"ማንም ሰው ገዳዮቹን ይቅር የማለት መብት የለውም" የጋዜጠኛ ኻሾግጂ እጮኛ

የፎቶው ባለመብት, @mercan_resifi
በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለው ሳዑዲ አረቢያዊ ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ እጮኛ፤ ማንም ሰው ገዳዮቹን ይቅር የማለት መብት የለውም ስትል ይቅርታውን አወገዘች፡፡
እጮኛው ይህን የተናገረችው ልጁ ለአባቱ ገዳዮች ይቅርታ እንዳደረገ ከተናገረ በኋላ ነው፡፡
የሳዑዲ አረቢያን መንግሥት በመተቸት የሚታወቀው ኻሾግጂ በቱርክ ኢስታምቡል በሚገኘው የሳዑዲ ቆንስላ ውስጥ የተገደለው ከሁለት ዓመታት በፊት ነበር፡፡
የሳዑዲ ባለሥልጣናት አሟሟቱን በተመለከተ ከሃገሪቱ መንግሥት በመጣ ትዕዛዝ እንዳልሆነ ቢናገሩም በአለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ በደህንነት አካላትና በተባበሩት መንግሥታት ዘንድ አመኔታን አላገኙም።
ጀማል ኻሾግጂ ከመሞቱ በፊት ነዋሪነቱን አሜሪካ የነበረ ሲሆን ለዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ይፅፍ ነበር።
ጋዜጠኛው ቆንስላ ውስጥ ከገባ በኋላ መጥፋቱን ተከትሎ የሳዑዲ ባለሥልጣናት እርስ በርስ የሚጣረሱ መረጃዎች ይሰጡ ነበር፡፡ በመጨረሻም ወደ ሳዑዲ እንዲያመጣው የታዘዘው ቡድን ተልዕኮው ወዳልሆነ አቅጣጫ አምርቶ መገደሉን አምነዋል።
በጎርጎሳውያኑ ታህሳስ 2019 በጋዜጠኛው ግድያ እጃቸው አለበት የተባሉ አምስት ግለሰቦችን በሪያድ በተደረገ ሚስጥራዊ የፍርድ ሂደት ሞት ተፈርዶባቸዋል።
የተባባሩት መንግሥታት ልዩ ተወካይ አግነስ ካላማርድ የፍርድ ሂደቱን "የፍትህ ተቃራኒ" ሲሉ የጠሩት ሲሆን ነፃ ምርመራ መደረግም እንዳለበት አሳስበዋል።
እጮኛው ያለችው ምንድን ነው?
እጮኛው ሃቲስ ሴንጊዝ "ጀማል ኻሾግጂ ከሁላችንም በላቀ የሚደነቅና የሚወደድ ዓለም አቀፍ ምልክት ነበር" ስትል ዛሬ በትዊተር ገጿ ላይ አስፍራለች፡፡
ሴንጊዝ አክላም "ጀማል የጋብቻ ሥርዓታችንን ለመፈጸም የሚያስፈልጉ መረጃዎችን ለማምጣት በሄደበት የተገደለው በአገሩ ቆንስላ ውስጥ ነው፤ ገዳዮቹም እርሱን አድፍጠው ለመግደልና ለመደበቅ በበቂ ዝግጅት ከሳዑዲ የመጡ ነበሩ" ብላለች፡፡
በመሆኑም ይህንን ዘግናኝ ድርጊት የፈጸሙ ሰዎችን ማንም ሰው ይቅር የማለት መብት የለውም ስትል ተናግራለች፡፡ ፍትህ እስከሚያገኝ ድረስ እርሷ እና ሌሎች ዝም እንደማይሉም ገልጻለች ሴንጊዝ፡፡
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
የጀማል ኻሾግጂ ቤተሰቦች ያሉት ምን ነበር?
መግለጫው በጋዜጠኛው ልጅ ሳላህ ኻሾግጂ ትዊተር ገፅ ላይ በዛሬው ዕለት የወጣ ሲሆን፤ "በዚች በተቀደሰች የረመዳን ወር አምላክ ያለንን እናስታውሳለን። የሰው ልጅ ይቅር ካለና እርቅ ማውረድ ከቻለ ሽልማቱ የሚገኘው ከአላህ ነው" በማለት ኑሮውን በሳዑዲ አረቢያ ጂዳ ያደረገው ሳላህ ፅፏል።
"ስለዚህም የሰማዕቱ ጀማል ኻሾግጂ ቤተሰቦች አባታችንን የገደሉትን ይቅርታ አድርገንላቸዋል፤ ሽልማቱንም ከአምላካችን እናገኘዋለን" በማለት በትዊተር ገፁ አስፍሯል።
በእስልምና ሕግ መሰረት ቤተሰብ ይቅርታ ቢያደርግም የሞት ቅጣቱ ተፈፃሚ ይሆናል። በዚህ ሁኔታ ግን የሞት ቅጣቱ ተፈፃሚ ይሁን አይሁን የታወቀ ነገር የለም።
ከዚህ ቀደም ሳላህ ሳዑዲ በምታደርገው ምርመራ እንደሚተማመንና ድጋፉንም እንደሚቸር ገልጾ ነበር።
ከዚህ በተጨማሪም የአባቱን ሞት በመጠቀም የሃገሪቱን አመራር ሊያዳክሙ ይፈልጋሉ ያላቸውን "ተቃዋሚዎችና ጠላቶች" በማለትም ተችቷል።
የጀማል ኻሾግጂ ልጆች የአባታቸውን ሞት ተከትሎ ቤትና የወር ክፍያ በካሳነት እየተሰጣቸው እንደሆነ ባለፈው አመት ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል።
ከጋዜጠኛው ልጆች መካከልም የመጀመሪያ ልጁ ሳላህ ኻሾግጂ ብቻ ሳዑዲ አረቢያ መኖር መቀጠሉንም ጋዜጣው አስነብቧል።













