የኮሪደር ልማት ያስከተለው "መፈናቀል" የባለሀብቶችን "ፍላጎት መገደቡን" የአሜሪካ መንግሥት ሪፖርት አመለከተ

ከቤቶች ከፈረሱበት ስፍራ ቆርቆሮ ተሸክሞ የሚወጣ ወጣት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት በአዲስ አበባ የተጀመረው በ2016 ዓ.ም. ሲሆን ቢያንስ በ40 የአገሪቱ ከተሞች በመካሄድ ላይ ነው

"በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ" ነዋሪዎች እና ንግዶች "በትንሽ ወይም ያለምንም ማስጠንቀቂያ የተባረሩበት" የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት፤ የባለሀብቶችን መዋለ ንዋይ የማፍሰስ "ፍላጎት እንደገደበ" የአሜሪካ መንግሥት ሪፖርት ገለጸ።

ግጭቶችን እና የውጭ ምንዛሬ ተመን ልዩነት "እንደገና መስፋትን" የሚጠቅሰው ሪፖርቱ፤ የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ሁኔታ "ለአሜሪካ እና ሌሎች የውጭ ንግዶች ፈታኝ ነው" በማለት ገምግሟል።

የአሜሪካ መንግሥት ይህንን ግምገማ ያሰፈረው አርብ መስከረም 16/2018 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ዓመታዊ የኢንቨስትመንት ሁኔታ መግለጫ ነው።

የአሜሪካ ኩባንያዎች "በመረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ እንዲያሳልፉ" በሚል በአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የሚዘጋጀው ይህ ሪፖርት፤ ከ170 በላይ የሚሆኑ አገራትን የኢንቨስትመንት አመቺነት ሁኔታ ይዳስሳል።

ኢትዮጵያን የተመለከተው የመስሪያ ቤቱ ሪፖርት በስጋትነት ካነሳቸው ጉዳዮች አንዱ በአዲስ አበባ ተጀምሮ ቢያንስ በ40 የአገሪቱ ከተሞች በመካሄድ ላይ ያለውን የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ነው።

በተለይም የከተሞች ዋና ዋና መንገዶችን ገጽታ ማስዋብ፣ የእግረኛ መንገድን ማስፋት እንዲሁም የመዝናኛ ቦታዎችን መገንባት ላይ የሚያተኩረውን ይህ ፕሮጀክት የተጀመረው የካቲት 2016 ዓ.ም. ነበር።

መንግሥት የኮሪደር ልማት "ኢትዮጵያን በምሥራቅ አፍሪካ ቁልፍ የንግድ እና የሎጂስቲክስ ማዕከል ለማድረግ ያለመ" ፕሮጀክት እንደሆነ ይገልጻል። ፕሮጀክቱ "መሠረተ ልማትን እንደሚያጎለብት" እንዲሁም "ድንበር ተሻጋሪ ንግድን እንደሚያሳልጥም" ያብራራል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሪፖርት በበኩሉ ፕሮጀክቱን የተመለከተው ከነዋሪዎች እና ንግዶች የንብረት መብቶች ጥበቃ ጋር በተያያዘ ነው።

ሪፖርቱ፤ በተከታታይ የተተገበሩት የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች "በውጭ ዜጎች ባለቤትነት የተያዙትን ጨምሮ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን እና የንግድ ድርጅቶችን አባርሯል፤ ንብረቶቻቸውን በትንሽ እና ያለምንም ማስጠንቀቂያ ወይም ካሳ አፍርሷል" ብሏል።

በኮሪደር ልማቱ ምክንያት ከተካሄዱ "መፈናቀሎች መካከል የተወሰኑት ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ እና ጠመንጃ ተደቅኖ" እንደተፈጸሙ "በውጭ ዜጎች ባለቤትነት የተያዙ ቢዝነሶች" መናገራቸውንም ሪፖርቱ ያትታል።

ይህ የፕሮጀክቱ አካሄድ "የባለሃብቶችን ፍላጎት እንደገደበም" ገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ ሕንጻዎች እና መንገዶችን የሚያሳይ ከላይ የተነሳ ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Office of the Prime Minister

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሠረት መሬት የሕዝብ ንብረት መሆኑን የሚጠቅሰው ሪፖርቱ፤ በዚህም ምክንያት ኢንቨስተሮች መሬትን መከራየት እንጂ ባለቤት መሆን እንደማይችሉ ያስታውሳል። ይህ አሰራር "ባለሥልጣናት ለሕዝብ ጥቅም መሬቱን መልሰው እንዲወስዱ ወይም የሊዝ [ስምምነትን] በቁጥጥር ስም እንዲሰርዙ እንዳስቻላቸው" አስፍሯል።

በሪፖርቱ ላይ የተጠቀሰው በቂ ካሳ እና ማስጠንቀቂያ ያለመስጠት ጉዳይ ዓለም አቀፉ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሚያዝያ 2017 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት ላይም የተንጸባረቀ ነው። መንግሥት በበኩሉ የኮሪደር ልማት በተከናወነባቸው አካባቢዎች ለተነሱ ሰዎች ምትክ ቤት እና ቦታ እንዲሁም ካሳ እና መቋቋሚያ መስጠቱን ይገልጻል።

ዓመታዊው የአሜሪካ መንግሥት ሪፖርት በበኩሉ በውጭ ዜጎች ባለቤትነት የተያዙ ንግዶች በፕሮጀክቱ ከይዞታቸው እንዲነሱ ሳይደረግም እንኳ "ቀጥተኛ ባልሆኑ" መንገዶች ስራቸውን ላይ ተጽዕኖ መድረሱን ይጠቅሳል።

የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች "ከንግድ [ቦታዎች] ፊት ለፊት ያሉ መንገዶችን" ማፍረሳቸውን የሚያነሳው የአሜሪካ መንግሥት ሪፖርት፤ ይህም የንግድ ስራን "የማይቻል" እንዳደረገው ያስረዳል። ከዚህም የተነሳ "የንግድ ስራዎች ቀጥታ ባይነኩም እንኳ ከስራ እንዲወጡ" መገደዳቸውን አትቷል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም አንዳንድ የውጭ እና የአገር ውስጥ ባለሃብቶች "ድንገተኛ እና ከፍተኛ የግብር ግመታ ወይም ወደ ኋላ ተመልሶ በሚሰራ አዲስ ሕግ የተነሳ የመጣ የግብር ጥያቄ" እንዳጋጠማቸውን መግለጻቸውን ጠቅሷል።

እነዚህ የግብር ጥያቄዎች የቀረቡት "ያለ በቂ ግልጽነት ወይም አሰራርን ሳይከተሉ" እንደሆነ የሚናገረው ሪፖርቱ፤ "ትርፋቸው በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ" እንዳደረገ እንዲሁም እርምጃው "ቀጥተኛ ያልሆነ መንገድ የባለቤትነት መብት ማሳጣት [ድርጊትን] እንደሚያቋቁም" አስፍሯል።

ሪፖርቱ ስለ ሙስና በሚያብራራበት ክፍሉ ላይም የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ላከናወኑ ኩባንያዎች ኮንትራት የተሰጠትን መንገድ ጠቅሷል። "ከሕግ በተቃረነ መልኩ የኮሪደሩ ልማት ፕሮጀክት የግንባታ ኮንትራቶች ለጨረታ አልቀረቡም፤ ይልቁንም ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ግንኙነት ላላቸው ኩባንያዎች ተሰጥተዋል" ብሏል።

በመሳሪያ የተመታ ታንክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካ መንግሥት ሪፖርት እንደሚያስረዳው ከኮሪደር ልማት በተጨማሪ ግጭቶችም የንብረት መብት ጥሰት አስከትለዋል። በተለይም በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያሉ ግጭቶች "ምግባር የጎደላቸው ባለሥልጣናት ወይም የታጣቂ ቡድን አባላት በተደጋጋሚ ንብረቶችን እንዲነጥቁ" ምክንያት መሆናቸውን ገልጿል።

በሁለቱ ክልሎች የሚገኙ የቱሪስት ሎጅ ባለቤቶች "ንብረቶቻቸው ያለ ምንም ካሳ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት [ማረፊያነት] ተይዘው" እንደነበር መናገራቸውንም አክሏል።

ግጭቶቹ "የእንቅስቃሴ ገደብ" እንዲጣል ማድረጋቸውን እንዲሁም "የመንግሥትን ጣልቃ የመግባት አቅም መገደባቸውንም" ዘርዝሯል። "ወደ ግጭት የመመለስ ስጋትን የደቀነው" እና "እየጨመረ የመጣው" የትግራይ ክልል የፖለቲካ ውጥረትም በተግዳሮትነት ተጠቅሷል።

ሪፖርቱ በተግዳሮትነት የሚጠቅሰው ሌላኛው ጉዳይ "ተመልሶ እየሰፋ" የሚገኘውን የባንክ እና የትይዩ ገበያ (ብላክ ማርኬት) የውጭ ምንዛሬ ተመን ልዩነት ነው። መንግሥት በሐምሌ 2016 ዓ.ም. የውጭ ምንዛሬ ተመን ገበያ መር እንዲሆን መወሰኑ "ኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት መዳረሻ የማድረግ ፍላጎትን እንደ አዲስ ቀስቅሶ" እንደነበር ገልጿል።

ይህ እርምጃ የብርን አቅም በ100 በመቶ ላይ እንዲወድቅ ስላደረገው በባንኮች እና በትይዩ ገበያው መካከል ያለውን የተመን ልዩነት "ለአጭር ጊዜ ዘግቶ" እንደነበር አስታውሷል። ከህዳር 2017 ወዲህ ግን ልዩነቱ እንደገና መስፋት መጀመሩን በመግለጽ በተግዳሮትነት ጠቅሶታል።