ሱፐር ቲዩስደይ፡ የትራምፕ ተቀናቃኝ ማን ሊሆን እንደሚችል የሚለው ወሳኝ ቀን

የአሜሪካ ምርጫ

'ሱፐር ቲዩስደይ' ይሏታል። እኛ ኃያሏ ማክሰኞ ስንል በግርድፉ ተርጉመናታል። ለነገሩ ትራምፕን ለመርታት ኃያል መሆን ሳያሻ አልቀረም።

የአሜሪካ ፖለቲካ '9 አረንጓዴ ጠርሙሶች' እያልን በልጅነታችን እንደዘመርነው መዝሙር ያለ ነው። ትራምፕን እንገነድሳለን ብለው ቆርጠው ከተነሱት በርካታ ዴሞክራቶች መካከል አብዛኞቹ ተገንድሰው አሁን ጥቂቶች ቀርተዋል።

ለአብነት እንኳ ዛሬ ጠዋት ኤሚ ክሎቡቻር የተሰኙት ልስልስ ዴሞክራት ከቅድመ-ምርጫው ራሳቸውን ማግለላቸውን አሳውቀዋል።

ከዚያ በፊት ጥቁር አሜሪካዊያኑ ኬሪ ቡከርና ካማላ ሃሪስ፤ ፒት ቡቲጀጅ፣ እንዲሁም አንድሪው ያንግ፣ ወድቀው የተሰበሩ አረንጓዴ ጠርሙሶች ናቸው። አብዛኛዎቹ በዕድሜ አሁን ከቀሩት ዕጩዎች ያንሳሉ። እንደ ኦባማ በለጋ ዕድሜያቸው [በፖለቲካ ሒሳብ] ታሪክ መሥራት ባይችሉም ልምዳቸውን በጥቁር ቦርሳቸው ይዘው ሄደዋል።

ኢንዶርስመንት

በአሜሪካ ፖለቲካ 'ኢንዶርስመንት' የምትለው ቃል በጣም ትከበራለች። 'ኢንዶርስ' ተደረጉ ማለት ፈገግ ብለው መተኛት ይችላሉ ማለት ነው። ኢንዶርስመንት - ይሁንታ እንደማለት ነው።

ለምሳሌ የቀድሞው ፕሬዝደትን ባራክ ኦባማ፤ ትራምፕን ለመፈንገል እየታገሉ ያሉት ጆ ባይደንን ኢንዶርስ ቢያደርጓቸው [ልብ ይበሉ ኦባማ እስካሁን ለትኛውንም ዕጩ ይሁንታን አልሰጡም] የኦባማ ደጋፊዎች ተገልብጠው የባይደን ከመሆን የሚያግዳቸው የለም።

በአሜሪካ ፖለቲካ ኢንዶርስመንት ገንዘብ ነው፤ ኃይል ነው፤ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ሁኔታዎችን የመገለባበጥ ኃይል ያለው ሱናሚ ነው።

'ኧረ የሳቸውስ ነገር አከተመ' የተባለላቸው ጆ ባይደን ዕድሜ ለኢንዶርስመንት ይኸው የሹፌሩን ወንበር ለመያዝ እየተገዳደሩ ነው። ባለፈው ሳምንት በደቡብ ካሮላይና ከተደረገው ምርጫ በፊት ጆ ከአንድ ወሳኝ ሰው የኢንዶርስመንት ስጦታ ይደርሳቸዋል። ምርጫውን በርኒ ሳንደርስን በመዘረር ያሸንፋሉ። የኢንዶርስመንት ጥቅሙ እዚህ ድረስ ነው እንግዲህ።

ሱፐር ቲዩስደይ

በአሜሪካ ምርጫ ሁለት ወሳኝ ቀናት አሉ። አንደኛው ዋናው የምርጫ ዕለት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ተቀናቃኝ ሆኖ የሚቀርብ ዕጩ የሚለይበት ነው።

የአሜሪካ 14 ግዛቶች በሱፐር ቲዩስደይ ይሳተፋሉ። ድምፃቸውን ዕጩዬ ለሚሉት ሰው ይሰጣሉ። ዘንድሮ ተረኞች ዴሞክራቶች ናቸው። ሪፐብሊካኑ ትራምፕን ከነጩ ቤተ-መንግሥት ለመፈንቀል የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ነው።

የ78 ዓመቱ አዛውንት ፖለቲከኛ በርኒ ሳንደርስ በዘንድሮው ምርጫ ብዙ ተዓምራትን አሳይተዋል። እዚህ ይደርሳሉ ብሎ የገመተ ብዙ አልነበረም። ለዚያም ነው ብዙዎች 'እኒህ ሽማግሌማ አይቻሉም' የሚሏቸው።

ሌላኛው ተጠባቂ የቀድሞው ምክትል ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ናቸው። ከአንድ ዓመት በፊት ወጣት ዴሞክራቶች 'እኔ ልወክል፤ እኔ ልሁን' ብለው ወደ መድረክ ሲመጡ 'አሁን ጆ ባይደንን ሊያሸንፉ ነው የሚለፉ?' ተብለው ነበር። የኋላ ኋላ ግን በክርክር መድረኮች ላይ ባይደን እየቀለሉ መጡ። አልፎም በትራምፕ አስተዳደር ስማቸው ይብጠለጠል ጀመር።

የባይደን ነገር ቤተ-መንግሥት ወዲህ እሳቸው ወዲያ መሰለ። ባይደን ግን አልተኙም። አክትሞላቸዋል ሲባል አፈር ልሰው ተነሱ። በግዙፉ የደቡብ ካሮላይና ግዛት ተቀናቃኞቻቸውን ግራ ቀኝ ዘርረው መሪውን ጨበጡ።

ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, EPA

በቅርቡ ራሳቸውን ከምርጫው ካገለሉ ዕጩዎች መካከል ኤሚ ክሎቡቻርና ፒት ቡቲጀጅ ባይደንን ኢንዶርስ ካደረጉት መካከል ናቸው።

የጆ ባይደን አፈር ልሶ መነሳት ለነባር ፖለቲከኞች ስጋት ነው። የጆ አልሞት ባይነት የበርኒ ሳንደርስ እና ኤሊዛቤት ዋረንን ፊት አቅልቶትም ይሆናል። ልጥጡ ሃብታም ማይክ ብሉምበርግም በብስጭት ሳይደብኑ አልቀረም።

ገና ከእንቅልፏ ያልነቃችው አሜሪካ ዕለተ ማክሰኞ አልደረሰላትም። ከ14 ግዛቶች መካከል ካሊፎርኒያና ቴክሳስ ምራቅ የሚያስውጥ ሕዝብ አላቸው። በእነዚህ ሁለት ግዛቶች አሸናፊነት የተቀዳጀ ዕጩ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር አንገት ለአንገት ለመተናነቅ ይዘጋጃል።

እየወጡ ባሉ ግምቶች መሠረት በርኒ ሳንደርስ መጪው የትራምፕ ተቀናቃኝ ሊሆኑ ይችላሉ። ግን የአሜሪካን ፖለቲካ ከመገመት አዲስ ፕላኔት ማግኘት ሳይቀል አይቀርም።

ጆ ባይደን መሪውን ይዘው ጠላቶቻቸውን ክው ሊያደርጉ ይችላሉ። ቢሊዬነሩ ማይክ ብሉምበርግም የዋዛ አይደሉም። ልብ ይበሉ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝደንት ለመሆን ያለሙት ኤሊዛቤት ዋረንም 'ሰርፕራይዝ' ሊያደርጉን ይችላሉ።