ዩኬ ጥገኝነት ጠያቂዎችን በወታደራዊ ካምፖች እንደምታቆይ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ዩናይትድ ኪንግደም ጥገኝነት ጠያቂዎችን በወታደራዊ ካምፖች ልታቆይ እንደምትችል ተገለጸ።
'ዘ ታይምስ' እንደዘገበው በስኮትላንድ እና በደቡባዊ ኢንግላንድ ባሉ ወታደራዊ ካምፖች ጥገኝነት ጠያቂዎችን ለማቆየት ውይይት ተጀምሯል።
ከዚህ ቀደም ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳያቸው ውሳኔ እስከሚያገኝ በሆቴል ይኖሩ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር፤ የአገር ውስጥ ጉዳይ እና የመከላከያ ሚኒስቴር አመራሮች ወታደራዊ ካምፖችን በአፋጣኝ ለጥገኝነት ጠያቂዎች ማቆያ እንዲያዘጋጁ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ቢቢሲ መረዳት ችሏል።
ጥገኝነት ጠያቂዎችን በሆቴል ማቆየት በቢሊዮን ፓውንድ የሚቆጠር ገንዘብ ስለሚያስወጣ አሠራሩን ለማስቀረት የዩኬ መንግሥት ወስኗል።
ፀረ ስደተኞች ተቃውሞዎች የሚካሄዱት በእነዚህ ሆቴሎች አቅራቢያ ነው።
በቀጣዩ ወር መጨረሻ ጥገኝነት ጠያቂዎችን በስኮትላንድ፣ ኢንቨርነስ ከተማ ወደሚገኘው ካሜሩን ባራክስ ወታደራዊ ካምፕ እና በምሥራቅ ሰሴክስ ወደሚገኘው ክሮውቦሮው ወታደራዊ ማሠልጠኛ ካምፕ ለመውሰድ ዕቅድ ተይዟል።
የዩኬ መንግሥት የኢንዱስትሪ ዞኖች እና ሌሎች ጊዜያዊ መጠለያዎችን ለመጠቀም አቅዷል።
የቢቢሲ ምንጮች እንደገለጹት፤ ማቆያዎቹ ከጤና እና ደኅንነት አንጻር ደረጃቸውን የጠበቁ ይሆናሉ።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ቃል አቀባይ፤ "ሕገ ወጥ ስደተኞች ሆቴል መቆየታቸው አስቆጥቶናል። መንግሥት ለስደተኞች የተዘጋጁ ሆቴሎችን ባጠቃላይ ይዘጋል። ለስደተኞች የሚወጣውን ገንዘብ ለመቀነስ እና ማኅበረሰቡ ላይ የሚደርሰውን ጫና ለማቃለል ሌሎች አማራጭ ማረፊያዎች ይዘጋጃሉ" ብለዋል።
አሁን ሰዓት በሆቴሎች ተጠልለው የሚገኙ ጥገኝነት ጠያቂዎች ብዛት ወደ 32,000 ይደርሳል።
እአአ በ2023 የስደተኞቹ ቁጥር 56,000 ደርሶ ነበር።
የዩኬ የአገር ውስጥ ጉዳይ እንዳለው፤ ጥገኝነት ጠያቂዎችን በሆቴል ለማቆየት የተወሰነው ሌሎች ማረፊያዎችን ለማዘጋጀት የወጡ ኮንትራቶች "ጉድለት ስለተገኘባቸው" እና አሠራሩም "ደካማ" ስለሆነ ነው።
በዚህ ምክንያት ለጥገኝነት ጠያቂዎች ማቆያ የሚወጣው ገንዘብ 15 ቢሊዮን ፓውንድ ደርሷል።
ጠቅላይ ሚኒስተር ስታርመር ሁሉንም የጥገኝነት ጠያቂዎች ሆቴሎች ለመዝጋት "ቁርጠኛ ነን" ብለዋል።
"የቀደመው መንግሥት ይሄንን ሁሉ ምስቅልቅል ትቶልን መሄዱ ምን ያህል እንደሚያናድደኝ ልነግራችሁ አልችልም" ሲሉም አክለዋል።
ቀድሞ ወታደራዊ ካምፕ የነበሩ ሁለት ማቆያዎች ጥገኝነት ጠያቂዎችን ማስተናገድ ጀምረዋል። እነዚህም በኬንት የሚገኘው ናፒር ባራክስ እና በሰሴክስ የሚገኘው አርኤኤፍ ናቸው።















