ገንዘብ ያለው ሊገዛው የሚችለው 'ወርቃማው' ፓስፖርት ለምን ተፈላጊ ሆነ?

ፓስፖርት

የአውሮፓ ሕብረት ተልዕኮ አባላት በማልታ ያለውን የሕግ የበላይነት ለመመርመር ጉብኝት እያደረገ ሲሆን የታዋቂዋ የምርመራ ጋዜጠኛ መገደልም አገሪቱን ጫና ውስጥ ከቷታል።

በፈረንጆቹ 2017 የተፈጸመው የጋዜጠኛ ዳፊን ካሩዋና ጋሊዚያ ግድያ የማልታን ፖለቲካዊ መዋቅር ያፍረከረከና በአገሪቱ የተንሰራፋውን ሙስና ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው የሚሉም አልጠፉም።

ከዚህ በተጨማሪ 'ወርቃማ ፓስፖርት' ሥርዓት የሚባለው የሌላ አገር ዜጎች ከፍተኛ ገንዘብ በማፍሰስ የማልታን ዜግነት ሲገዙ ተስተውሏል። ይህም ለግለሰቦቹ ከግብር ማምለጫና ፖለቲካዊ ሽሽት ለሚያደርጉ ሰዎች ጥሩ መሸሸጊያ እንዲሆን በሩን ከፍቷል።

ለመሆኑ የማልታን ዜግነት ለመግዛት ምን ያክል ገንዘብ ያስከፍላል?

ይህንን አሰራር የማልታ መንግሥት ያስተዋወቀው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2014 ሲሆን ባለሃብቶችንና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ነው ያዘጋጀሁት ይላል። በዚህ አንድ ግለሰብ የማልታን ፓስፖርት ለማግኘት የሚከተሉትን ማድረግ አለበት፡

  • 650 ሺህ ዩሮ ለብሔራዊ ልማት ፈንድ ማበርከት
  • 150 ሺህ ዩሮ በማልታ የአክሲዮን ገበያዎች ወይም ድርሻ መግዛት
  • ቢያንስ እስከ 350 ሺህ ዩሮ የሚያወጣ ቤት መግዛት ወይም በዓመት 16 ሺህ የሚያስከፍል ቤት መከራየት

እነዚህ ሁሉ ወጪዎች ሲደመሩ ከ 1.1 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ወጪን ይጠይቃል ማለት ነው። በተጨማሪም አመልካቾች በማልታ ቢያንስ የ12 ወራት የኑሮ ፈቃድ ማግኘት ያለባቸው ሲሆን ነገር ግን በሀገሪቱ መኖር አይጠበቅባቸውም።

የማልታ መንግሥት ይህንን አሰራር ካስታወቀ በኋላ 833 ባለሀብቶችና 2109 የቤተሰብ አባላት የማልታ ዜግነትን ማግኘት ችለዋል።

ማንኛውም የማልታ ፓስፖርት የያዘ ሰው ደግሞ በመላው አውሮፓ እንደልቡ መንቀሳቀስ ይችላል።

በአውሮፓዊያኑ 2017 እና 2018 ግማሽ ድረስ ማልታ ለውጭ አገራት ዜጎች ከሸጠችው ፓስፖርት ከ162 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ማግኘት የቻለች ሲሆን ይህም ከአገሪቱ ዓመታዊ አጠቃላይ ምርት 1.38 የሚሆነውን ሸፍኗል።

ምንም እንኳን የማልታ መንግሥት ከየትኞቹ አገራት የሚመጡ ሰዎች ፓስፖርቶችን እንደሚገዙ ግልጽ ባያደርግም አገራቱ የሚገኙባቸውን አካባቢዎች ግን አስቀምጧል። በዚህም መሰረት አብዛኛዎቹ ፓስፖርት የገዙት ሰዎች የመጡት በቀዳሚነት ከአውሮፓ ሲሆን በመቀጠል ከመካከለኛው ምሥራቅና እሲያ ተቀምጠዋል።

ነገር ግን የአውሮፓ ሕብረት በየዓመቱ የሚደረጉ የዜግነት ጥያቄዎችን ለህዝብ ይፋ የማድረግ ግዴታ አለበት። ማልታ ይህንን ሥርዓት ይፋ ካደረገች ወዲህ በርካታ ከሳዑዲ አረቢያ፣ ከሩሲያ እና ከቻይና የመጡ ግለሰቦች ዜግነት ገዝተዋል።

ለምሳሌ ሳዑዲ አረቢያ በአውሮፓዊያኑ እስከ 2015 ድረስ የትኛውም ዜጋዋ የማልታ ፓስፖርት ገዝቶ አያውቅም ነበር። ከ2015 በኋላ ግን 400 ሳዑዲዎች ወርቃማውን የማልታ ፓስፖርት ገንዘባቸውን ፈሰስ አድርገው ገዝተዋል።

ይህንን ሥርዓት በመጠቀም በርካታ ቤተሰቦች ልጆቻቸው የተሻለ ትምህርት እንዲያገኙ በማሰብና ባሉበት አገር ችግር ሲያጋጥማቸው በማንኛውም ሰዓት ወደ ሁለተኛ አገራችው እንዲሄዱ በማሰብ ጥሪታቸውን እያሟጠጡ ወርቃማውን የማልታ ፓስፖርት እየገዙ ነው።

በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ ቆጵሮስ እና ቡልጋሪያ ተመሳሳይ ሥርዓት አላቸው።

በአውሮፓዊያኑ ከ2008 እስከ 2018 ድረስ ቆጵሮስ ለ1685 ኢንቨስተሮችና ለ1651 የቤተሰብ አባላት ዜግነት እንደሰጠች ታውቋል።