ድካምና የአቅም ማነስ ይሰማዎታል? እነሆ ምክንያቱና መፍትሄው

የደከማት ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከአምስት ሰዎች አንዱ ባልተለመደ መልኩ ለረዥም ሰዓታት የድካም ስሜት የሚያጋጥመው ሲሆን ከአስር ሰዎች አንዱ ደግሞ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ የሰውነት መዛልና ከፍተኛ ድካም እንደሚሰማቸው የእንግሊዙ ሮያል የሥነ ልቦና ኮሌጅ መረጃ ይጠቁማል።

ነገሮችን አስገራሚ የሚያደርገው ደግሞ ድካምና የሰውነት መዛል ከሰው ልጆች ታሪክ ጋር አብረው የቆዩ ቢሆኑም ምክንያታቸው ምን እንደሆነ ለመረዳት ብዙም ጥረት አልተደረገም።

አዲስ እየተሰሩ ያሉ ጥናቶች ደግሞ እነዚህ ስሜቶች ከምንበላው ምግብ ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት እንዳላቸው ማሳየት ጀምረዋል።

የአይረን (ብረት) እጥረት ጉዳቱ ምንድነው?

የአይረን እጥረት በዓለማችን ሁሉም ክፍሎች የተለመደ የአመጋገብ ሥርዓት ችግር ነው። ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነው የዓለማችን ህዝብ የአይረን እጥረት እንዳለበት የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

የእንግሊዝ ብሔራዊ የአመጋገብ እና ሥነ ምግብ ጥናት ማዕከል የሰራው ጥናት እንደሚያሳየው እድሜያቸው ከ11 እስከ 18 ከሆኑ ታዳጊ ሴቶች 48 በመቶ፣ ከ19 እስከ 64 ከሚሆኑ ሴቶች 27 በመቶ እንዲሁም እድሜያቸው ከ11 እስከ 18 ከሚሆኑ ታዳጊ ወንዶች ደግሞ ከአስሩ አንዱ ዝቅተኛ የሆነ የአይረን መጠን አካላቸው ያገኛል።

ለመሆኑ የአይረን እጥረት እንዴት ከአቅም ማነስ ጋር ይገናኛል?

ደማችን ከቀይ ደም ህዋሳት፣ ከነጭ ደም ህዋሳት፣ ከፕላዝማ እና ከፕላትሌትስ የተሰራ ነው። ቀይ የደም ህዋሳት ደግሞ በመላው ሰውነታችን ለሚገኙ ክፍሎች ኦክስጂን ማመላለስ ዋነኛ ተግባራቸው ነው።

እነዚህ ቀይ የደም ህዋሳት የሚመረቱት በአከርካሪ አጥንታችን ውስጥ ሲሆን በቀን በሚሊየኖች ይመረታሉ።

ቀይ የደም ህዋሳት በደማችን ውስጥ የሚቆዩት እስከ 120 ቀናት ድረስ ብቻ ስለሆነ በየጊዜው መቀየር ያስፈልጋቸዋል። የአከርካሪ አጥንታችን ደግሞ እነዚህን ቀይ የደም ህዋሳት በየቀኑ በብዛት ለማምረት አይረን እንዲሁም እንደ ፎሊክ አሲድና ቢ12 ያሉ ቫይታሚኖችን በበቂ ሁኔታ ማግኘት አለበት።

ስለዚህ የአይረን እጥረት ቀይ የደም ህዋሳት ቁጥር ትንሽ እንዲሆን ያደርጋል። ይህ ደግሞ በሰውነታችን ውስጥ የኦክስጅን ስርጭትን በእጅጉ ስለሚቀንሰው አብዛኛዎቹ የሰውነታችን ክፍሎች ይዳከማሉ።

ቀይ የደም ህዋስ እጥረት አኒሚያ የተባለ የጤና እክልን ያስከትላል። አኒሚያ አነስተኛ ቀይ የደም ህዋሳት ቁጥር ሲኖር አልያም በቀይ የደም ህዋሳት ውስጥ የሚገኘው ሄሞግሎቢን መጠን ዝቅ ሲል ይከሰታል። ሄሞግሎቢን ደግሞ በሰውነታችን ውስጥ የኦክስጂን ስርጭትን ይቆጣጠራል።

ስለዚህ አኔሚያ ድካምንና የአቅም ማነስ፣ ማዞር፣ የትንፋሽ ማጠር እንዲሁም የልብ በፍጥነት መምታትን ያስከትላል።

አንድ ሰው አኒሚያ ሲኖርበት ቀይ የደም ህዋሳት ከሌላ ጊዜው በተለየ የስፋት መጠናቸው ስለሚጨምር ከአከርካሪ አጥንት ወጥተው ወደ ሰውነታችን ለመሰራጨት ይቸገራሉ።

ምናልባት አኒሚያ ከአመጋገብ ጋር ብቻ ላይገናኝ ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን በሰውነታችን ውስጥ የአይረን መጠንን ከፍ የሚያደርጉ ምግቦችን ማዘውተር ጠቃሚ ነው።

በአይረን የበለጸጉ ምግቦች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ምግባችን ውስጥ የአይረን መጠንን ከፍ ማድረግ ለሰውነታችን ተጨማሪ ኃይልና ጉልበት እንደሚሆነው የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የእንግሊዝ የህክምና ጥናት ማዕከልና የእንግሊዝ የማህበረሰብ ጤና አገልግሎት በጋራ እንደገለጹት፤ ይህ የድካምና አቅም ማነስ ችግር ከአይረን እጥረት ጋር እንደሚያያዝ ብዙዎች አይረዱም። በተለይ ደግሞ ልጅ የሚወልዱ እና ለመውለድ እድሜያቸው የደረሰ ሴቶች ለዚህ በእጅጉ የተጋለጡ ናቸው።

ምንም እንኳን ዝቅተኛ የአይረን መጠን በብዛት ሴቶች ላይ የሚስተዋል ችግር ቢሆንም እድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ ወንዶች ተጋላጭነት በእጅጉ ከፍ ያለ ነው።

ይህ ማለት ግን የአቅም ማነስና የድካም ስሜት የሚያጠቃው ማንኛውም ሰው አይረን መውሰድ አለበት ማለት ነው?

መልሱ ሁሌም ላይሆን ይችላል ነው። ዋናውና የመጀመሪያው ጉዳይ መሆን ያለበት የህክምና ባለሙያን ማማከር ነው። ምክንያቱም ያለ ህክምና ባለሙያ ምክር አይረንን መውሰድ ሌላ የጎንዮሽ ችግር ሊያስከትል ይችላል።

ስለዚህ የአይረን መጠናችንን ከፍ ለማድረግና የድካም ስሜትን ለመቀነስ ምን አይነት ምግቦች ማዘውተር አለብን?

ቀይ ሥጋ፣ የዶሮ ሥጋ፣ ዓሳ፣ ጥራጥሬዎች፣ አፕል፣ ቦለቄ፣ የዱባ ፍሬ እና የመሳሰሉ ምግቦች ከፍተኛ የአይረን ክምችት ስላላቸው እነሱን አዘውትረን በአመጋገባችን ውስጥ ማካተት ጠቃሚ ነው።

የቫይታሚን ዲ፣ የቫይታሚን ኤ እና የቫይታሚን ቢ12 እጥረት እንዲሁም የዚንክ እጥረት ድካምና የአቅም ማነስን ሊያስከትሉ የሚችሉ ችግሮች ናቸው።