ኬንያዊያን ማክሰኞ በቤታቸው የሚቀበሩትን ሞይን እየተሰናበቱ ነው

የዳንኤል አራፕ ሞይ ስንብት

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የዳንኤል አራፕ ሞይ ስንብት

ኬንያን ለረጅም ጊዜ የመሩትን የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዳንኤል አራፕ ሞይን አስከሬን ለመሰናበት ኬንያዊያን በመዲናዋ ናይሮቢ በሚገኘው የፓርላማ ሕንጻ ሰልፍ ይዘው እየተሰናበቱ ነው።

ከፈረንጆቹ 1978 እስከ 2002 ድረስ የአገሪቱን የመጀመሪያ ፕሬዝዳንት ጀሞ ኬንያታን ተክተው ኬንያን በፕሬዝዳንትነት ለ24 ዓመታት የመሩት ዳንኤል አራፕ ሞይ፤ ማክሰኞ ዕለት ነበር በ95 ዓመታቸው የሞቱት።

በስንብት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዳንኤል አራፕ ሞይን "ምልክት የሆኑ መሪ ናቸው" ብለዋቸዋል።

በርግጥ ሞይ በሁለት ወገን ነው የሚታወሱት። ተቺዎቻቸው አምባገነን ነበሩ ሲሏቸው፤ ደጋፊዎቻቸው ደግሞ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት እንጅ አምባገነን አልነበሩም በማለት ይከራከሩላቸዋል።

የፖለቲካ ተቃዋሚዎቻቸውን አይምሩም፤ በመግደልና በመግረፍ ይቀጧቸው ነበር በማለት ተቺዎቻቸው ይከሷቸዋል።

በ1982 እ.አ.አ የተደረገውና የከሸፈው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ይህንን አምባገነንነት ባሕርይ እንዲላበሱ እንዳደረጋቸው ብዙዎች ይስማማሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ምንም እንኳ ስልጣናቸውን ከ24 ዓመታት በኋላ ያስተላለፉ ቢሆንም ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በማድረግም ዳንኤል አራፕ ሞይ በኬንያዊያን ዘንድ ይወደሳሉ።

የዳንኤል አራፕ ሞይ ስንብት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የዳንኤል አራፕ ሞይ ስንብት

በዛሬው ዕለት ታዲያ የእኒህን የቀድሞ መሪያቸውን አስከሬን ለመሰናበት ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል የተወጣጡ ኬንያዊያን በመዲናዋ ናይሮቢ ከፓርላማ ሕንጻ ፊት ለፊት ረጅም ሰልፍ ተሰልፈው ወረፋ እየጠበቁ በመሰናበት ላይ ይገኛሉ።

አን ንጃምቢ የተባለች የ46 ዓመት ወይዘሮ የቀድሞ መሪዋን ለመሰናበት ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዛ ናይሮቢ ተገኝታለች። "ትምህርት ቤት በነጻ ወተት እንድንጠጣ ያደረጉንን አልረሳውም። በጣም ለጋስ ሰው ነበሩ፤ መቼም አልረሳቸውም" ብላለች።

አክላም "በ1988 ትምህርት ቤት አግኝቻቸው በርትቼ መማር እንዳለብኝ መክረውኛል፤ ያን በማድረጋቸውም ትምህርቴን እንዳጠናቅቅ የትምህርት ወጪዬን የሸፈኑልኝ ያክል ተሰምቶኝ ትልቅ መሪዬ ናቸው ብዬ ነው የማስታውሳቸው" ብላለች።

ዛሬ የመጀመሪያው የመሰናበቻ ቀን ሲሆን እስከ ሰኞ ድረስ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ኬንያዊያን በፓርላማው ሕንጻ እየተገኙ እንዲሰናበቱ እድል ተመቻችቶላቸዋል።

የኬንያ ሁለተኛው ፕሬዝዳንት ዳንኤል አራፕ ሞይ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው በሚቀጥለው ማክሰኞ የሚደረግ ሲሆን፤ የሚቀበሩትም ከመዲናዋ ናይሮቢ 200 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው የግል ቤታቸው ነው።