በኻሾግጂ ግድያ የአሜሪካ ዝምታ 'መፍትሄ አይሆንም'፡ የተባበሩት መንግሥታት

አልጋ ወራሽ ሞሃመድ ቢን ሰልማን (ቀኝ) እና ጀማል ኻሾግጂን (ግራ)

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, አልጋ ወራሽ ሞሃመድ ቢን ሰልማን (ቀኝ) ጀማል ኻሾግጂን (ግራ) የገደሉት ከእኔ ትዕዛዝ አልተቀበሉም ሲሉ ተናግረው ነበር።

ባለፈው ጥቅምት ላይ የተገደለው የሳዑዲ ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂን በተለመለከተ አሜሪካ እርምጃ መውሰድ ይኖርባታል ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ባለሙያ አስጠነቀቁ።

''ዝምታ መፍትሄ አይሆንም። ስለጉዳዩ በግልጽ መነገር አለበት። የእስካሁኑ በቂ አይደለም። እርምጃ መወሰድ አለበት'' ሲሉ በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አግነስ ካላማረድ ተናግራለች።

የጋዜጠኛውን አሟሟት ለማጣራት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ የመራችው ቡድን ኻሾግጂ ''ከሕግ አግባብ ውጪ በጭካኔ መገደሉን'' ደርሼበታለሁ ብሏል።

የሳዑዲ ዜግነት ያለው ዝነኛው ጋዜጠኛ ጀማል ካሾግጂ፤ ቱርክ ኢስታንቡል ወደሚገኘው የሳዑዲ ቆንጽላ ገብቶ ደብዛው ጠፍቶ ከቆየ በኋላ መገደሉ ተገልጿል።

የቱርክ ባለስልጣናት በሳዑዲ ሰዎች ስለመገደሉ መረጃዎች አሉን ይላሉ።

አግነስ፤ አሜሪካ በኤፍቢአይ አማካይነት ግድያውን በማስመልከት ምረመራ ማድረግ ይኖርባታል ያለች ሲሆን፤ ጨምራም አሜሪካ ከኻሾግጂ ግድያ ጋር በተያያዘ በሚስጥር የተያዙ መረጃዎችን ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ይኖርባታል ብላለች።

ከአግነስ ጋር መግለጫውን የሰጠችው የኻሾግጂ እጮኛ ''ምንም እንዳልተፈጠረ አድርጎ ማለፍ አይቻለም'' ያለች ሲሆን፤ የአውሮፓ አገራት ጉዳዩን በአጽንኦት እንዲመለከቱት ጠይቃለች።

ዃሾግጂ ኢስታንቡል የሳዑዲ ቆንስላ ውስጥ ሲገደል የዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ አምደኛ ነበር።

101 ገጽ የሚረዝመው የአግነስ ሪፖርት፤ በኻሾግጂ ግድያ የሳዑዲ አረቢያው አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማንን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሳዑዲ አመራሮች ቀጥተኛ ተሳትፎ እንደነበራቸው ''አሳማኝ መረጃዎች'' አሉ ይላል።

በወቅቱ ሳዑዲ በተደጋጋሚ ጀማል ኻሾግጂ ወደ ቆንስላው ከገባ ከደቂቃዎች በኋላ ቆንጽላውን ለቆ ወጥቷል ብላ ስትከራከር ብትቆይም፤ ዘግይታ ኻሾግጂ መገደሉን አምናለች።

ሳዑዲ ኻሾግጂ መገደሉን ከማመኗ በፊት፤ የአገሪቱ ጠቅላይ አቃቢ ሕግ በቆንጽላው ውስጥ በነበሩ ሰዎች እና በጀማል መካከል በተፈጠረ ጸብ ምክንያት ሊሞት ችሏል ብለው ነበር።

ጀማል ኻሾግጂ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጀማል ኻሾግጂ

ጀማል ኻሾጂ ማን ነበር?

ጀማል ኻሾግጂ በሳዑዲ ዝነኛ ጋዜጠኛ ነበር፤ የሶቪየት ሕብረት የአፍጋኒስታን ወረራን በዝርዝር ዘግቧል። እንደ ኦሳማ ቢን ላደን ከመሳሰሉ ግለሰቦች ጋር ቃለ መጠይቅ አድርጓል።

ለበርካታ አስርት ዓመታት ለሳዑዲ ንጉሳውያን ቤተሰብ የቅርብ ሰው ነበር፤ የሳዑዲ መንግሥት የመገናኛ ብዙሃን አማካሪ ሆኖም ሰርቷል።

ከሁለት ዓመታት በፊት ግን ከሳዑዲ መንግሥት ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ሃገር ጥሎ ወደ አሜሪካ ተሰደደ። አሜሪካም ሆኖ የዋሽንግተን ፖስት አምደኛ ሆነ። በጽሑፎቹ የሳዑዲ አረቢያውን ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማንን ይተች ነበር።

ጀማል ኻሾግጂ እንዴት ነበር የተገደለው?

ሳዑዲ፤ ጋዜጠኛ ጀማል ባሳለፍነው ወር በሳዑዲ ቆንጽላ ውስጥ መገደሉን ብታምንም ስለ አሟሟቱ እርስ በእርስ የሚጣረሱ መረጃዎችን ስትሰጥ ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት ኻሾግጂ በግፍ ነው የተገደለው ይላል።

ቱርክ በበኩሏ፤ ጀማል ኻሾግጂ ታንቆ እንደተገደለ እንዲሁም አስክሬኑ በኬሚካል እንዲቀልጥና እንዲተን መደረጉን እናምናለን ብላለች። ሳዑዲ አረቢያ የኬሚካል እና የቶክሲኮሎጂ ባለሙያዎችን ኢስታንቡል ወደሚገኘው ቆንጽላዋ መላክዋን የቱርክ ባለስልጣናት ይናገራሉ።

የሳዑዲ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ደግሞ ኻሾግጂ የተገደለው ሊያግባባው ወደ ኢስታንቡል ባቀናው ቡድን ነው ብሎ ነበር። ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ፤ ቡድኑ ኻሾግጂን ማግባባት ሲሳነው በኃይል ወደ ሳዑዲ እንዲያመጡት ትዕዛዝ ተቀብለው ወደ ቱርክ ማቅናታቸውን ተናግረዋል።

የኃይል አማራጭን ሲወሰድ፤ ኻሾግጂ መጠኑ ከፍ ያለ መድሃኒት በመወጋቱ ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል። አስክሬኑም የሳዑዲ ''ተባባሪ'' ለሆነ ሰው ቱርክ ውስጥ ተሰጥቷል ሲሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ተናግረዋል። ጨምረውም በግድያው አምስት ሰዎች ተጠያቂ መደረጋቸውንና ስለ ጉዳዩ አልጋ ወራሽ ሞሃመድ ቢን ሰልማን ምንም እንደማያውቁ ተናግረው ነበር።

በኢስታንቡል የሚገኘው የሳዑዲ ቆንጽላ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በኢስታንቡል የሚገኘው የሳዑዲ ቆንጽላ

ኻሾግጂ ወደ ሳዑዲ ቆንላ ለምን አቀና?

ጀማል ከቀድሞ ሚስቱ ጋር መፋታቱን የሚያረጋገጥ ሰነድ ለማግኘት፣ ከዚያም ቱርካዊት እጮኛውን ለማግባት በእለተ አርብ ሴብቴምበር 28 በቆንጽላው ተገኘ። በቆንጽላው ያሉ ሰዎች ግን ለማክሰኞ ኦክቶበር 2 ቀጠሩት።

''ቱርክ ውስጥ በሚገኝ የሳዑዲ ቆንጽላ ውስጥ ምንም ሊያደርጉኝ አይችሉም ብሎ ገምቶ ነበር'' ስትል እጮኛው ለዋሽንግተን ፖስት ጽፋለች።

''ጀማል ምንም እንደማይገጥመው እርግጠኛ ነበር''

ማክሰኞ ሴብቴምበር 2 ከቀጠሮ ሰዓት 15 ደቂቃ ቀደም ብሎ ወደ ቆንጽላው ሲገባ በተንቀሳቃሽ ምስል ይታያል።

ጀማል ወደ ቆንጽላው ከመግባቱ በፊት ለእጮኛው ሁለት ስልክ ቁጥሮች ሰጥቷት "ካልተመለስኩ ለቱርኩ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ታይር ኤርዶጋን አማካሪዎች ደውለሽ ንገሪያቸው" ብሏት ነበር።

እጮኛው ሳትታክት ለ10 ስዓታት በቆንጽላው በር ላይ ጠበቀችው። በነጋታውም ወደ ቆንጽላው ሄዳ ጠበቀችው። ጀማል ግን የውሃ ሽታ ሆኖ ቀረ።

በጀማል ግድያ እጃቸው አለበት የተባሉት የሳዑዲ የጸጥታ ኃይል አባላት እነማን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በጀማል ግድያ እጃቸው አለበት የተባሉት የሳዑዲ የጸጥታ ኃይል አባላት

በጀማል ግድያ እጃቸው አለበት የተባሉት የሳዑዲ የጸጥታ ኃይል አባላት እነማን ናቸው?

15 አባላት ያሉት ቡድን ጀማል ደብዛ የጠፋ ዕለት ከሳዑዲ አረቢያ ተነስቶ ኢስታንቡል ቱርክ በግል አውሮፕላን መግባቱን ቱርክ ይፋ አድርጋ ነበር።

ከ15ቱ ሰዎች መካከል ማህር ሙትሬብ የተባለው ግለሰብ ሎንደን በሚገኘው የሳዑዲ ኤምባሲ የጸጥታና ደህንነት አባል መሆኑን ቢቢሲ አረጋግጧል።

አራት ግለሰቦች ደግሞ ከልዑል አልጋ ወራሹ ሞሐመድ ቢን ሰልማን ጋር ቅርርብ አላቸው።

የቱርክ መገናኛ ብዙሃን እንደሚሉት ከሆነ፤ 15ቱ ግለሰቦች አጥንት መቁረጫ መጋዝ ጭምር ይዘው ነው የሄዱት።

ከግለሰቦቹም መካከል አንዱ የሬሳ ምርመራ ባለሙያ ነው።