ትራምፕ በካሾግጂ ግድያ ምክንያት ውግዘት ከደረሰባት ሳዑዲ ጎን ቆመዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሳዑዲ አረቢያ ከጀማል ካሾግጂ ግድያ ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ ውግዘት ቢደርስባትም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሃገሪቱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሳዑዲ ተባባሪ እና ከየትኛውም ሃገር በላይ በአሜሪካ መዋለ ንዋይዋን ያፈሰሰች ናት ሲሉ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም የሳዑዲው አልጋ ወራሽ ልዑል ሞሃመድ ቢን ሳልማን በቅርቡ ህይወቱ ስላለፈው ካሾግጂ አሟሟት የማወቃቸው ዕድል ከፍተኛ ነው ብለዋል።
"ሆኖም ግን የእኛ ግንኙነት ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
የሳዑዲ ዜግነት ያለው ጋዜጠኛ ጀማል ካሾግጂ ቱርክ ኢስታንቡል ወደ ሚገኘው የሳዑዲ ቆንስላ ገብቶ ህይወቱ ማለፉ ከተረጋገጠ ሳምንታት አልፈዋል።
ሳዑዲ በቆንስላው ሠራተኞች ተገቢ ያልሆነ አያያዝ ጋዜጠኛው ህይወቱ ማለፉን በመግለጽ አልጋ ወራሹ ስለግድያው ያውቁ ነበር የሚለውን ዘገባ አጣጥለዋል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሲ አይ ኤ ግድያውን ሞሃመድ ቢን ሳልማን ማዘዛቸውን ያምናል ሲሉ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው "አልጋ ወራሹ ስለግድያው ሊያውቁም ላያውቁም ይችላሉ" ብለዋል።
ሲ አይ ኤም ቢሆን ስለግድያው "100%" እርግጥኛ አይደለም ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
ባለፈው እሑድ ከቱርክ የቀረበላቸውንና ጋዜጠኛውን አገዳደል ያመላክታል ተባለለትን ድምጽ ለመስማት ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን አስታውቀዋል።












