ስለእንግሊዟ ንግሥት ኤልሳቤጥ ያልተሰሙ አምስት እውነታዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የንግሥት ኤልሳቤት ሁለተኛ አንዳንድ ሚስጥሮች የንግሥቲቷ የቅርብ ሰው የሆነች ሴት ባሳተመችው መጽሀፍ ላይ ይፋ ሆነዋል።
አንጄላ ኬሊ የእንግሊዟ ንግሥት ልብስ አዘጋጅና የቅርብ ወዳጅ ስትሆን፣ ለዓመታት በቤተ መንግስት ያሳለፈችውን ጊዜ በመጥቀስ በርከት ያሉና ለህዝብ እስካሁን ይፋ ያልሆኑ እውነታዎችን ለንባብ አብቅታለች።
ምንም እንኳን እንዲህ አይነት መረጃዎችን ለህዝብ ይፋ ለማድረግ ከንጉሣዊ ቤተሰቦቹ ፈቃድ ማግኘት ከባድ ቢሆንም ኬሊ ግን ከንግሥቲቷ ይሁንታ ማግኘቷ ነው የተገለጸው።
ለመሆኑ ይፋ የሆኑት መረጃዎች የትኞቹ ናቸው?
1. ንግሥቲቱ ጫማ የሚለካላቸው ሰው አላቸው
እ.አ.አ. ከ2002 ጀምሮ የንግሥቲቱን ልብሶች ታዘጋጅ የነበረችው ኬሊ በመጽሀፏ ላይ እንደገለጸችው ንግሥት ኤልሳቤጥ የሚለብሷቸው ጫማዎች በእግራቸው ልክ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ጫማዎቹን በእግሯ የምትለካ ሴት አለቻቸው። ይህች ሴት ደግሞ ራሷ ኬሊ ናት።
''ንግሥቲቷ ለራሷ የሚሆን ጥቂት ጊዜ ነው ያላት፤ በዚህ ምክንያት ሁሉንም ጫማዎቿን ተጫምታ ለመለካት ትቸገራለች። እኔና ንግሥቲቱ ተመሳሳይ የእግር መጠን ስላለን ጫማዎቿን እለካላታለሁ'' ብላለች መጽሀፏ ላይ።
2. ንግሥቲቱ በ 2012ቱ የለንደን ኦሎምፒክ ስለነበራቸው ተሳትፎ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኬሊ እንደምትለው ንግሥቲቱ ወደ ለንደን ኦሎምፒክ መክፈቻ ለመግባት ከ'ጀምስ ቦንድ' ፊልም ተዋናዩ ዳንኤል ክሬግ ጋር ለመስራት አላቅማሙም ነበር።
''በአምስት ደቂቃ ውስጥ ነበር እሺ ያለችው'' ትላለች ኬሊ።
በመቀጠልም ለመክፈቻው ተብሎ በተሰራው አጭር ፊልም ላይም ተዋናዩ ቤተ መንግሥት ወደሚገኘው ክፍላቸው ሲገባ የሚናገሩትን ነገር ራሳቸው ወስነዋል። ፊልሙም ላይ ''እንደምን አመሸህ ሚስተር ጄምስ'' ነበር ያሉት።
አጭሩ ፊልም ከቤተ መንግሥት የተነሱት ንግሥቲቱ ከጄምስ ቦንድ ጋር በመሆን በሄሊኮፕተር ለንደንን ከዞሩ በኋላ ስቴዲየም ሲደርሱ በፓራሹት እንደዘለሉና ህዝቡን እንደተቀላቀሉ ያሳያል። ነገር ግን በፓራሹት የዘለሉት ንግሥቲቱ ሳይሆኑ እርሳቸውን መስላ የቀረበች አንዲት ሴት ነበረች።
3. ንግሥቲቱ በየዓመቱ የሚታደሙት የፈረስ ውድድር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ንግሥቲቱ በየዓመቱ የማይቀሩበት የ'ሮያል ስኮርት' የፈረስ ውድድር በጣም በጉጉት የሚጠበቅ ትዕይንት ነው። ተመልካቾች ደግሞ በፈረሶቹ ውጤት ላይ ብቻ ሳይሆን በንግሥቲቱ የባርኔጣ ቀለም ላይም ጭምር ነው የሚወራረዱት።
ይህንን የተረዱት ንግሥቲቱ በአንደኛው ዓመት ላይ ኬሊ ከአወራራጅ ድርጅቶች ጋር እንድትነጋገርና ዜጎች ቀድመው በባርኔጣቸው ቀለም ላይ የሚወራረዱበት ጨዋታ እንዲዘጋ እንድታስደርግ ነግረዋታል።
በተጨማሪም ተሳታፊዎች ቀድመው የንግሥቲቱን የባርኔጣ ቀለም ለማወቅ እንዳይሞክሩ የማሳሳቻ ሌላ ባርኔጣ እስከማዘጋጀት መድረሳቸውንም ኬሊ ገልጻለች።
4. ሚሸል ኦባማን ያቀፉበት አጋጣሚ
እ.አ.አ. በ2009 ዓ.ም. ንግሥት ኤልሳቤጥ የቀድሞዋ የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማን ማቀፋቸው ከፕሮቶኮል ውጪ ነበር ብለው ብዙዎች መዘገባቸውን ኬሊ ታስታውሳለች።
'' እውነታው ንግሥቲቱ ለቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማ የነበራቸውን ቅርበትና ወዳጅነት ለመግለጽና እንደሚያከብሯት ለማሳየት ነው ያቀፏት። በእንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ውስጥ ደግሞ ፕሮቶኮል ብሎ ነገር የለም። የተሰማቸውን ነው ያደረጉት'' ብላለች።
5. የንጉሣዊያን ቤተሰብ ልጆች በጥምቀታቸው ስለሚለብሱ ገዋን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኬሊ እንደምትለው አዲስ የተወለዱ የንጉሣዊያን ቤተሰብ ልጆች በጥምቀታቸው ወቅት የሚለብሱትን ልብስ ለማቅለም ጠንካራ ጥቁር የሻይ ቅጠል ጥቅም ላይ ይውላል።
''ጋወኑ እውነተኛና ትክክለኛው ቀለም እንዲይዝ ከዮርክሻየር የመጣ የሻይ ቅጠል እንጠቀማለን''
''እያንዳንዱን የህጻናት ጋወን በሻይ ቅጠል ውሃ በተሞላ ትንሽ ጎድጓዳ ሰሀን ውስጥ አድርገን ለአምስት ደቂቃ እንተወዋለን። ትክክለኛው ቀለም እስኪመጣም ቶሎ ቶሎ እንከታተለዋለን'' ብላለች።












