በዩናይትድ ኪንግደም በቋሚነት ለመቆየት ጥገኝነት የሚጠይቁ ስደተኞች 20 ዓመት እንዲጠብቁ ሊደረግ ነው

የፎቶው ባለመብት, PA Media
በዩናይትድ ኪንግደም የጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት የሚያገኝ ስደተኞች በአዲሱ ዕቅድ መሠረት በቋሚነት በአገሪቱ ውስጥ ለመኖር ከማመልከታቸው በፊት 20 ዓመታትን መጠበቅ እንደሚኖርባቸው ሰኞ ዕለት ይፋ እንደሚደረግ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትሯ ሻባና ማህሙድ ገለፁ።
በዩናይትድ ኪንግደም አዲስ የተረቀቀው የጥገኝነት ፖሊሲ መንግሥት በትናንሽ ጀልባ ወደ አገሪቱ የሚገቡ እና የጥገኝነት ጠያቂዎችን ቁጥር ለመቀነስ ጥረት እያደረገ ባለበት ወቅት ይፋ የሚሆን ነው።
በዕቅዶቹ መሠረት ጥገኝነት የተሰጣቸው ሰዎች በአገሪቱ ውስጥ በጊዜያዊነት ብቻ እንዲቆዩ የሚፈቀድላቸው ሲሆን፣ የስደተኛ ሁኔታቸውም በየጊዜው እየተገመገመ እና የትውልድ አገራቸው ደህንነቱ የተጠበቀ ነው ተብሎ ሲታመን እንዲመለሱ ይነገራቸዋል።
በአሁኑ ጊዜ የስደተኝነት ቆይታ ለአምስት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን ከዚያ በኋላ ሰዎች በአገሪቱ ውስጥ በቋሚነት ለመቆየት ማመልከት ይችላሉ።
አሁን የአገር ውስጥ ሚኒስትሯ የመጀመሪያውን ጊዜ ከአምስት ዓመት ወደ ሁለት ዓመት ተኩል ለማሳጠር ይፈልጋሉ፤ ከዚያ በኋላ የስደተኞች ሁኔታ በየጊዜው ይገመገማል ብለዋል።
ነገር ግን በዩኬ ውስጥ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት የሚፈጀውን ጊዜ ከአምስት ዓመት ወደ 20 ለማራዘም አቅደዋል።
ማህሙድ ዕሁድ ለታተመው ታይምስ እንደተናገሩት ማሻሻያዎቹ "የተነደፉት ሰዎችን በመሠረታዊነት ወደዚህ አገር ሕገወጥ ስደተኛ ሆናችሁ አትምጡ፤ በጀልባ አትግቡ ለማለት ነው።"
አክለውም "ሕገ ወጥ ስደት አገራችንን ፈተና ውስጥ እየከተታት ነው" ካሉ በኋላ "አገራችንን አንድ ማድረግ የመንግሥት ኃላፊነት ነው" ብለዋል።
"ይህን ካላስተካከልን አገራችን ይበልጥ እየተከፋፈለች የምትሄድ ይመስለኛል" ሲሉ ለጋዜጣው ተናግረዋል።
ይህ የስደተኞች ፖሊሲ የተወሰደው በግራ ዘመም ሶሻል ዲሞክራቶች ከምትመራው ዴንማርክ ሲሆን፣ አገሪቱ በአውሮፓ ካሉ ሌሎች አገር አንጻር በጣም ጠንካራ የሆነ የስደተኞች እና የጥገኝነት ጥያቄ ስርዓት አላት።
በዴንማርክ ውስጥ ስደተኞች ለሁለት ዓመታት ብቻ የሚቆይ ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ ይሰጣሉ፤ እናም በመጨረሻም የጥገኝነት ጊዜያቸው ሲያበቃ እንደገና ማመልከት ይጠበቅባቸዋል።
እና የዩኬ አገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትሯ አዲሱ አካሄድ፣ ከአንዳንድ የሌበር ፓርላማ አባላት ተቃውሞ እንደሚገጥመው ጥርጥር የለውም።
የሊበራል ዲሞክራት የአገር ውስጥ ጉዳይ ቃል አቀባይ ማክስ ዊልኪንሰን "መንግሥት በኮንሰርቫቲቮች የተፈጠረውን ስርዓት የለሽ የጥገኝነት ስርዓት ለማስተካከል አዳዲስ መንገዶችን መመልከቱ ትክክል ነው" ብለዋል።
አክለውም ሌበር "እነዚህ እርምጃዎች የጥገኝነት ጥያቄዎችን በፍጥነት የማስኬድ ሌላ አማራጭ መሆናቸውን መካድ የለበትም፤ ስለዚህ እዚህ የመኖር መብት የሌላቸውን እናስወግዳለን በሚል ራሱን መሸንገል የለበትም"
የስደተኞች ካውንስል ዋና ስራ አስፈፃሚ ኤንቨር ሰሎሞን የመንግሥትን ዕቅዶች "ጨካኝ እና አላስፈላጊ" ሲሉ ገልጸው "በአስከፊ ጦርነቶች መካከል የቤተሰብ አባላቶቻቸው ሲታሰሩ፣ ሲሰቃዩ ወይም ሲገደሉ ያዩ ስደተኞች አይመለሱም" ብለዋል።















