"እናቴ የልጅ ልጇ ክርስትና ላይ እንዳትገኝ ቪዛ ተከለከለች" -ቱቱ መላኩ

ብሪታኒያዊት ሴት በእድሜ የገፉት እናቷ የልጅ ልጃቸው ክርስትና ላይ እንዳይገኙ ቪዛ መከልከላቸው "ኢፍትሃዊነት" ነው አለች።
ሬዲንግ የምትኖረው ቱቱ መላኩ እናቷን ከኢትዮጵያ እአአ ጥር 10 ወደ ዩኬ ለማምጣት ዕቅድ ነበራት።
ቱቱ በዩናይትድ ኪንግደም መኖር ከጀመረች 30 ዓመት የሞላት ሲሆን የራሷን ምግብ ቤት ከፍታ እየሰራች ትገኛለች።
እናቷ ቪዛ የተከለከሉበትን ምክንያት በሚመለከት ከባለሥልጣኖች ያገኘችው ምላሽ "ተመልሰው እንደሚሄዱ ምንም ማረጋገጫ የለም" የሚል ነው።
ቢቢሲ ከአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ ለማግኘት ቢሞክርም ለጊዜው አልተሳካለትም።
ቱቱ ለቪዛ 134 ፓውንድ የከፈለች ሲሆን ማመልከቻዋ ውድቅ መደረጉን እና ውሳኔው ዳግም እንዲታይላት የምታመለክትበት ምንም ምክንያት እንደሌለ ተነግሯታል።
መገናኛ ብዙኃን "ወደዚህ አገር ቤተሰቤን እንዳመጣ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበራቸው" የምትለው ቱቱ፣ አክላም "አውቃለሁ ወደዚህ አገር የሚመጣ ሁሉ ተመልሶ መሄድ እንደማይፈልግ የሚረዱትም በመገናኛ ብዙኃን ምክንያት መሆኑ ይገባኛል" ብላለች።
ቱቱ በሬዲንግ ፓልመር ፓርክ የኢትዮጵያ ምግብ ቤት ያላት ሲሆን ከዚህ በፊት ለማኅበረሰቡ ባበረከተችው አስተዋጽኦ ተሸላሚ ሆና ነበር።
"የራሴ ሥራ አለኝ፤ በማኅበረሰቡ የተሸለምኩ ነኝ፤ ሕጉን አክብሬ ነው የምኖረው። ይገባኛል ምን እየሰራሁ እንደምኖር አያውቁኝም። ነገር ግን ሰነዶችን በሙሉ አስገብቻለሁ፤ ማን እንደሆንኩ ከዚያ ማረጋገጥ ይችሉ ነበር።"
የብሪታኒያ ዜግነት ያላት ቱቱ የሁለት ልጆች እናት ስትሆን ልጆቿን ያሳደገችውም ያስተማረችውም ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ መሆንን በመግለጽ "ይህ ቤቴ ነው" ትላለች።
"ብሪታኒያዊ ነን፤ እኔ ደግሞ በተለየ፣ ብሪታኒያዊ በመሆኔ ኩራት ይሰማኛል" ብላለች።
እናቷ አፍሪካ ውስጥ "ትልቅ ቤተሰብ" እና ጓደኞች ያሏቸው መሆናቸውን ገልጻ ወደ እንግሊዝ የምትመጣ ከሆነ ያንን ማኅበረሰብ እንደማታገኝ ገልጻለች።
ቱቱ እናቷ ወደ ዩኬ አራት ጊዜ መጥተው መመለሳቸውን በመናገር "የልጅ ልጇን መጥቶ ለማየት የ10 ቀን ቪዛ ለመስጠት ነው የከለከሉት" ስትል ለቢቢሲ አስረድታለች።
"መምጣት አለባት ምክንያቱም ይህ ኢፍትሃዊነት ነው።"
ቱቱ መላኩ ለአካባቢው የምክር ቤት ተወካይ ጉዳይዋን ማስረዳቷን ጨምራ ገለጻለች።
የአካባቢው ተወካይ የሆኑት የምክር ቤት አባል ማት ሮዳን ቢቢሲ ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም።















