በዩኬ ጥገኝነት የሚያገኙ ስደተኞች የቆይታ ጊዜ የተገደበ ሊሆን ነው

የፎቶው ባለመብት, PA Media
በዩናይትድ ኪንግደም የጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያገኘ ስደተኞች በአገሪቱ በቋሚነት እንዳይቆዩ እንደሚደረግ ተገለጸ።
ይህ ጉልህ የፖሊሲ ለውጥ የፊታችን ሰኞ በአገር ውስጥ ሚኒስቴሯ ሻባና መሕሙድ በኩል በምክር ቤት ይፋ ይደረጋል።
በፖሊሲው መሠረት፤ ጥገኝነት ያገኙ ስደተኞች በዩኬ ለወሰነ ጊዜ ብቻ የሚቆዩ ይሆናል።
ዩኬ ጥገኝነት ጠያቂዎችን በዘላቂነት የምታኖርበት አሠራር ሊለወጥ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፤ የፖሊሲ ለውጥ የተደረገው በጀልባ የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ ነው ተብሏል።
የጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያገኘ ሰዎች አገራቸው መመለስ አስጊ አይደለም ተብሎ በሚታመንበት ወቅት ላይ ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ይደረጋል።
አሁን ላይ ዩኬ ለጥገኝነት ጠያቂዎች የአምስት ዓመት የቆይታ ጊዜ ትፈቅዳለች። ከዚያም ስደተኞች በዩኬ በዘላቂነት ለመቀጠል ማመልከት ይችላሉ።
ዩክሬናውያን ስደተኞች ለሦስት ዓመት እንዲቆዩ ከተደረገ በኋላ ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ ይፈቀድላቸዋል።
የመንግሥት ውስጥ አዋቂዎች የፖሊሲ ለውጡን "ትልቅ" ሲሉ ገልጸውታል። ፖሊሲው የተወሰደው ከዴንማርክ ነው።
የዴንማርክ ግራ ዘመም ሶሻል ዴሞክራት መንግሥት በአውሮፓ ጠንካራውን የስደተኞች ፖሊሲ በመተግበር ይታወቃል።
ጥገኝነት ጠያቂዎች የሁለት ዓመት የመኖሪያ ፈቃድ ከተሰጣቸው በኋላ በድጋሚ ማመልከት አለባቸው። ዜግነት ለማግኘት ያለው ሒደት ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ፈታኝ እየሆነ መጥቷል።
የዴንማርክን አሠራር ያደነቁት የዩኬ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር፤ በምርጫ ወቅት የተሻለ የሕዝብ ድምጽ ያስገኘ አካሄድ ነው ሲሉም አሞካሽተውታል።
የዩኬ ሌበር ፓርቲ ጠንካራ እርምጃ ካልወሰደ "የጨለማ ኃይሎች ይወርሱናል" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ዴንማርክ ስደተኞች ቤተሰቦቻቸውን የሚወስዱበትን ሒደት በማራዘም የምትታወቅ ሲሆን፤ ይህ አሠራርም በአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ተወድሷል።
ዩኬ ለስደተኞች ያላት መልካም አቀባበል በጀልባ ወደ አገሪቱ የሚገቡ ጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን ገልጸዋል።
"ከአደጋ ለሚሸሹ ሰዎች ከለላ መስጠታችንን እንቀጥላለን። ግን ሥርዓት ማስጠበቅ አለብን" ሲሉም በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ጽፈዋል።
የዴንማርክን አሠራር የሚተቹ ጥቂት አይደሉም። 200 ስደተኞችን ወደ ሶርያ ለመመለስ ማቀዷ አወዛጋቢ እንደነበር ይታወሳል።
የሌበር ፓርቲ ተወካይ ክሌቭ ሉዊስ "አገሪቷን ወደተካረረ ቀኝ ዘመምነት እየወሰዷት ነው" ብለዋል።
ሌላኛው የፓርቲው ተወካይ ናዲያ ዋቶም "በፖለቲካም በሞራልም ተቀባይነት የሌለው ነው" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ቀኝ ዘመሙ የዩኬ ፓርቲ ሪፎርም ዩኬ፤ ለጥገኝነት ጠያቂዎች ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ከመስጠት ይልቅ የመጡበትን መንገድ ተከትሎ ወደየአገራቸው መመለስን ይመርጣል።
ወግ አጥባቂው ኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ በበኩሉ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ ሐሳብን የሚደግፍ ሲሆን፤ ሌበር ፓርቲ ግን ሐሳቡን ውድቅ አድርጓል።
የአገር ውስጥ ሚኒስቴሯ ሻባና መሕሙድ ሰኞ ዕለት በሕዝብ ተወካዮች ፊት ቀርበው አዲሱን ፖሊሲ ሲያቀርቡ የአገሪቱ ድንበር "ከቁጥጥር ውጪ ሆኗል" ብለው እንደሚከራከሩ ይጠበቃል።















