ኮሮናቫይረስ፤ ለስምንት ልጆቿ ድንጋይ የቀቀለችው ኬንያዊት ሃገር ጉድ አስባለች

የፎቶው ባለመብት, TUKO
ስምንት ልጆቿ ጠኔ ቢበረታባቸው ጊዜ ምግብ እንዲመስላቸው ድንጋይ በብረት ድስት የቀቀለችው ኬንያዊት እናት ጉዳይ አገር ጉድ አስብሏል።
ነገሩ እንዲህ ነው፤ ፔኒናህ ባሃቲ የተሰኘችው ይህች ሴት ነዋሪነቷ በባሕር ዳርቻዋ የሞምባሳ ከተማ ነው። ፔኒናህ የስምንት ልጆች እናት ናት። ነገር ግን ባለቤቷ መሞቱ ኑሮን አክብዶባታል።
ይባስ ብሎ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሰውን ከሰው መለየቱ የእሷንም ኑሮ ከድጡ ወደማጡ አድርጎታል።
ከዚያ በፊት በየሰዉ ቤት እየተዘዋወረች ልብስ በማጠብ ነበር የልጆቿን አፍ የምታረጥበው። ስምንት ልጆቿ እራት አይቀርብም ወይ እያሉ ሲወትወቷት ግን አንድ መላ ፈየደች። እራት እስኪቀርብ ጋደም በሉ ትላቸውና ብረት ድስት ውስጥ ድንች መሳይ ነገር ትከት ጀመር።
በወቅቱ ረሃብ ያንገላታቸው ልጆቿ በሚበስለው 'ድንጋይ' ተዘናግተው እንቅልፍ በቀላሉ ሊወስዳቸው እንዳልቻለ እናት ፔኒናህ ተናግራለች።
"'እየዋሸሽን ነው' ሲሉ ወቀሱኝ። እኔ ግን ምንም የማበላቸው ነገር ስላልነበር የማደርገው ጠፋኝ።"
የፔኒናህ ጎረቤት የስምንቱን ሕፃናት ለቅሶ ሰምታ ነው ጉዳዩን ለማጣራት ብቅ ያለችው።

የፎቶው ባለመብት, TUKO
ይህን ጉድ ያስተዋለች ጎረቤት ናት ጉዳዩን ለመገናኛ ብዙሃን ሹክ ያለችው።
የፔኒናህ ታሪክ ኤንቲቪ በተሰኘው የቴሌቪዥን ጣብያ ላይ ከቀረበ በኋላ ኬንያውያን ለእርዳት እጃቸውን ከመዝርጋት አላመነቱም። የሞባይል ስልኳ አስሬ ይንቃጨል ጀመር [በሞባይል ባንኪንግ በሚገባላት እርዳታ] አልፎም ፔኒናህ መፃፍና ማንበብ ስለማትችል በጎረቤቷ ስም በተዘጋጀ የባንክ አካውን ወገኖቿ "አለንልሽ" እያሏት ነው።
ያለ ውሃና መብራት ባለሁለት ክፍል ቤት ውስጥ ከስምንት ልጆቿ ጋር የምትኖረው ፔኒናህ የወገኖቿን እርዳታ 'ተዓምር' ስትል ነው የገለፀችው።
'ኬንያዊያን እንዲህ ዓይነት ፍቅር ይለግሱኛል ብዬ አስቤ አላውቅም። ከሁሉ አቅጣጫ ነበር እየደወሉልኝ እንዴት እናግዝሽ ሲሉኝ የነበረው' ብላለች።
የኬንያ መንግሥት በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ እንኳን መምራት ላልቻሉ ዜጎቹ ነፃ የምግብ እርዳታ አቅርቧል። ነገር ግን ይህ እርዳታ ከፔኒናህ ደጃፍ አልደረሰም።
የፔኒናህ ባልና የስምንት ልጆቿ አባት ባለፈው ዓመት ነበር በአመፀኛ ወጣቶች ሕይወቱን ያጣው።
የፔኒናህ ጎረቤት ወገኖቿንና የኬንያ ቀይ መስቀልን ለእርዳታቸው አመስግናለች። ዕድሜ ለፔኒና አሁን ሞምባሳ ውስጥ ያሉ ራሳቸውን መመገብ ያልቻሉ ኬንያዊያን እርዳታ እየተደረገላቸው ነው።
የኬንያ መንግሥት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት በሚል ሞምባሳን ጨምሮ ወደ ሌሎች ዋና ዋና ከተሞች መግባትም ሆነ መውጣት ከልክሏል። አልፎም በመላ አገሪቱ ከምሽት 1 ሰዓት እስከ ንጋት 11 ሰዓት የሚቆይ ሰዓት እላፊ ታውጇል።
በርካታ ድርጅቶች በራቸውን ዘግተዋል። የተቀሩት ደግሞ በአነስተና ሠራተኛ ለመንቀሳቀስ ተገደዋል። ይህ ደግሞ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ኬንያዊያን ከሥራ ውጪ አድርጓቸዋል።
ለኮሮናቫይረስ ምርመራ እንዲሆን ከዓለም ባንክ ወፈር ያለ ዶላር የተቀበለው የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ገንዘቡን በሻይ፣ ብስኩትና በሞባይል ካርድ ነው የጨረሰው የሚል ሪፖርት ወጥቷል። ይህ ዜና ከፔኒናህ ታሪክ ጋር መግጠሙ ኬንያዊያንን አስቆጥቷል።
ማኅበራዊ ድር-አምባዎች ላይ ገዥውን መንግሥት በወቀሳና ስድብ የጠራረጉትም አልጠፉም።
ኬንያ 395 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ያረጋገጠች ሲሆን 17 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።














