የሞት ፍርድ ተፈርዶበት የነበረው ኬንያዊ የሕግ ዲግሪውን አጠናቀቀ

ዊልያም ኦኩሙ

የፎቶው ባለመብት, Africa Prisons Project

የሞት ፍርድ ተፈርዶበት የነበረ ኬንያዊ ከለንደን ዩኒቨርስቲ የሕግ ዲግሪውን ከሰሞኑ አግኝቷል።

ናይሮቢ በሚገኘው ኪማቲ እስር ቤት የምርቃት ሥነ ሥርዓት ተዘጋጅቶለት የነበረው ዊልያም ኦኩሙ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማው ለፎከስ ኦን አፍሪካ ራዲዮ ገልጿል።

"ይህ የሚያሳየን ከቆሻሻም ቢሆን መልካም ነገር እንደሚገኝ ነው" በማለት ተናግሯል።

አክሎም "ምን ዓይነት ደስታ ውስጥ እንዳለሁኝ ሊገልፅልኝ የሚችል የእንግሊዝኛ ቃል የተፈጠረ አይመስለኝም" ብሏል።

በሠላዎቹ እድሜ ላይ የሚገኘው ዊልያም ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ነበር ከእስር የተፈታው፤ የሕግ ዲግሪውም ሕይወቱን እንደቀየረ ገልጿል።

እስር ቤትም ውስጥ በነበረበት ወቅት ያገኘው እውቀት ራሱንም ሆነ ሌሎች እስረኞች ለመከላከል እንደጠቀመው አስረድቷል።

የሕግ ትምህርት ለመማርም ያነሳሳው ጉዳይ የሞት ፍርድ የተፈረደበት ሕጉን ባለመረዳቱና በሂደቱም ወቅት ትክክለኛ ጠበቃ ባለማግኘቱ መሆኑንም ገልጿል።

ከሁለት ዓመታት በፊት የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተፈረደበት የሞት ቅጣት ከኬንያ ሕገ መንግሥት ጋር የማይጣጣም መሆኑንም ገልፆ ነበር።

ዊልያም የሞት ቅጣት ተፈርዶበት የነበረው የዝርፊያ ወንጀልን ለመፈፀም ኃይልን በመጠቀሙ ሲሆን፤ ለራሱም ጥብቅና በመቆም የሞት ቅጣቱ የከፋ ነውም ሲል አስረድቷል።

ዳኛውም ቅጣቱን ወደ አስር ዓመታት አቅልለውለታል፤ እስሩንም ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ አጠናቆ ተፈትቷል።

በኬንያ እስር ቤቶች ከአምሳ ሺህ በላይ እስረኞች ያሉ ሲሆን፤ ብዙዎቹ ደግሞ ቀለል ያለ ወንጀል የፈፀሙ እንደሆነ ተገልጿል።

ድህነትና አለመማር ተደራርበው እስረኞች ትክክለኛ የሕግ ውክልና እንዳያገኙ አድርጓቸዋል ተብሏል።