ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ፡ 'ማህበረሰብን እንደ መሀይም መቁጠር የለብንም ይሉ ነበር'

ዶክተር ቦጋለች ገብሬ ከህፃናት ጋር

የፎቶው ባለመብት, KMG WEBSITE

በልጅነታቸው በግርዛት ምክንያት ከፍተኛ ስቃይ ደርሶባቸዋል። ሦስት ጊዜ ያህል ከተደረገባቸው የጠለፋ ሙከራ አምልጠዋል። ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቱ በእርሳቸው ላይ ብቻ ሳይሆን በእህቶቻቸውም ላይ ደርሶ ሁለቱን እህቶቻቸውን በግርዛት ምክንያት በሞት አጥተዋል።

መከራቸው ይህ ብቻም አልነበረም "ሴት ልጅ አትማርም" በሚለው የአገሬው ልማድ የትምህርት ዕድል ማግኘት አልቻሉም ነበር። በወቅቱም አባታቸው ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ ሲከለክሉ እናታቸው ደብቀው ትምህርት ቤት ይልኳቸው ነበር።

ትምህርት ቤት ለመሄድ በጠዋት ይነሱና ውሃ ለመቅዳት ወንዝ ይወርዳሉ። ከዚያም የቀዱትን ውሃ ሳር ውስጥ ደብቀው ለመማር ክፍል ውስጥ ይቀመጣሉ።

አጎታቸው በመጠኑም ቢሆን ያሉባቸውን ኃላፊነቶች ይጋሯቸው ነበር። በኋላም በሚስጢር የያዙት ትምህርት ተጋለጠ - ማንበብ መቻላቸው ታውቆ ጉድ ተባለ።

በወቅቱ በአካባቢው ከአራተኛ ክፍል በላይ የተማሩ ብቸኛዋ ሴት እንደነበሩም ይነገራል - ዶክተር ቦጋለች ገብሬ፤ በብዙዎቹ አጠራር 'ቦጌ'።

በእናታቸው ድጋፍ በድብቅ የጀመሩት ትምህርት አሜሪካ ድረስ ወስዷቸዋል። በእስራኤል አገር በሂብሪው ዩኒቨርሲቲ ሙሉ የትምህርት ዕድል አግኝተው 'ማይክሮ ባዮሎጂ' እና 'ፊዚዮሎጂ' አጥንተዋል። ከዚያም በአሜሪካ አገር በማሳቹሴትስ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲም በ'ኢፒዲሚዎሎጂ' ሦስተኛ ድግሪያቸውን አግኝተዋል።

በ1989 ዓ.ም ወደ አገራቸው በመመለስ በእርሳቸው ላይ ሲደርስ የነበረው በደል በሌሎች ላይ እንዳይደርስ ለመሞገት ከምባታ ጠንባሮ ዞን የተጀመረውን እና 'ከምባቲ ሜንቲ ጌዝማ' [ኬ ኤም ጂ] ወይንም የከምባታ ሴቶች ራስ አገዝ በመባል የሚታወቀውን አገር በቀል ድርጅት መስርተዋል።

ድርጅቱ በአካባቢው በሺህዎች የሚቆጠሩ ሴቶችን ከግርዛት እንደታደገ ይነገራል። "ያልተገረዘች ሴት ባል አታገኝም" የሚለውን የአካባቢውን የቆየ ልማድ ታግሎ፤ የነበረውን የግርዛት ሽፋን 3 በመቶ እንዲወርድ ያደረገ ታላቅ ተግባር ማከናዎናቸውን ብዙዎች ይናገሩታል።

እኝህ በኢትዮጵያ የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱት የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና ተመራማሪ ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ተሰምቷል።

በአሜሪካን አገር በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ከትናንት በስቲያ ሌሊት ሕይወታቸው ማለፉ ታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ እና ዶክተር ቦጋለች ገብሬ

የፎቶው ባለመብት, Facebook

ሕልፈታቸው ለብዙዎች ዱብዳ ነበር። ሕመም ሳይጠናባቸው ሥራ ላይ እያሉ ነበር ወደ አሜሪካ አገር የሄዱት በመሆኑም ሕልፈታቸውን ሲሰማ ማመን እንዳልቻለ የድርጅቱ ሠራተኛ የሆነው አቶ በላይ አድማሱ ይናገራል።

አቶ በላይ፤ ዶ/ር ቦጋለች በጎጂ ልማዳዊ ድርጊት እና በሴቶች አቅም ማጎልበት ላይ እንደሚሠሩ ያወቀው ገና ተማሪ ሳለ ነበር - በተለያዩ መድረኮች ላይ ተሞክሯቸውን ሲያካፍሉ።

"በአካባቢው ቀዳሚ የትምህርት እድል ያገኙ ሴት እንደነበሩ ልምዳቸውን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ያካፍሉ ነበር" ይላል።

በአካባቢው ያለው ባህል ሴቶች ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ስለሚያውቁ በሴቶች ደህንነትና መብት ላይ የሚሠሩት በሙሉ አቅማቸው ነበር።

"'ማህበረሰብ መሀይም አይደለም፤ ዕውቀት አለው። ከእነሱ የምንማረው ብዙ ነገር አለ። እነሱን አንደ አላዋቂ መቁጠር የለብንም' የሚለው አቋማቸው ያስገርመኛል" ይላል።

በዚህም ምክንያት ከማህበረሰቡ ጋር ጠጋ ብሎ መወያየት እንደሚያስፈልግ እና ማህበረሰቡ የራሱን ችግር መፍታት እንዳለበት ያላቸው እምነት ከእርሱ ጋር የቀረው ሃሳባቸው ነው።

በፖፕሌሽን ሚዲያ ሴንተር የኢትዮጵያ ተወካይ የነበሩት ዶክተር ንጉሴ ተፈራም ከዶ/ር ቦጋለች ጋር የሥራ ትውውቅ ነበራቸው።

እርሳቸውም ዶ/ር ቦጋለች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ በተደረገው ጥረት ውስጥ የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ እንደነበር ይመሰክራሉ።

ከእርሳቸው ጋር በአገር ውስጥ ብቻም ሳይሆን ከአገር ውጭ በተደረጉ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ላይ የመገናኘት ዕድል የነበራቸው ዶ/ር ንጉሴ፤ በአሜሪካ 'ውመን ደሊቨር' ባዘጋጀው ስብሰባም ላይ ሽልማት ሲበረከትላቸው በሥፍራው እንደነበሩ ያስታውሳሉ። ይህ ብቻም ሳይሆን ለጊዜው በውል አያስታውሱት እንጂ ሌሎች ሽልማቶችም እንደተበረከተላቸው ይናገራሉ።

"ጎጂ ልማዳዊ ድርጊትን ለማስወገድ በተደረገው ጥረት ሁሉ ማንን ማንሳት እንችላለን? ሲባል በመጀመሪያው መስመር መምጣት ያለባት ዶክተር ቦጋለች ትመስለኛለች" ይላሉ።

ዶ/ር ንጉሴ እንደሚሉት ዶ/ር ቦጋለች የጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ነገር ያንገበግባቸዋል። ሲናገሩም ሆነ ሲፅፉ ልባቸው የሚጨነቅበት፣ እልህ ውስጥ የሚገቡበት ሙሉ በሙሉ የተሰጡበት ነበር።

ጥረታቸውም በለሆሳስ ሳይሆን ለመልካም ነገር እልኸኛ ነበሩ።

"ልቧ ውስጥ የሚነድ እሳት፣ በጣም ቁጭትና ሀዘን ያለባት፣ የበለጠ ለመሥራት ብዙ የምታስብ እንደነበር አውቃለሁ፤ ለሁላችንም ጥሩ ምሳሌ የሆነች ሴት ነበረች" ይላሉ።

ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች 70/80 በመቶ ሕፃናትን እና ሴቶችን ነው በአገራችን የሚያጠቃው የሚሉት ዶ/ር ንጉሴ፤ ይህንን ለመግታት ላደረጉት አስተዋፅኦ ሥራቸው ራሱ እንደሚመሰክር ይገልጻሉ።

"የሴቶች መብት በተሻለ መልኩ የሚከበርበት አገር ኖራ፤ የትምህርት እድል አግኝታ ከፍ ባለችበት ሰዓት በሕዝቡ ላይ ተስፋ ሳትቆርጥ መምጣቷ በጣም ይገርመኛል፤ የጥንካሬ ምልክት ናት" የምትለው ደግሞ የሕግ ባለሙያዋ ህሊና ብርሃኑ ናት።

ለሴቶች መብት እንደሚቆረቆር ሰው በጣም ብዙ ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች አሉ የምትለው ህሊና፤ ብዙ ጊዜ በተሻለ ማህበረሰብ ውስጥ መኖር ሲጀመር ወደታች መመልከት የተለመደ አለመሆኑን በመግለፅ ዶ/ር ቦጋለች ግን ይህንን ልማድ የሰበሩ ሴት እንደሆኑ ትናገራለች።

"ወደ ኢትዮጵያ ከመጣች በኋላም የአንድ ሰው ሳይሆን፤ የሺህ ሰው ጥንካሬ ነው ይዛ የመጣችው" ትላለች።

ህሊና እንደምትለው ጥንካሬያቸው፣ መሥራት የሚፈልጉትን በትክክል አስቀምጠው መምጣታቸው ለእርሷም ሆነ ለሌሎች መልካም ነገር መሥራት ለሚፈልጉት ተምሳሌት ናቸው።

"እምቢታ፣ መጋፈጥ የተለመደም አይደለም፤ ህብረተሰቡን ያስደነግጣል፤ ያንን ሁሉ ጥሳ ማህበረሰቡን ለመለወጥ መሞከሯ በጣም ጥንካሬዋን ያሳየናል" ስትል ታስታውሳቸዋለች።

"በመልካም ነገር ፅንፍ [ራዲካል] ሃሳብ ሲኖር፣ የማህበረሰቡን ልማድ ላለመቀበል ወደ ታች የሚጎትትሽን ነገር እንዳታይ ምሳሌ ናት" በማለት ታክላለች።

ህሊና እንደምትለው በጠለፋ ማግባት እስከ 2005 ድረስ በሕግ የተከለከለ አልነበረም። ግርዛት፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻ በማህበረሰባዊ ደረጃ እንደ መጥፎ ባህል ብቻ ሳይሆን ኢ- ሰብዓዊ ድርጊትም እንደሆነ በሕግም እንደሚያስጠይቅ አይወራም። ብዙ ጊዜ ጎጂ ባህል በሚል ተሸፋፍኖ ነበር የሚነገረው። ዶ/ር ቦጋለች ግን ጎጂ ልማድ በሚለው ሸፋፍነው አላስቀመጡትም፤ ይልቁኑ ሕገ-ወጥነት ብለው ነበር የተጋፈጡት።

ዶ/ር ቦጋለች በዚህ በጎ ተግባራቸው በአፍሪካ በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በመከላከል በአውሮፓዊያኑ 2007 የተበረከተላቸውን 'ላሪሳ' ሽልማት ጨምሮ በዓለም አቀፍና በአገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ሽልማቶችንም አግኝተዋል።

ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ በ2008 ዓ.ም የዓመቱ በጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚም ነበሩ።

የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው በተወለዱበት ከምባታ ጠንባሮ ዞን ለማድረግ የድርጅቱ ቦርድ አባላት ከዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ጋር በመሆን እየተነጋገሩ እንዳሉ በዚያው ዞን የኬ ኤም ጂ ሠራተኛ የሆኑት አቶ በላይ አድማሱ ገልፀውልናል።