ቡሪንዲ፡ ፕሬዝደንት ላይ ድንጋይ ወርወረዋል የተባሉ በ30 ዓመት እሥራት ተቀጡ

ተመራጩ ፕሬዝዳንት ኤቬሪስት ንዳይሺሜዬ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሰሜናዊ ቡሩንዲ የሚገኝ አንድ ፍርድ ቤት አዲሱ የሃገሪቱ ፕሬዝደንት ኤቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ ያሉበት መኪና ላይ ድንጋይ በመወርወር የመግደል ሙከራ አድርገዋል ያላቸውን ሁለት ወንዶችና አንዲት ሴት በ30 ዓመታት እሥራት እንዲቀጡ ወሰነ።

ምንም እንኳ አቃቤ ሕግ ሰዎቹ የፕሬዝደንቱን ደህንነት አደጋ ላይ በመጣላቸው ሰባት ዓመታት መታሠር አለባቸው የሚል የቅጣት አስተያየት ቢሰጥም ፍርድ ቤቱ ግን ፕሬዝደንቱን ለመግደል ሞክረዋል በሚል እያንዳንዳቸው በ30 ዓመት እሥራት ይቀጡ ሲል በይኗል።

ካያንዛ በምትባል ከተማ አንድ ነዳጅ ማደያ ውስጥ ይሰሩ የነበሩት ሶስቱ ግለሰቦች ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ፕሬዝደንቱን ከተማቸውን በጎበኙበት ወቅት ከሥራ ቦታቸው ሆነው የፕሬዝደንቱ መኪና ሲያልፍ ድንጋይ ወርውረዋል ተብለው ነው የተያዙት።

ሶስቱም ተከሳሾች ድርጊቱን አልፈፀምንም ሲሉ ይከራከራሉ።

«ከተፈጠረው ክስተት በኋላ በርካቶች ታሥረው ነበር። በርካቶች ከእሥር ቢለቀቁም ሁለቱ ወንዶችና አንዲት ሴት ሳይለቀቁ ቀሩ። ሰዎቹ እሁድ ዕለት እንደተፈረደባቸው ሰማን» ሲል አንድ የከተማዋ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ሟቹን ፕሬዝደንት ፒዬር ንኩሩንዚዛን በመተካት በቅርቡ ሥልጣን የጨበጡት የ52 ዓመቱ የቡሩንዲው ተመራጩ ፕሬዝዳንት ኤቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ በብዙዎች ዘንድ "ትሁት" እና "ሐይማኖተኛ" እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።

ወዳጃቸውና የትግል አጋራቸው ሟቹ ፕሬዝደናት ፒዬር ንኩሩንዚዛ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት ውስጥ በአገሪቱ ውስጥ "ከፍተኛ ተጽዕኖ" የነበራቸው ጄነራል ሆነው ቆይተዋል።

በብዛት 'ኔቫ' በመባል የሚታወቁት ሜጀር ጀነራል ንዳይሺሚዬ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1968 በማዕከላዊ ቡሩንዲ በምትገኘው የአገሪቱ የፖለቲካ ማዕከል ጊቴጋ ግዛት ውስጥ ነው የተወለዱት።

በዴሞክራሲያዊ ምርጫ አሸንፈው ወደ ስልጣን መጥተው የነበሩት የሚልቺየር ንዳዳዬ ግድያን ተከትሎ በአውሮፓውያኑ 1993 የእርስ በርስ ጦርነት ሲቀሰቀስ ኤቬሪስት ንዳይሺሜዬ በቡሩንዲ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የሕግ ተማሪ ነበሩ።

በወቅቱ ልክ እንደ ቀድሞው ፕሬዝዳንት ሁሉ እሳቸውም በዋና ከተማዋ ቡጁምቡራ ውስጥ በሁቱ ተማሪዎች ላይ ከተፈጸመው ግድያ ተረፈዋል።

ከዚህ በኋላም ሸሽተው ከአገራቸው በመውጣት በቱትሲዎች የሚመራውን መንግሥት ከሚፋለሙት አማጺያን ጋር ተቀላቀሉ።

ኤቬሪስት ንዳይሺሜዬ የቀድሞው መሪ ፒየር ንኩሩንዚዛ ወደስልጣን ከመምጣታቸው በፊት ደጋፊያቸው በመሆን ታንዛንያ ውስጥ በመንግሥትና በአማጺያኑ መካከል የሠላም ንግግር በሚደረግበት ጊዜ በቅርበት አብረዋቸው ይሰሩ ነበር። 

ተመራጩ ፕሬዝዳንት የስድስት ልጆች አባትና የሮማ ካቶሊክ ዕምነት ተከታይ ሲሆኑ ሟቹ ንኩሩንዚዛ ይከተሉት የነበረውና "እግዚአብሔርን ማጉላት" የሚሉትን የፖለቲካ አመለካከት እንደሚያራምዱ ይነገርላቸዋል።

አዲሱ ፕሬዝዳንት ንዳይሺሜዬ የሚመሯት ቡሩንዲ በዲፕሎማሲው መስክ የተገለለችና ከለጋሾች ጋር ያላት ግንኙነትም የሻከረ ነው።