'ኸርድ ኢሚዩኒቲ' ውጤታማ ላይሆን ይችላል ሲሉ ባለሙያዎች አስጠነቀቁ

ኸርድ ኢሚዩኒቲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ስፔናውያን ተመራማሪዎች 'ኸርድ ኢሚዩኒቲ' የተሰኘው መላ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት ላይሠራ ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

'ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች የተሳተፉበት ይህ ጥናት እንደሚጠቁመው 5 በመቶ ሰዎች ብቻ ናቸው የሰውነት የመከላከል አቅምን ማዳበር የቻሉት' ይላል ላንሴት የተሰኘው የሕክምና ጋዜጣ ያወጣው ዘገባ።

'ኸርድ ኢሚዩኒቲ' ማለት በርካታ ሰዎች በበሽታው እንዲያዙ በማድረግ በሽታን የመከላከል አቅም ማዳበር ነው ሲሉ ባለሙያዎች ይተነትናሉ።

የበሽታን የመሠራጨት መጠን ለመገደብ ቢያንስ ከ70 እስከ 90 በመቶ የሚሆን የሕብረተሰብ ክፍል በበሽታው መያዝ አለበት።

በሰውነት ውስጥ የሚገኘው የኮቪድ-19 የመከላከል አቅም ከቦታ ቦታ እንደሚለያይ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ። እንደ ስፔን ያሉ ሃገራት በዚህ ረገድ ዕድለኞች ናቸው ማለት ይቻላል።

የጥናቱ ቡድን አባላት ምንም እንኳ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በስፔን ከፍተኛ ጉዳት ቢያደርስም ቫይረሱ በሕብረተሰቡ ዘንድ ተሰራጭቶ የመቆየቱ ነገር እርግጥ አይደለም ይላሉ።

ከኸርድ ኢሚዩኒቲ ይልቅ አካላዊ መራራቅ፣ አዳዲስ ታማሚዎችን ለይቶ ማቆየት እና የሕክምና ክትትል ማድረግ የተሻሉ አማራጮች ናቸው ይላሉ አጥኚዎቹ።

ጥናቱ አውሮፓ ውስጥ 'ኸርድ ኢሚዩኒቲ' አስመልክቶ ከተሰሩ ጥናቶች መካከል በስፋትና ጥልቀት የሚደርሰው የለም ተብሏል።

ቻይና እና ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ጥናቶች ተሰርተው ነበር። ነገር ግን የነዚህ ጥናቶች ውጤት እንደሚጠቁመው ቫይረሱ በስፋት በተሰራጨባቸው አካባቢዎች እንኳ በርካቶች ተጋላጭነታቸው ዝቅ ያለ ነው።

ስፔን እስካሁን ድረስ ከሩብ ሚሊየን በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረስ እንተደያዙባት አረጋግጣለች። ከ28 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ሞተዋል። ነገር ግን ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የሟቾች ቁጥር በየቀኑ ከ10 በታች ሆኗል።

ቢሆንም ግን በቅርቡ በሰሜን ምዕራብ የምትገኘው ጋሊሲያ ከተማ ባለሥልጣናት ቫይረሱ እንደ አዲስ ማንሰራራቱን ተከትሎ የእንቅስቃሴ ገደብ ጥለዋል።

ባለሥልጣናቱ ቫይረሱ እንደ አዲስ ያገረሸው መጠጥና ምግብ ቤቶች በመከፈታቸው ምክንያት ነው ይላሉ።

ኮሮና
Banner