ታዋቂው አሜሪካዊ ስፖርተኛ ከነልጁ በሄሊኮፕተር አደጋ ሞተ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሜሪካዊው የቅርጫት ኳስ ኮከብ ኮቢ ብራያንት ከሴት ልጁ ጋር ካሊፎርኒያ ግዛት ውስጥ ሲጓዝበት የነበረው ሄሊኮፕተር ተከስክሶ ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር ህይወቱ አለፈ።
የ41 ዓመቱ ብራያንትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ላይ አደጋው የደረሰው ሲጓዙበት የነበረው የግል ሄሊኮፕተር ከተከሰከሰ በኋላ በእሳት ተያይዞ ነው።
የሎስ አንጀለስ ፖሊስ እንዳስታወቀው ከአደጋ በህይወት የተረፈ ሰው የለም።
ብራያንት ለታዋቂው ሎስ አንጀለስ ሌከርስ የቅርጫት ኳስ ቡድን በመጫወት አምስት ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን በመቻሉ በውድድሩ ታሪክ ውስጥም ታላላቅ ከሚባሉ ተጫዋቾች መካከል የሚጠቀስ ስፖርተኛ ነበር።
በርካቶች በብራያንት ድንገተኛ ሞት ድንጋጤያቸውን እየገለጹ ሲሆን ታዋቂ ግለሰቦችን ሃዘናቸውን እየገለጹ ነው።
የስፖርተኛው ሞት እንደተነገረም በመላው አሜሪካ በሚካሄዱ የቅርጫት ኳስ ውድድሮች ላይ ለብርያንት የህሊና ጸሎት ተደርጎለታል።
የአሜሪካ የቅርጫት ኳስ ውድድር የበላይ አካል የሆነው ኤንቢኤ የብራያንትን ሞት ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ማህበሩ በስፖርተኛውና በ13 ዓመት ታዳጊ ልጁ ሞት የተሰማውን ሃዘን ገልጿል።
መግለጫው "ላለፉት 20 የውድድር ወቅቶች ኮቤ ተሰጥኦንና ለስፖርቱ ያለውን ሁሉ በማድረግ አሸናፊ መሆን እንደሚቻል አሳይቷል" ሲል ብራያንትን አስታውሶታል።
ብራያንት ለ20 ዓመታት በዘለቀው የቅርጫት ኳስ ህይወቱ የተጫወተው ሎስ አንጀለስ ሌከርስ ለተባለው ቡድን ብቻ የነበረ ሲሆን ከአራት ዓመት በፊት መጫወት አቁሟል።
በተለያዩ ጊዜያት በቅርጫት ኳስ ውድድር ባሳየው ችሎታው የኮከብነት ሽልማቶችን ያገኘ ሲሆን ሁለት ጊዜ በኦሊምፒክ ላይ ተሳትፎ የአሸናፊነትን ክብር ተጋርቷል።
ብራያንት ከሁለት ዓመት በፊት 'ዲር ባስኬትቦል' በሚል ለቅርጫት ኳስ ስፖርት ያለውን ፍቅር በሚያሳየውና በእራሱ በተጻፈው አጭር ፊልም የኦስካር ሽልማትን ለማግኘት ችሎ ነበር።
ኮቢ ብራያንት በአደጋው አብራው ህይወቷ ካለፈው ሴት ልጁ በተጨማሪ የሌሎች ሦስት ሴት ልጆች አባት ነው።












