ኮሮናቫይረስ፡ ምርመራ የተጀመረባቸው የአሜሪካ ምክር ቤት ደህንነት ኃላፊ ከስራ ለቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ ምክርቤት የደህንነት ኮሚቴ ኃላፊና የሪፐብሊካኑ ሊቀመንበር ምስጢራዊ የግብይት ስምምነቶች ፈፅመዋል በሚል ምርመራ መጀመሩን ተከትሎ ከኃላፊነታቸው ለቅቀዋል።
የሰሜን ካሮላይና ተወካዩ ሪቻርድ በር ከስራቸው የለቀቁት ምርመራው ኮሚቴው የሚሰራውን ስራ አንዳያደናቅፈውና ሊረብሸው ይችላል በሚል ነው።
የአሜሪካው የምርመራ ዘርፍ ፌደራል ቢሮ ኢንቨስትጌሽን (ኤፍቢአይ) የሪቻርድ በርን ስልክም በቁጥጥር ስር አውሎ ያደረጓቸው የስልክ ልውውጦች ላይ ምርመራ እያደረገ ነው።
ሴናተሩ ምንም ስህተት አልፈፀምኩም ቢሉም ኤፍቢአይ በበኩሉ ግን የኮሮናቫይረስ ሊያስከትለው የሚችለውን የገበያ መውደቅን ለህዝቡ ይፋ ካልተደረገና ውስጣዊ መረጃን በመጠቀም ሽያጮችን አካሂደዋል ብሏቸዋል።
ሴናተሩ ለቢቢሲ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት አልሰጥም ቢሉም እሳቸውም ሆነ ሚስታቸው በኮሮናቫይረስ ፍራቻ የኢኮኖሚ ቀውስ ከማጋጠሙና የገበያው ሁኔታ አዘቅት ከመግባቱ በፊት የ1.7 ሚሊዮን ዶላር የአክስዮን ሽያጭ አካሂደዋል ተብሏል።
የምክር ቤት አባላት ለህዝብ ይፋ ያልሆነ መረጃን እንዲሁም በስልጣናቸው ምክንያት የተገኙ መረጃዎችን በመጠቀም የንግድ ስምምነቶች ማድረግ ፍፁም ህገወጥ ነው።
እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ የሪፐብሊካኑ ሴናተር ኬሊ ሊዮፍለር እንዲሁም ጄምስ ኢንሆፌ፤ የዲሞክራት ሴናተር ዲያን ፌይንስተንም በኮሮናቫይረስ ምክንያት ገበያው ከማሽቆልቆሉ በፊት ሽያጭ አካሂደዋልም በሚልም ቢወነጀሉም ምርመራ ስለመጀመሩ ግን የተገለፀ ነገር የለም።
ሴናተር ዲያን ፌይንስተን በበላቸው ባለቤቷ ስላካሄዳቸው ግብይቶችን በተመለከተ ከኤፍቢአይ የቀረበላቸውን ጥያቄ እንደመለሱ አስታውቀዋል።
በትክክል ሪቻርድ በር የተወነጀሉበት ጉዳይ ምንድን ነው?
የአሜሪካ የፍትህ መስሪያ ቤት በሪቻርድ በር ላይ ምርመራ ከጀመረ ሁለት ወራት ሊጠጋው ነው።
በመጀመሪያ የሪቻርድ በር የአክስዮን ሽያጭ ይፋ የሆነው ፕሮ ፐብሊካ በሚባለው የምርምራ ጋዜጠኞች ቡድን ሲሆን፤ መረጃውም ይፋ ያደረገው በጥርና የካቲት ወር ላይ ሴናተሩ ከ30 በላይ በተለያዩ ኩባንያዎች ላይ ያሉ የአክሲዮን ድርሻዎቻቸውን መሸጣቸውን ነው።
ሴናተሩ ሸጠዋቸዋል የተባሉት የአክሲዮን ድርሻዎች በኮሮናቫይረስ ከፍተኛ ጫና ከደረሰባቸው ዘርፎች መካከል የሚገኙ ሲሆኑ እነሱም ሆቴሎች፣ ሬስቶራንትና የእቃ ማጓጓዣ ኢንዱስትሪ ናቸው።
ሪቻርድ በር የምክር ቤቱ ደህንነት ኮሚቴ ሊቀመንበር እንደመሆናቸው በአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ስጋቶችን በተመለከተ በየቀኑ መረጃ ያገኛሉ።
ሴናተሩ ህዝቡ በሚያገኘው መረጃዎችና ዜናዎች ተመስርተው " ሽያጮቹን ፈፅሜያለሁ" ብለው ተከራክረዋል።
ነገር ግን እሳቸው የኮሮናቫይረስን ጫና በመፍራት ሽያጮችን ሲያካሂዱ ለህዝቡ ግን ይሰጡት በነበረው መረጃ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ቀላል እንደሆነና ምንም ጉዳት የማያስከትል ነው በማለታቸው ከፍተኛ ትችቶችን ቀርቦባቸዋል።
ጠበቃቸው አሊስ ፊሸር በበኩላቸው በአሜሪካ የፍትህ መስሪያ ቤት የተጀመረውን ምርመራ ደንበኛቸው በፀጋ እንደተቀበሉትና፤ ምርመራውም " ያደረጉት ሽያጭ ተገቢና ህጋዊ መንገድን" የተከተለ መሆኑን ይፋ ያደርጋል ብለዋል።
"ህጉ ሴናተሮችን ጨምሮ ማንኛውም አሜሪካዊ ለህዝብ ይፋ ከሆነ መረጃን መሰረት በማድረግ የአክሲዮኖችን ሽያጭ ማድረግን ይፈቅዳል" በማለት ሴናተሩ ተናግረዋል።
በርካታ የአክሲዮን ድርሻቸውን የፈፀሙት በየካቲት ወር አጋማሽ ሲሆን፤ ለህዝቡ ባይሆንም በንግዱ ዘርፍ ላሉ ሃብታም አሜሪካውያን ቡድንም የኮሮናቫይረስ ኢኮኖሚያዊ ጫና የከፋ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በአሜሪካ ብሔራዊ ሬድዮ የተገኘ የሳቸው ንግግር እንደሚያመላክተው ቡድኑንም ከሃገር ውጭ የሚያደርጓቸውን ጉዟዎችም እንዲሰርዙ አስጠንቅቀዋል። ሴናተሩ ሬድዮው ንግግሬን ከአውድ ውጭ አስተላልፎብኛል ብለዋል ።
ሆኖም አሁን በሪፐብሊካኖች ውሳኔ መሰረት ለተወሰነ ጊዜ ከኃላፊነታቸው ገለል እንዲሉ በተሰጣቸው ትእዛዝ መሰረት ውሳኔውን ተቀብለዋል። በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው ቤታቸው እንዲፈተሽ የፍርድ ቤት ፈቃድ መገኘቱንም ተከትሎ ለባለስልጣናቱ ስልካቸውን አስረክበዋል።
ሪቻርድ በር ማናቸው?
ሪቻርድ በር የምክር ቤቱን ደህንነት ኮሚቴም ለአመታት በአመራርነት የመሩ ሲሆን፤ ሩሲያ በ2016 በነበረው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጣልቃ ገብታለች ወይ የሚለውንም ምርመራ መርተዋል።
በደህንነት ምርመራው መሰረት ሩሲያ ዶናልድ ትራምፕን በመወከል በምርጫው ጣልቃ ገብታለች የሚለው ውጤት ላይ መድረሱን ተከትሎ ኮሚቴውም ውሳኔውን ተቀብሎታል።
የሪቻርድ በር የስልጣን ዘመን በጎርጎሳውያኑ 2023 የሚያልቅ ሲሆን እንደገና ለመወዳደር እንደማያስቡም አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።














