የነዳጅ ማጣሪያ እና የማዳበሪያ ፋብሪካዎች ግንባታ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስታወቁ

የፎቶው ባለመብት, Abiy Ahmed Ali
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ በሶማሌ ክልል ለሚገነቡት የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ እንዲሁም የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ መሠረተ ድንጋይ መጣሉን አስታወቁ።
በትናንትናው ዕለት ወደ ሶማሌ ክልል ያመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ ሐሙስ መስከረም 22/2018 ዓ. ም. የሁለቱ ፋብሪካዎች ግንባታ መጀመርን አብስረዋል።
በክልሉ ይገነባል የተባለው የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ "ሂላል" ከተባለው የነዳጅ ሥፍራ ድፍድፍ ነዳጅ እንደሚያወጣ፣ እንደሚያጣራ እና እንደሚያጠራቅም ገልጸዋል።
የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካው "በዓመት 3.5 ሚሊዮን ቶን" ነዳጅ አምርቶ የማቅረብ አቅም እንዳለውም በመልዕክታቸው አስፍረዋል። የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ድርጀት ሚገነባው "በጎልደን ኮንኮርድ ግሩፕ" እንደሆነም ጠቅሰዋል።
በሶማሌ ክልል ለዓመታት የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ ሲያካሂድ የነበረው ጎልደን ኮንኮርድ ግሩፕ (ጂሲኤል)፤ በካሉብ እና ሃይላላ ሳይቶች ሲያከናውን የነበረውን ፕሮጀክት መጀመሪያ ምዕራፍ ማጠናቀቁን የገንዘብ ሚኒስቴር በትናንናው ዕለት አስታውቆ ነበር።
ከገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ጋር የተገናኙት የጂሲኤል ግሩፕ ሊቀመንበር ዡ ጎንግሻን፤ ቀጣዩን የኢንቨስመንት ምዕራፍ ዕቅድ እና ገንዘብ ልወጣን በተመለከተ እንደተነጋገሩ ተገልጿል።
በቀጣይም ኩባንያው በነዳጅ ማጣሪያ ልማት እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ የብረት ማቅለጫ ማዕከል ምስረታ ላይ እንደሚሰማራ አስታውቀዋል ተብሏል።
በተመሳሳይ በዛሬው ዕለት መሠረቱ የተጣለው የዩሪያ ማደሪያ ፋብሪካ ደግሞ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና ከዳንጎቴ ግሩፕ ጋር "በመተባበር" የሚገነባ እንደሆነ ዐቢይ ገልጸዋል።
ነሐሴ ወር ሁለቱ አካላት ግንባታውን ለማከናወን በተፈራረሙበት ወቅት ዳንጎቴ ግሩፕ የፋብሪካውን 60 በመቶ ድርሻ እንደሚይዝ፤ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ደግሞ 40 በመቶ ድርሻ እንደሚኖረው ተገልጾ ነበር።
ዐቢይ፤ ለማዳበሪያ በግብአትነት የሚውለው የተፈጥሮ ጋዝ "ከካሉብ የጋዝ ሥፍራ" እንደሚያወጣ አስታውቀዋል።
ፋብሪካው የሚያወጣውን ጋዝ ለማጓጓዝ "108 ኪሎ ሜትር የማጓጓዣ ቱቦ" እንደሚጠቀም እንዲሁም "በዓመት ሦስት ሚሊዮን ቶን" ምርት እንደሚያቀርብ አስታውቀዋል።
የማዳበሪያ ፋብሪካው ግንባታ "ከሦስት ዓመት ብዙም ባልበለጠ" ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ከዚህ ቀደም ተገልጾ ነበር።
"ሁለት አሻጋሪ ፕሮጀክቶች" ሲሉ ፋብሪካዎቹን የጠሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ "ዛሬ ለኢትዮጵያዊያን ሁሉ የሚያኮራ ታሪካዊ ሁነት ተፈፅሟል" ብለዋል።
"እነዚህ ፕሮጀክቶች የኢንዱስትሪ ዕድገትን ከማሳየት በላይ ናቸው። ዕድሎቻችንን የመጠቀም፣ ትብብሮችን የማጠናከር እና ሰላምን የማጽናት የጋራ ኃላፊነታችንን የሚያሳዩ ናቸው" ሲሉም ግንባታቸው የተጀመሩትን ፋብሪካዎች አሞካሽተዋቸዋል።















