርሳዎችን፣ የዲቪዲ ማጫወቻን በመስረቅ የተወነጀለች ሲሆን ከዓመታት ተስፋ አስቆራጭ የፍርድ ቤት ውጣ ውረድ በኋላ በዚህ ወር ነው ነፃ የወጣችው።

"በመጨረሻም ነፃ በመሆኔ ተደስቻለሁ" በማለት በአስተርጓሚዎቿ አማካኝነት ለሪፖርተሮች ተናግራለች።

"ለአራት ዓመትም ያህል እየታገልኩ ነበር" ብላለች።

ሆኖም የፍርድ ሂደቱ በርካታ የፍትህ ጥያቄዎችን አስነስቷል። በተለያየ የኑሮ ደረጃ ያሉ ሰዎች በሲንጋፖር የፍትህ ሂደት ምን ያህል በእኩል ደረጃ እንደማይታዩም ያሳየ ነው ተብሏል።

በተለይም ጥፋተኛ ሆና መገኘቷ የሥርዓቱን መበስበስ ያሳየ ነው በማለትም ተችተውታል።

ፓርቲ ሊያኒ በአሰሪዋ የተቀጠረችው በጎሮጎሳውያኑ 2007 ነበር። አሰሪዋ ሊየው ሙን ሊዮንግና በርካታ የቤተሰቦቹ አባላት የሚኖሩት በአንድ ቤት ውስጥ ይኖሩ ነው፤ ልጁ ካርልም ከቤተሰቡ ጋር በዚሁ ቤት ይኖር ነበር።

የሥራ ድርሻዋም እነዚህን ሁሉ ሰዎች መንከባከብና ለእነሱ ምግብ ማብሰል፣ ልብስ ማጠብ፣ ማፅዳትና እንዲሁም ሌሎች ኃላፊነቶች ነበሩባት።

በ2016 ልጅየው ካርል ሊየው ከባለቤቱና ከልጆቹ ጋር ሆኖ ከአባቱ ቤት ወጥቶ ሌላ ቤት ይኖር ጀመረ።

ልጅየው ሌላ ቤት መኖር ሲጀምርም የእሷ የሥራ ድርሻ ባይሆንም የልጁን ቤትም ሆነ ቢሮውን እንድታፀዳ በተደጋጋሚ ትጠየቅ እንደነበረ ለፍርድ ቤት የቀረበው ማስረጃ ያስረዳል።

ይህ ሁኔታ የአገሪቱን የአሰሪና ሠራተኛ ህግ የጣሰ ሲሆን እሷም በተደጋጋሚ ቅሬታዋን አቅርባለች። ከጥቂት ወራት በኋላም የአሰሪዋ ቤተሰቦች ሰርቀሻል በሚል ውንጀላ ከሥራ አባረሯት።

ልጅየው ካርል ሊው ከሥራ መባረሯን ሲነግራትም "ለምን እንደተባረርኩ አውቃለሁ፤ ሽንት ቤትህን አላፀዳም በማለቴ ነው" ብላው ነበር።

ያላትን ጓዝ ጠቅልላ እንድትወጣም የተሰጣት ሁለት ሰዓት ነበር። ሆኖም እቃሽን ወደ አገርሽ እንልክልሻለን አሏት። እሷም በዚያኑ ቀን ወደ ኢንዶኔዥያ ተመለሰች።

ሆኖም እቃዋን እያስተካከለች እያለም ለሲንጋፖር ባለስልጣናት ያልተዋወለችበትን የልጁን ቤት አጽጂ መባሏን በመጥቀስ እከሳለሁ አለች።

ፓርቲም ከቤት ከወጣች በኋላ የጠቀለለችውን ጓዝ ሲያዩ የእሷ ያልሆነና የሰረቀችው ዕቃ እንዳገኙ ለፖሊስ ሪፖርት አደረጉ።

ፓርቲ ስለዚህ ጉዳይ የምታውቀውም አልነበረም። ከአምስት ሳምንታት ቆይታ በኋላ ሌላ ሥራ ፈልጋ ወደ ሲንጋፖር ተመልሳ ስትመጣ በቁጥጥር ስር ዋለች።

የፍርድ ሂደቷም ተጓተተ፤ በነበረባት የወንጀል የፍርድ ሂደት ምክንያት መስራት ስላልቻለች በስደተኛ ሠራተኞች መጠለያ ውስጥም ለመቆየት ተገደደች። ኑሯዋንም ለማሸነፍ የእነሱን ድጋፍ ማግኘት ነበረባት።

ሰረቀች የተባለችው ምንድን ነው?

ፓርቲ አሰሪዎቿ ሰረቀች ብለው የሚወነጅሏት 115 ልብሶች፣ ውድ ቦርሳዎች፣ የዲቪዲ ማጫወቻና ጌራልድ ጌንታ የተሰኘ ስያሜ ያለው ሰዓት ነው። የእነዚህ እቃዎች ዋጋም ሲገመት 34 ሺህ ዶላር (1.3 ሚሊዮን ብር) የሚያወጣ ነው አሉ።

በፍርድ ሂደቱም ወቅት የእሷ መከራከሪያ የነበረው አንዳንዶቹ እቃዎች እነሱ እንደሚሉት የተሰረቁ ሳይሆኑ ተጥለው የተገኙ፣ የራሷ እቃዎችና እሷ ከቤታቸው ከተሰናበተች በኋላ ሻንጣዎቿ ውስጥ ሆን ተብለው የተከተቱ ናቸው ትላለች።

ሆኖም በ2019 የአንድ ግዛት ዳኛ ጥፋተኛ መሆኗን የበየኑባት ሲሆን ሁለት ዓመት ከሁለት ወርም እንድትታሰር ወሰኑባት። ሆኖም ፓርቲም ዝም አላለችም ይግባኝ ጠየቀች።

ጉዳዩ እየተጓተተ ወደ ሲንጋፖር ከፍተኛ ፍርድ ቤት የደረሰ ሲሆን በመጨረሻም ባለንበት የመስከረም ወር ነው ፍርድ ቤቱ በነፃ እንድትሰናበት ወሰነ።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ቻን ሴንግ ኦን እንዳሉት ከአሰሪዎቿ ክስ ጀርባ ድብቅ ሴራ እንዳለ ጠቅሰው፤ ከዚያም በተጨማሪ በጉዳዩ ላይ የተሳተፉ ፖሊሶች፣ ዐቃቤ ሕግና የግዛቲቷ ዳኛም ላይ ጣታቸውን ጠቁመዋል።

አሰሪዎቿ ለፖሊስ ሪፖርት ያደረጉት የአሰሪና የሠራተኛ ሕግን በመጣስ የቤት ሠራተኛቸው የልጃቸው ካርል ቤት እንድትሰራ ማዘዛቸውን በመጥቀስ እንዳትከሳቸው ለማድረግ ነበር ብለዋል ዳኛው።

ፓርቲ ሰርቃለች ተብሎ በአሰሪዎቿ የቀረቡት ቁሶች ማለትም ሰዓቱም ሆነ ሁለት ስልኮች ከጥቅም ውጪ የሆኑና የማይሰሩ ናቸው ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ አሰሪዎቿ አይሰራም ብለው የወረወሩት የዲቪዲ ማጫወቻን ሰርቀሻልም ተብላ እንደ ማስረጃ ቀርቦባታል።

የዲቪዲ ማጫወቻ

የፎቶው ባለመብት, HOME

በኋላ ላይ ዐቃቤ ሕግ የዲቪዲ ማጫወቻው እንደማይሰራ ያውቁ እንደነበር ቢገልፅም፤ በፍርድ ሂደቱ ግን እንደ አንድ ማስረጃ ሆኖ ቀርቦ ነበር።

ይህም ሁኔታ የፍርድ ሂደቱን ያዛባ ነው በሚል ዳኛ ቻን ተችተውታል።

ከዚህም በተጨማሪ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ሆኖ የቀረበው የባለሐብቱ ልጅ ካርል ያቀረባቸው ማስረጃዎችም ታማኝነት በዳኛው ዘንድ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።

ፓርቲ ሰረቀቻቸው የተባሉ በርካታ የሴት ልብሶች የነበሩ ሲሆን የማን እንደሆኑ በተጠየቀበት ጊዜ ካርል "የእኔ ናቸው" ብሏል።

በፍርድ ሂደቱም ወቅት አንዳንዶቹን ማስታወስ ካለመቻሉ በተጨማሪ "የሴት ልብሶች ለምን ኖሩት?" ለሚለው ጥያቄ "እንደ ሴት መልበስ እንደሚወድ" ቢናገርም ዳኛ ቻን "የሚታመን" ሆኖ አላገኙትም።

ፖሊስ በበኩሉ ወንጀሉ ተፈፅሞበታል የተባለውን ቤት ያየው ሪፖርት ከተደረገ ከአምስት ሳምንታት በኋላም መሆኑ ጥያቄን በዳኛው በኩል አጭሯል።

ፓርቲ የምትናገረው ቋንቋ አንደኛው የኢንዶኔዥያ ቢሆንም ፖሊስ በፍርድ ሂደቱ ወቅት አስተርጓሚ አላቀረበላትም። እሷ የማትናገረውን ማሌይ የተባለውን ቋንቋ አስተርጓሚ ነው የቀረበላት።

"ፖሊስ ምርመራውን ያካሄደበት መንገድ በጣም የሚያሳዝንና አሳሳቢ " በማለት በሲንጋፖር ማኔጅመንት ዩኒቨርስቲ የሕግ ፕሮፌሰር የሆኑት ኡጅን ታን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"የግዛቲቱ ዳኛም ቢሆኑ ቀድመው ነው ውሳኔ ላይ የደረሱት። ፖሊስም ሆነ ዐቃቤ ሕግ የፈፀሟቸውን ስህተቶች ማየት አልቻሉም" ይላሉ።

የዳዊትና ጎልያድ ትግል

የበርካቶችን ቀልብ መግዛት የቻለው ይህ የፍርድ ሂደት በቱጃሩና በቤተሰቦቹም ላይ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።

ምን ያህል ሃብታሞች ከሕግ በላይ እንደሆኑና ደሃዎችና መጠጊያ የሌላቸውን ቢያሰቃዩና ቢበድሉም የሚደርስባቸው ነገር እንደሌለ ማሳያ ነው፤ ይህንንም አሳዛኝ እውነታ ያጋለጠ ነው ተብሏል።

ምንም እንኳን መጨረሻ ላይም ቢሆን ፓርቲ ፍትህ ብታገኝም በአጠቃላይ ሥርዓቱ ላይ ጥያቄ አስነስቷል።

"በቅርብም እንዲህ አይነት የፍርድ ሂደት አስታውሳለሁኝ" የሚሉት ፕሮፌሰሩ "በብዙዎች ጭንቅላት ይመላለስ የነበረውም በእሷ ቦታ እኔ ብሆንስ? ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ምርመራው ይካሄድ ይሆን? የተዛባ ዳኝነት ያጋጥመኝ ይሆን የሚለው ነው።"

አሰሪዎቿ ፖሊስንና ፍርድ ቤቱን ሐሰተኛ በሆነ ክስ መቆጣጠር ችለዋል፤ ይህም የአገሪቱ አጠቃላይ የፍትህ ሥርዓት ላይ ጥያቄ አስነስቷልም ተብሏል።

ይህ ሊዋጥላቸው ያልቻለው ሲንጋፖራውያን ቁጣ ተከትሎ ሊየው ሙን ሊዮንግና ሥራ አስኪያጅ ከሆኑባቸው በርካታ ኩባንያዎች ራሳቸውን በጡረታ እንደሚያገሉ አስታውቀዋል።

የከፍተኛ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ እንደሚያከብሩና በሲንጋፖር የፍትህ ሥርዓትም እምነት እንዳላቸው ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ሆኖም የቤት ሠራተኛቸውን ለፖሊስ ሪፖርት በማድረጋቸው ግን ምንም እንደማይፀፀት አሳውቀዋል። "ከልቤ የማምነው ነገር ቢኖር ወንጀል ተፈፅሟል ብለን የምንጠራጠር ከሆነ ለፖሊስ ማሳወቅ የዜግነት ግዴታችን ነው" ብለዋል።

ልጅየው ካርል በበኩሉ በሁኔታው ላይ ዝምታን የመረጠ ሲሆን፤ ምንም አይነትም መግለጫ ከመስጠትም ተቆጥቧል።

ፓርቲና ጠበቃዋ አኒል ባልቻንዳኒ

የፎቶው ባለመብት, Home/Grace Baey

የምስሉ መግለጫ, ፓርቲና ጠበቃዋ አኒል ባልቻንዳኒ

ይሄ ጉዳይም የፓርቲ ብቻ ሆኖ አልቀረም የፖሊስና ዐቃቤ ሕግ ምርመራቸውን የሚያካሂዱበት ሁኔታ መገምገም አለበት ተብሏል።

የሕግና የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ኬ ሻንሙጋም ቢሆኑ በፍርድ ሂደቱ ስህተት እንደተፈፀመ አምነው መንግሥት በቀጣይነት የሚያደርገውንም በጥብቅ እንከታተላለን ብለዋል።

ገንዘብና ስልጣን ምን ያህል የተቆራኘ መሆኑንና ሃብታም ሰዎችም ሕግን እንደፈለጉ ማሽከርከር ይችላሉ የሚለውን እሳቤ ከማጉላቱም በተጨማሪ ስደተኛ ሠራተኞች ፍትህን ለማግኘት ያለባቸውን ፈተና አጋልጧል ተብሏል።

ፓርቲ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ድጋፍ በሲንጋፖር ቆይታ ወንጀለኛ አይደለሁም በሚል ተከራክራለች። ጠበቃው አኒል ባልቻንዳኒም 150 ሺህ ዶላር የሚያስከፍለውን የጥብቅና አገልግሎቱን በነፃ ሰጥቷታል።

"ጠበቃዋ ከመንግሥት ጋር ተናንቆ ነው የታገለላት፤ የዳዊትና የጎልያድ ትግልም ይመስላል፤ በመጨረሻም ዳዊት አሸነፈ" ይላሉ ፕሮፌሰር ታን።

ፓርቲ በበኩሏ በአሁኑ ወቅት ወደ ትውልድ አገሯ ለመመለስ ዝግጁ ናት።

"ችግሮቼ ሁሉ ተቀርፈዋል እናም ወደ ኢንዶኔዥያ መመለስ እፈልጋለሁ" በማለት ለአንድ ሚዲያ የተናገረችው ፓርቲ "አሰሪዎቼን ይቅርታ አድርጌላቸዋለሁ። በሌሎች ሠራተኞች ላይ እንዳይደግሙት ብቻ መንገር እፈልጋለሁ" ብላለች።