'ድሃውን ትራምፕ' ሀብታሙ ማይክ ብሉምበርግ ይተኳቸው ይሆን?

እጩዎች

የአሜሪካን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ገንዘብ ይበላል። ሚሊዮን ዶላሮች የሌሉት አሜሪካዊ ወደዚያ ሰፈር ድርሽ ማለት አይችልም። በሕግ ባይከለከልም በገቢር እንዲያ ነው።

ትራምፕና ሂላሪ ለምሳሌ በድምሩ 2.4 ቢሊዮን ዶላር ከስክሰዋል። ይሄ ገንዘብ እኛ ጋር ቢመጣ ግማሽ የሕዳሴ ግድብ ይጨርስልናል።

በአሜሪካ ድሃ እንዴት ሆኖ ፕሬዝዳንት ይሆናል? በየት አድርጎ? እርግጥ በኑሮ ለነጣ፣ ለገረጣ አሜሪካዊ በሮቹ ሁሉ ዝግ ናቸው ማለት አይደለም። ጭንቅላት ብቻ ይዞ መወዳደርም አልተከለከለም፤ ቢሊየነር ደጋፊ ከተገኘ። አልያ ግን ጉዞው እሾሃማ ነው።

እርግጥ ነው በዚያች ምድር ተወልዶ፣ በዚያች ምድር 14 ዓመት የኖረ እና ዕድሜው 35 እና ከዚያ በላይ የሆነ አሜሪካዊ ሁሉ ለፕሬዝዳንትነት ልወዳደር ቢል አርፈህ ቁጭ በል የሚለው የለም። ነገር ግን ያለጥርጥር ሩጫው ባጭር ይቀጫል።

ለዚያም ይሆናል ቢሊየነሮች በብዛት ዕጩ ሆነው የምናየው። ለዚያ ይሆናል ከእያንዳንዱ እጩ የመነጋገሪያ አትሮንስ ጀርባ አንድ ቢሊየነር እንዳለ የሚነገረን?

ብሉምበርግ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ማይክል ብሉምበርግ

ብሉምበርግና 'የማያልቀው' ዶላሩ

በአሜሪካ ምርጫ ለሚወዳደሩ ዲሞክራቶች ገንዘብ በመቀፍቀፍ የሚታወቁ ሁለት ቢሊየነሮች አሉ። አንዱ ጆርጅ ሶሮስ ነው። ሌላው ደግሞ ማይክል ብሉምበርግ።

ማይክል ብሉምበርግ ማን ነው ለሚለው ትንሽ ዝቅ ብለን እናነባለን።

ለጊዜው ብሉምበርግ እጩ የዲሞክራቲክ ደጋፊ ከመሆን አልፈው እጩ ተወዳዳሪ ለመሆን እንዴት እንደደፈሩ እንመልከት። በተጨማሪም ብሉምበርግ ረዥሙን ጉዞ ከጀመሩ ወዲህ ምን እንዳጋጠማቸው በአጭሩ እንመልከት።

ከሰሞኑ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ቴሌቪዥን የዲሞክራቲክ እጩዎች የሙግት ወደ አትሮንስ መጥተው ለሕዝብ ታይተዋል፤ በላስቬጋስ፣ ኔቫዳ።

ብሉምበርግ ገና ከወዲሁ ለማስታወቂያ 1 ቢሊየን 400 ሚሊዮን ብር ገደማ ረጭተዋል።

ያ ምሽት ለእርሳቸው ጥሩ አልነበረም፤ ተፎካካሪዎቻቸው አላስተረፏቸውም። ያለፈ የታሪክ ጠባሳቸውን እየነካኩ እረፍት ነስተዋቸዋል።

አንዱ ሁለቱን ብቻ እንጥቀስ።

ግራ ዘመሙና ላቅ ያለ የፕሬዝዳንትነት ተስፋ የተጣለባቸው የዲሞክራቱ እጩ በርኒ ሳንድረስ ብሉምበርግን ክፉኛ ነቅፈዋቸዋል፤

"ብሉምበርግ አያፍርም እንዴ? እኛ ስለፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እናወራለን....እሱ'ኮ እንዲያውም የኢፍትሐዊነት ተምሳሌት ነው፤ 125 ሚሊዮን አሜሪካዊያን ሀብታቸው ተደምሮ የእሱን አያህልም። እንደዚህ ዓይነት ሞራል ይዞ....?" የሚል ይዘት ያለው ንግግር አድርገዋል።

ሌላኛዋ እጩ ኤልዛቤጥ ዋረን ደግሞ "...አንድ ጊዜ ስሙኝማ፥ ዘንድሮ ከማን ጋር እንደምንወዳደር ልንገራችሁ። ሴቶችን ከሚያጎድፈውና የሴት ለሴት ተፋቃሪዎችን 'ፈረስ-ፊት' ብሎ ከሚጠራ ሰው ጋር ነው። ይህን ጊዜ ስለ ትራምፕ የማወራ መስሏችሁ ይሆናል እኮ፤ አደለም፤ የማወራው ስለ ከንቲባ ብሉምበርግ ነው።"

ማይክል ብሉምበርግና የዋሺንግተን ከንቲባ ሙሪል ቦውሰር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ማይክል ብሉምበርግና የዋሺንግተን ከንቲባ ሙሪል ቦውሰር

የብሉምበርግ ጥላሸቶች

የሚከተሉት አጫጭር ኩነቶች ብሉምበርግ ባለፈ ሕይወታቸው ተናገሯቸው የሚባሉና ወደፊት ዋጋ ያስከፍሏቸዋል ተብለው የሚጠበቁ ናቸው።

  • እ.አ.አ በ1990 ዋሺንግተን ፖስት እንደዘገበው ማይክል ብሉምበርግ በአንድ ወቅት ስለሴቶች እንዲህ ብለው ነበር። "ሴት ልጅ በአስተሳሰቧ ልደነቅ የምትል ከሆነ ቤተ መጽሐፍት እንጂ የውበት ሳሎን ምን ያስኬዳታል?"
  • ይኸው ጋዜጣ እንደዘገው በአንድ ወቅት ብሉምበርግ ሴት ሠራተኛቸው እርጉዝ ሆና አይተው "አስወርጂው" እንዳሏት ዘግቦ ነበር። እርሳቸው ግን ይህን ስላለማለታቸው ቃለ መሐላ ፈጽመው ክደዋል።
  • የኒውዮርክ ከንቲባ በነበሩ ጊዜ "አስቁም! ፈትሽ" የሚል ፖሊሲ አምጥተው ጥቁሮችንና ላቲኖዎችን ለፖሊስ ለእንግልት ዳርገዋል ተብለው ይተቻሉ።
  • በአንድ ወቅት "ደግሞ ግብርና ሥራ ነው እንዴ? እዚህ ያለን ማንኛውንም ሰው ላስተምር እችላለሁ" የሚል መልዕክት ያለው ንግግር በማድረጋቸው ተወቅሰዋል።

በአሜሪካ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የጤና ሁኔታ መሠረታዊ ነጥብ ነው። ሽማግሌው ሳንደርስ መጠነኛ የልብ ሕመም አጋጥሟቸው ስለነበር ከዚያ ወዲያ የጤና ሁኔታቸውን የሚያትት መረጃን ለሕዝብ ይፋ አላደረጉም። ብሉምበርግም ከዚህ ቀደም የልብ ሕመም አጋጥሟቸዋል የሚሉ መረጃዎችም ወጥተዋል። ይህም ሌላ ጥቁር ነጥብ ሆኖ ተመዝግቦባቸዋል።

የሚገርመው ሳንድረስ ከብሉምበርግ ጋር ሲነጻጸሩ በዕድሜ እጅግ የጃጁ ይምሰሉ እንጂ ሁለቱም 78 ደፍነዋል። ከሁለቱ አንዱ ትራምፕን ተገዳድረው በለስ ቢቀናቸው እንኳ በአሜሪካ ታሪክ በስተርጅና ወደ ነጩ ቤተመንግሥት ለመግባት ቀዳሚ ይሆናሉ።

ብሉምበርግና ትራምፕ ድሮ ጥሩ ወዳጆች ነበሩ። የአሁኑን አያድርገውና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ብሉምበርግና ትራምፕ ድሮ ጥሩ ወዳጆች ነበሩ። የአሁኑን አያድርገውና

ሁለቱ ቢሊየነሮች አይዋደዱም

እርግጥ ነው ከብሉምበርግ አንጻር ትራምፕ ቆሎ ቆርጥመው ያድራሉ የሚባሉ ድሀ ናቸው ሊባል ይችላል። ትራምፕ ምን አላቸውና! 4 ቢሊዮን ዶላር ቢሆን ነው ሀብታቸው። ይህ ለብሉምበርግ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ለዚያም ይሆናል የማይዋደዱት።

ትራምፕና ብሉምበርግ ዓይንና ናጫ ናቸው። ለነገሩ ትራምፕ እንኳን ከሌላ ከራሳቸውስ ቢሆን ይስማማሉ?

ለምሳሌ ይህንን የኔቫዳውን የክርክር መድረክ ተከትሎ ትራምፕ በትዊተር ሰሌዳቸው፣ "ይሄ በንቅዘት የተዘፈቀው የብሉምበርግ ሚዲያ ይሄ ክርክር ምን ያህል ውዳቂ እንደነበር ይዘግብ ይሆን?" ብለው ጻፉ።

የሚዲያው ባለቤት ማይክል ብሉምበርግ ለምላሹ አልዘገዩም፤ "ይሄ ከክስ ያልጸዳው ፕሬዝዳንት አሁንም ዝም አይልም?" ብለው በነገር ሸንቆጥ አድርገዋል፤ ትራምፕን።

ብሉምበርግ ባለፈው ሕዳር ለፕሬዝዳንትነት እንደሚወዳደሩ ከገለጹ ወዲህ የእርሳቸው ንብረት የሆነው ብሉምበርግ ሚዲያ እርሳቸውንም ሆነ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ባላንጣዎቻቸው ላይ የምርመራ ዘገባ እንደማይሰራ ይፋ አድርጓል።

ሌላ ጊዜ ደግሞ ትራምፕ እንዲህ አሉ፤ "እንደ ብሉምበርግ ቀሽም ተፎካካሪ አይቼ አላውቅም፤ ሳንድረስ ቢፎካከረኝ ይሻለኛል።"

ብሉምበርግ ከዚህ በኋላ ለፕሬዝዳንትነት ብቁ አይሆንም። ዕድሜው ገፍቷላ። በሕይወት ሳለ የመጨረሻው ሙከራ ነው የሚሆነው። ለቢሊየነር ደግሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከመሆን በላይ ምን ሌላ ሕልም ሊኖረው ይችላል?

ለዚህም ነው ይህ ምርጫ "የቢሊየነሮቹ መዝናኛ" የሚባለው።

"ምናልባት ከትራምፕ ጋር ስለማትስማሙ ይሆን? ለመወዳደር የወሰንከው" ተብለው ነበር ማይክል ብሉምበርግ። በፍጹም፤ ሰውዬው [ትራምፕ] ዝርክርክ ነው፤ አገር መምራት የሚችል አይደለም፤ የእሱን ምስቅልቅል መልክ ለማስያዝ ነው" ብለዋል።

ትራምፕ በበኩላቸው "ይሄ ሰውዬ ገንዘቡን በማይሆን ነገር እንዳይረጭ፤ ምከሩት" ብለዋል ለጋዜጠኞች።

ማይክ ብሉምበርግ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በሀብት ሲነጻጸሩ ዝሆን ናቸው ብለናል። በቀደም ለታ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ደግሞ የዓመቱን ቀልድ ቀልደዋል-ብሉምበርግ።

አንድ ጋዜጠኛ "በቃ ይሄ ውድድር የሁለት ቢሊየነሮች ሆነ ማለት ነው?" ይላቸዋል ለብሉምበርግ።

ብሉምበርግ ቀበል አድርገው "አንዱ እኔ ነኝ፤ ሁለተኛው ቢሊየነር ደግሞ ማን ነው?" ሲሉ የትራምፕን ከእርሳቸው አንጻር የ'ድህነት' መጠን የት እንደሆነ ጠቆም አድርገዋል። የተሰበሰቡት ጋዜጠኞች በነገሩ አለመሳቅ አልቻሉም።

የብሉምበርግ ወላዋይነት

ብሉምበርግ ድሮ ገለልተኛ ነበር። በ2001 የኒውዮርክ ከተማ ከንቲባ ለመሆን ሲል ሪፐብሊካን ሆነ። በ2007 ደግሞ ገለልተኛነቱን መልሶ ያዘ። በ2018 ደግሞ ተመልሶ ዲሞክራት ሆነ። "ብሉምበርግ-ወላዋዩ" ይሏቸዋል ይህን ያዩ ተቺዎቻቸው።

ብሉምበርግ የኒውዮርክ ከንቲባ ከሆኑ በኋላ ሲጃራ በየቡና ቤቱ እንዳይጨስ ሕግ አውጥተዋል። የመንገድ ላይ ንግድን አስቀርተዋል። በእርሳቸው የከንቲባነት ዘመን በኒውዮርክ ወንጀል ቀንሷል። ምጣኔ ሐብቱም ጨምሯል። ይሄ ምናልባት እንደ ስኬት የሚመዘገብላቸው ነው የሚሆነው።

ብሉምበርግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ተና'ዶ ቢሊየነር የሆነው ብሉምበርግ

ብሉምበርግ የሚለው ስም ለብዙዎች አዲስ አይደለም።

ብሉምበርግ የሚል ግዙፍ ሚዲያ አለ። ብሉምበርግ የሚባል የዜና ወኪል አለ። ብሉምበርግ ቲቪ አለ። ብሉምበርግ ሳምንታዊ የፋይናንስ መጽሔት አለ። ባንኮችና ለስቶክ ማርኬት ግብአት የሚሆኑ የፋይናንስ መረጃ አቀነባባሪ ኩባንያ የእሳቸው ነው። ሁሉም በስማቸው ነው ያሉት።

የናጠጡ ሐብታም ናቸው። ፎርብስ 69 ቢሊዮን ይገመታል ሀብታቸ ይላል። የለም 88 ቢሊዮን ደርሷል የሚሉ መረጃዎችም አሉ። ለማንኛውም አሁን የምድራችን 9ኛው ሀብታም እሳቸው ናቸው።

የመሣሪያ ቁጥጥር እንዲጠናከር ገንዘብ ይለግሳሉ። ለታዳጊ አገሮች የውሃ ፕሮጀክቶች ላይም አይሰስቱም። ለዲሞክራቲክ እጩዎች ሲቸግራቸው የእርሳቸውን ደጅ ነው ይጠኑ የነበረው።

ብሉምበርግ ወጣት እያሉ ከሥራ ተባረው ተናደዱና ነው በዚያው ቢሊየነር የሆኑት ይላል አንድ የታሪካቸው ቅንጣት። እሳቸውም ቢሆኑ "ያኔ ነው ማርሽ ቀይሬ የራሴን ሀብት ማፍራት የጀመርኩት" ይላል።

ብሉምበርግ በፈረንጆቹ በ1942 ነው የተወለዱት። መካከለኛ ገቢ ካለው ቤተሰብ። አባቱ ሂሳብ ያዥ ነበሩ።

በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ምሕንድስና አጥንተዋል። ኤምቢኤ ደግሞ ከሃርቫርድ ወስደዋል። ከዚያ ዎልስትሪት ገቡ።

በ1972 የታዋቂው የ'ሶሎሞን ብራዘርስ' ኢንቨስትመንት ባንክ ቅጥረኛ ነበሩ። ከዚያ ትንሽ ድርሻ ሳይገዙ አልቀረም። ለ9 ዓመት አብረው ከሠሩ በኋላ ሶሎሞን ብራዘርስ ባንክ ተሸጠ። ብሉምበርግም ተባረሩ።

ሲባረሩ የተሰጣቸውን ገንዘብ ይዘው የራሳቸውን ሥራ ለመሥራት ተፍ ተፍ ማለት ጀመሩ። 'ብሉምበርግ ኩባንያን' የከፈቱት ከዚያ ጊዜ ወዲህ ነው።

ዛሬ እንደ ብሉምበርግ በዓለም ዙርያ የፋይናንስ መረጃ 'ዳታ'ን የሚሸጥ ግዙፍ ኩባንያ የለም። የሚያዘወትረሩት ጥቅስ የሚከተለው የሆነውም ለዚሁ ነው፤ "In God we trust. Everyone else, bring data,"።

'ዳታ' 6ኛው የአሜሪካ ሞጃ አድርጓቸዋል። 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንትስ ያደርጋቸው ይሆን?