ኮቢ ብራያንት ሕይወቱን ያጣበት ሄሊኮፕተር አደጋ የምርመራ ውጤት ይፋ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ታዋቂው አሜሪካዊ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ኮቢ ብራያንትና ታዳጊ ሴት ልጁን ጨምሮ 9 ሰዎች አሳፍሮ የተከሰከሰው ሄሊኮፕተር አደጋ ሪፖርት ይፋ ሆኗል።
ሪፖርቱ ዘጠኙም ተሳፋሪዎች ለሞት የበቁት ሰውነታቸው ላይ በደረሰ ከባድ ግጭት ሳቢያ ነው ብሏል።
180 ገፆች ያሉት ይህ ሪፖርት የሄሊኮፕተሯ አብራሪ የ50 ዓመቱ አራ ዞባያን አደንዛዥ ዕፅም ሆነ የአልኮም መጠጥ አልወሰደም ሲል ደምድሟል።
ባለፈው ጥር በአሜሪካዋ የካሊፎርኒያ ግዛት የተከሰተው የሄሊኮፕተር አደጋ መንስዔ ምን እንደሆነ አሁንም እየተጣራ ነው። አነስተኛዋ ሄሊኮፕተር ስትከሰከስ የአየር ሁኔታው ደመና እንደነበር ይታወሳል።
ታዋቂው የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ብራያንትና የ13 ዓመት ልጁ ጂያና ከዘጠኙ ተሳፋሪዎች መካከል ነበሩ። ከእነሱ በተጨማሪ ሁለት የጂያና እኩያ ሴት ቅርጫት ኳስ ተጫዋቾች፣ ቤተሰቦቻቸውና አሠልጣኛቸው ሄሊኮፕተሯ ውስጥ ነበሩ።
ተሳፋሪዎቹ ለታዳጊ ሴቶች የቅርጫት ኳስ ፍልሚያ ነበር ታውዘንድ ኦክስ ወደ ተሰኘው ሥፍራ ሲያቀኑ የነበረው። ዘጠኙንም ሰዎች ያሳፈረችው ሄሊኮፕተር በሰሜናዊ ሎስ አንጀለስ የሚገኝ ተራራ ላይ የተከሰከሰችው።
ሪፖርቱ የሁሉም ሟቾች የሞት ምክንያት አደጋ ነው ሲል ደምድሟል። የድህረ-አደጋ ምርመራው በከተማዋ ጤና ጉዳዮች ድረ-ገፅ ላይ በይፋ ተሰቅሏል።
አምስት ጊዜ የአሜሪማካ ቅርጫት ኳስ ሻምፒዮን መሆን የቻለው ኮቢ ብራያንት ዕድሜውን ሙሉ ኤልኤ ሌከርስ ለተበላው ቡድን ነው የተጫወተው። በአሜሪካ ቅርጫት ኳስ ማሕበር [ኤንቢኤ] ታሪክ ከታላላቅ ተጫዋቾች መካከል የሚመደብ ነው።
ለ20 ዓመታት ቅርጫት ኳስ የተጫወተው ኮቢ በፈረንጆቹ ሚያዝያ 2016 ነበር ቅርጫቱን የሰቀለው።
የኮቢ ብራያንት ባለቤት ቫኔሳ ብራያንት ጠበቆች የሄሊኮፕተር አብራሪውን ድርጅት ከሰዋል። ክሱ፤ አብራሪው ለበረራ ከመነሳቱ በፊት የአየር ሁኔታውን አላጣራም ይላል።
የሎስ አንጀለስ ከተማ ፖሊስ መርማሪዎች በአደጋው ሥፍራ ተገኝተው እጅግ አሰቃቂ ፎቶዎች ማንሳታቸውን አምነው ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ፎቶዎቹን ከማሕህሮቻቸው እንዲያጠፉ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል።













