ዩኬ ሕገወጥ ስደተኞች በፍጥነት ከአገር የሚወጡበትን ስርዓት ልታስተዋውቅ ነው

በጀልባ የሚጓዙ ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ, የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት በአነስተኛ ጀልባዎች ወደ አገሪቱ የሚገቡ ሕገወጥ ስደተኞችን ቁጥር መቀነስ ይፈልጋል

የዩናይትድ ኪንግደም የጥገኝነት ስርዓት ላይ ከፍተኛ ለውጦች የማድረግ እቅድ ያላቸው የአገር ውስጥ ሚኒስትሯ ሻባና ማሃሙድ፣ ወደ አገሪቱ የሚገቡ ሕገ ወጥ ስደተኞችን በፍጥነት ወደ መጡበት መመለስ የሚያስችል ዕቅድ ሊያስተዋውቁ ነው።

ሚኒስትሯ፤ ዛሬ ለሕዝብ እንደራሴዎች በሚያቀርቡት መግለጫ ላይ ሕገወጥ ስደተኞች ከአገር እንዲወጡ ከመደረጉ በፊት በተደጋጋሚ ይግባኝ የሚሉበት መንገድ የሚያበቃበትን ዕቅድ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከሰብዓዊ መብቶች ጋር የተያያዙ ሕጎች ማሻሻያዎችንም በተመሳሳይ ያቀርባሉ።

የጥገኝበት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያገኘ ስደተኞች የመኖሪያ ፈቃድ የሚሰጣቸው በጊዜያዊነት ብቻ እንደሚሆን የተገለፀ ሲሆን የመጡበት አገር ደህንነቱ የተጠበቀ ነው ተብሎ ከታመነ እንዲመለሱ ይደረጋል።

በተጨማሪም ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በቋሚነት ለመኖር ለማመልከት 20 ዓመት መቆየት ይጠበቅባቸዋል።

መሃሙድ፤ የአንጎላ፣ ናሚቢያ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግሥታት የሚባረሩ ስደተኞችን መቀበልን በተመለከተ ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያሻሽሉ አሳስበዋል። እነዚህ አፍሪካውያን አገራት ይህንን ማስተካከያ የማያደርጉ ከሆነ ለዜጎቻቸው ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የሚያስገባ ቪዛ መስጠት እንደሚያቆሙ ማስጠንቀቂያ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ማሃሙድ፤ "ለእኔ ይህ የሞራል ተልዕኮ ነው። ምክንያቱም ሕገ ወጥ ስደት አገራችንን ሲለያያት እያየሁ ነው፤ ማኅበረሰቦችን እየከፋፈለ ነው" ሲሉ እሁድ ዕለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለዚህ ሀሳብ ድጋፋቸውን የገለጹት በምክር ቤቱ የወግ አጥባቂ ፓርቲ ትይዩ አገር ውስጥ ሚኒስትር ክሪስ ፊሊፕ፤ የጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያላገኘ ስደተኞች "በአንድ ሳምንት ውስጥ" ከአገር እንዲወጡ በመጠየቅ እቅዱን ይበልጥ አጠንክረዋል።

ዕቅዱ ከተወሰኑ የሌበር ሕዝብ እንደራሴዎች ትችት ያስተናገደ ሲሆን፣ ራቼል ማስኬል መንግሥት በስደተኝነት ላይ "ሙሉ በሙሉ በተሳሳተ አቅጣጫ እየተጓዘ ነው" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት በአነስተኛ ጀልባዎች ወደ አገሪቱ የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ይፈልጋል።

ከዚህም በተጨማሪ የጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያላገኘ እንዲሁም በተለያየ ወንጀል ተሰማርተው የተገኙ ስደተኞች በፍጥነት ወደ መጡበት እንዲመለሱ ማድረግ ይፈልጋል።

የጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያገኘ ስደተኞችም ቢሆኑ በቋሚነት ለመኖር የሚያስችላቸውን ቅድመ ሁኔታ እንዲጠብቅ ማድረግ የዕቅዱ አካል ነው።

በዕቅዶቹ መሠረት ስደተኞቹ የጥገኝነት ጥያቄያቸው ውድቅ ሲደረግ ይግባኝ ማለት የሚችሉት አንድ ጊዜ ብቻ እንዲሆን ተወስኗል። በድጋሚ የሚቀርበው ጥያቄ ተቀባይነት ካላገኘም በፍጥነት ከአገር እንዲባረሩ ያደርጋል።

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ለመከተል የሚፈልገው የዴንማርክ የስደተኞች ስርዓትን ነው። ወንጀለኞች እና ጉዳያቸው በይግባኝ ስርዓት ውስጥ ቢያልፍም ተቀባይነት የማግኘት ዕድሉ አነስተኛ የሆነ ስደተኞችን ተከታትሎ ከአገር የሚያስወጣ ነጻ አካል የማቋቋም እቅድም አለው።

ዴንማርክ ውስጥ ስደተኞች ለሁለት ዓመታት ብቻ የሚቆይ ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሚሰጣቸው ሲሆን የጥገኝነት ጊዜያቸው ሲያበቃ እንደገና ማመልከት ይጠበቅባቸዋል።

የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትሯ የሰብዓዊ መብት ሕጎች፣ ቤተሰብ የመመስረት እና የመምራት መብትን የሚያስጠብቀው የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነት (ECHR) አንቀጽ 8ን ጨምሮ በኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ጉዳዮች ላይ የሚተገበርበትን መንገድ ለማሻሻል ይፈልጋሉ።

አንቀጽ 8 መጠቀም የሚችሉት ወላጆቻቸው ወይንም ልጆቻቸው በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ያሉ ጥገኝነት ጠያቂዎች ብቻ ይሆናሉ።

ዩኬ ሰብዓዊ ያልሆነ አያያዝ እና ክብርን የሚነፍግ አያያዝን የሚከላከለውን የሕጉን አንቀጽ 3 ለማሻሻል ከሌሎች አገራት ጋር ትሰራለች ተብሏል።