ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኮሪደር ልማትን "ሊያጣጥሉ የሚሞክሩ" አገራትን "ሥራችንን ለእኛ ተዉልን" ሲሉ አሳሰቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

የፎቶው ባለመብት, Abiy Ahmed Ali/screenshot

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥታቸው አዲስ አበባን ጨምሮ በበርካታ ከተሞች እያካሄደው ያለውን የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት "ለማጣጣል የሚሞክሩ" ያሏቸውን "አገራት እና ቡድኖች" ተቹ።

ዐቢይ፤ "የእናንተን ሥራ ሥሩ፤ ይሄን ለእኛ ተዉልን" ሲሉም አሳስበዋል።

ዐቢይ ዛሬ ሐሙስ መስከረም 22/2018 ዓ. ም. ከሶማሌ ክልል መዲና ጅግጅጋ ከተማ በቪድዮ ባስላለፉት መልዕክት ላይ የኮሪደር ልማትን "ለማጣጣል የሚሞክሩ" ያሏቸውን "አገራት እና ቡድኖች" ማንነት አልጠቀሱም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህንን የተናገሩት የአሜሪካ መንግሥት በኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ምክንያት "በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን" የሚገልጽ ሪፖርት ካወጣ ከቀናት በኋላ ነው።

የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አመቺነት ሁኔታ የሚዳስሰው እና በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የተዘጋጀው ሪፖርት፤ የኮሪደር ልማት ከንብረት መብቶች ጥበቃ አንጻር ስጋት መደቀኑን አመልክቷል።

አዲስ አበባን ጨምሮ ቢያንስ በ40 ከተሞች እየተካሄደ ባለው በዚህ ፕሮጀክት ምክንያት፤ "በውጭ ዜጎች ባለቤትነት የተያዙ" ቤቶች እና ንግዶች "ጠመንጃ ተደቅኖ" ጭምር "እንዲፈናቀሉ" መደረጉን ይገልጻል።

ከይዞታቸው ያልተነሱ የንግድ ሥፍራዎች ደግሞ "ፊት ለፊት ባሉ መንገዶችን መፍረስ" የተነሳ ሥራቸውን "የማይቻል" ደረጃ ላይ እንደደረሰ እና "ከሥራ እንዲወጡ" እንደተገደዱ ያስረዳል። በኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ምክንያት የታየው ይህ "የማባረር" አካሄድ የባለሀብቶችን በኢትዮጵያ ኢንቨስት የማድረግ "ፍላጎት እንደገደበ" በአሜሪካ መንግሥት የተዘጋጀው ሪፖርት አስፍሯል።

ይህ ሪፖርት ከወጣ ከቀናት በኋላ ወደ ሶማሌ ክልል የተጓዙት ጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ፤ በክልሉ መዲና ጅግጅጋ የተከናወነውን የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት እና የአዳዲስ ቤቶች ግንባታ መጎብኘታቸውን አስታውቀዋል።

በከተማዋ "60 ኪሎ ሜትር መንገድ" እንዲሁም "10 ኪሎ ሜትር የሚጠጉ" የእግረኛ እና የብስክሌት መንገዶች መገንባታቸውን ተናግረዋል። "በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ቤቶች" መገንባታቸውንም አክለዋል።

ዐቢይ፤ "የኮሪደር ልማት ያልነው ሥራ፤ ሥራ በመፍጠር የጭስ አልባውን ኢንዱስትሪ በማነቃቃት፣ የሰዎችን የአኗኗር ዘይቤ በማሻሻል እየተጫወተ ያለው ሚና በጣም በጣም ከፍተኛ ነው" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከባለሥልጣናቶቻቸው ጋር በጅግጅጋ

የፎቶው ባለመብት, Abiy Ahmed Ali

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሶማሌ ክልል ከጎበኟቸው ፕሮጀክቶች አንዱ በገበታ ለአገር አማካኝነት እየተገነባ ያለው ሸበሌ የመዝናኛ ሪዞርት ነው
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

መንግሥታቸው እያከናወነ ያለው "ከተማ የማስዋብ ሥራ"፤ "በሚቀጥሉት ቢበዛ 15፣ 20 ዓመታት የአብዛኛው ማኅበረሰብ የመኖሪያ ሥፍራ ከተማ" እንዲሆን እንደሚያደርግ አስገንዝበዋል።

መንግሥታቸው በከተሞች እያከናወነ ባለው ተግባር "በአፍሪካ ምልክት እና ምሳሌ" ተደርጎ መወሰዱን ተናግረዋል።

"ብዙዎች" የኮሪደር ልማትን "እንደሚጎበኙ" እና "ለመማር ጥያቄ እንደሚያቀርቡ" አክለዋል። ይሁን እንጂ "በተለይ ራቅ ያሉ አካባቢዎች" የሚገኙ "አንዳንድ" አካላት የኮሪደር ልማትን "ድንቅ ሥራ እንደማይቀበሉ" አስረድተዋል።

ዐቢይ፤ "ይህንን ሥራችንን አይተው ሊያጣጥሉ የሚሞክሩ አገራት እና አንዳንድ ቡድኖች ደግሞ፤ የእናንተን ሥራ ሥሩ፤ ይህንን ለእኛ ተዉልን። ይህ አገር ባለቤት አለው. . . ሥራችንን ለእኛ ተዉልን ነው መልዕክቴ" ሲሉ በስም ላልጠቀሷቸው አካላት መልዕክት አስተላልፈዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገላለጽ "አገራት፣ ግለሰቦች እና ቡድኖች" የኮሪደር ልማትን "በደስታ የማያዩት"፤ "ለአፍሪካ፣ ለኢትዮጵያ ያ የጨቀየው፣ ያላማረው ነገር በቂ ነው" ብለው ስለሚያስቡ ነው።

"አንደኛ እነሱም ላይ ጥያቄ እየመጣባቸው ነው። 'እንኳን እናንተ አፍሪካ እንዲህ እያደረገ ነውና ለምን አትሠሩም?' የሚል ጥያቄ አለ፤ በሌላ መንገድ ደግሞ ለእኛ በቂ ነው ብሎ የማሰብ ችግር አለ" ሲሉ ተደምጠዋል።

"ለእንደዚህ አይነቱ" ሐሳብ "ጆሮ መስጠት እንደማያስፈልግም" አክለዋል።

"ለእኛ የሚበጀንን፣ የሚያስፈልገን፣ የሚጠቅመንንን እኛ ነው የምናውቀው" ያሉት ዐቢይ፤ "ከእኛ በላይ የእኛን ልማት የሚያስብ ኃይል አለ ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው" በማለት ተናግረዋል።

መንግሥታቸው በስንዴ ልማት ባከናወነው ተግባር ዓለም አቀፍ ሽልማት ማግኘቱን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ "ሰሞኑን በደረሰኝ ዜና በአረንጓዴ አሻራ እንደዚሁ ከዓለም አቀፍ የተባበሩት መንግሥታት ተቋም ኢትዮጵያ ሽልማት አግኝታለች" ብለዋል።