በኢትዮጵያ ስለሚገነባው ግዙፍ የማዳበሪያ ፋብሪካ አንዳንድ እውነታዎች

አሊኮ ዳንጎቴ በፋብሪካ ውስጥ ነጭ የሰራተኞች ቆብ አድርገው

የፎቶው ባለመብት, X/@AlikoDangote

የምስሉ መግለጫ, በኢትዮጵያ የሚገነባው የማዳበሪያ ፋብሪካ ላይ የ60 በመቶ ድርሻ ያላቸው አሊኮ ዳንጎቴ

የኢትዮጵያ መንግሥት እና ናይጄሪያዊው ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ በጋራ በአፍሪካ ግዙፍ ከሚባሉት መካከል የሚጠቀስ የማዳበሪያ ፋብሪካ በሶማሌ ክልል ውስጥ ሊገነቡ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ቁልፍ የመዋዕለ ነዋይ ተቋማትን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከዳንጎቴ ግሩፕ ጋር በተፈራረመው ስምምነት ፋብሪካው በሁለቱ ወገኖች የጋራ ድርሻ የሚመራ ነው።

ኢትዮጵያ በየዓመቱ በአማካኝ ከ1.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ የተለያዩ ዓይነት ማዳበሪያዎች ከውጪ አገራት ታስገባለች። ለዚህም ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ የምታወጣ ሲሆን፣ በአገር ውስጥም የማዳበሪያ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን አርሶ አደሮች ይናገራሉ።

ይህ በሶማሌ ክልል፣ ጎዴ ውስጥ የሚገነባው ግዙፉ የማዳበሪያ ፋብሪካ በአፍሪካ ውስጥ ካሉ ተመሳሳይ ፋብሪካዎች በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ውስጥ የሚመደብ ይሆናል።

በዚህ ፋብሪካ ግንባታ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለው ዳንጎቴ ግሩፕ በአፍሪካ ቀዳሚው ባለሀብት የሆኑት የናይጄሪያዊው አሊኮ ዳንጎቴ ንብረት ነው።

ዳንጎቴ ከአፍሪካ ባሻገር በሀብት መጠናቸው በዓለም ላይ ካሉ ጥቁር ባለጸጋዎች መካከል ቀዳሚው ሲሆኑ፣ በፎርብስ መረጃ መሠረት በአሁኑ ወቅት ያላቸው የተጣራ ሀብት 24.9 ቢሊዮን ዶላር ነው።

ዳንጎቴ በኢትዮጵያ ውስጥ በኢንቨስትመንት ሥራ ላይ ሲሳተፉ የማዳበሪያ ፋብሪካው የመጀመሪያው አይደለም። ከአስር ዓመታት በፊት ጀምሮ በሲሚንቶ ማምረት ሥራ ላይ በመሰማራት በዳንጎቴ ሲሚንቶ ባለቤትነት ይታወቃል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥን ያስገኛል ተብለው ከሚታሰቡ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ እንደሆነ የተነገረለት ይህን የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት 2.5 ቢሊዮን ዶላር በጀት ተመድቦለታል።

በሶማሌ ክልል በሚገነባው የማዳበሪያ ፋብሪካ ባለቤትነት 60 በመቶ ድርሻው በዳንጎቴ ግሩፕ የሚያዝ ሲሆን 40 በመቶው ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ድርሻ ይሆናል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና አሊኮ ዳንጎቴ (ከኋላ) በተገኙበት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመን ሆልዲንግስ እና የዳንጎቴ ግሩፕ ተወካዮች የፋብሪካው ግንባታን ስምምነት ሲፈራረሙ

የፎቶው ባለመብት, pm office/fb

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና አሊኮ ዳንጎቴ (ከኋላ) በተገኙበት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመን ሆልዲንግስ እና የዳንጎቴ ግሩፕ ተወካዮች የፋብሪካው ግንባታን ስምምነት ሲፈራረሙ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በዳንጎቴ ግሩፕ መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረትም ሁለቱ ወገኖች ለፋብሪካው ግንባታ በጋራ ገንዘብ ይመድባሉ፣ ይገነባሉ እና ያስተዳድራሉ።

ፋብሪካው እጅግ ዘመናዊ የሆነ የዩሪያ ማዳበሪያ ማምረቻ እና ተያያዥ መሠረተ ልማቶች ስላሉት በዓለም ላይ ካሉት ሁሉ የዘመኑን ቴክኖሎጂ የሚጠቀም ያደርገዋል።

ከሦስት ዓመት ብዙም ባልበለጠ ጊዜ ግንባታው ይጠናቀቃል የተባለው ፋብሪካው ሥራ ሲጀምር በዓመት እስከ ሦስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የሚደርስ ዩሪያ ማዳበሪያ የማምረት አቅም አለው።

ፋብሪካው ለምርቱ ግብዓት በሶማሌ ክልል ውስጥ ከአንድ መቶ ኪሎ ሜትር በማይበልጥ ርቀት ላይ በአቅራቢያው ያለውን የተፈጥሮ ጋዝ የሚጠቀም ሲሆን፣ ይህም በዓለም ላይ ካሉ በአንድ አካባቢ ምርታቸውን ከሚያቀናብሩ ግዙፍ ፋብሪካዎች መካከል አንዱ ይሆናል።

አብዛኞቹ የማዳበሪያ ፋብሪካዎች የምርት ግብዓታቸውን ወደ ተለያዩ ቦታዎች በመውሰድ የመጨረሻውን ምርት የሚያገኙ ናቸው።በዚህም የማጓጓዣ እና ሌሎች ወጪዎች ይጨምርባቸዋል።

ፋብሪካው በሂደት የሚስፋፋ እና አዳዲስ ምርቶችን በማካተት የተለያዩ የማዳበሪያ ምርቶችን በማቅረብ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ የማዳበሪያ ማምረቻ ማዕከል ለማድረግ እንደሚሠራ ተገልጿል።

ፋብሪካው ሥራውን ጀምሮ በሙሉ አቅሙ ሲያመርት በናይጄሪያ ካለው ግዙፉ የማዳበሪያ ማምረቻ ፋብሪካ ጋር እኩል ይሆናል።

ዳንጎቴ ግሩፕ በአፍሪካ ውስጥ በተለያዩ ወሳኝ የኢንደስትሪ ምርቶች ላይ የተሰማራ ግዙፍ መዋዕለ ነዋይ አፍሳሽ ነው።

ዳንጎቴ ሌጎስ አቅራቢያ ናይጄሪያ ውስጥ ያለው እና በአፍሪካ ትልቁ የማዳበሪያ ማምረቻ ፋብሪካ ባለቤት ሲሆን፣ ፋብሪካው በዓመት 3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ዩሪያ ማዳበሪያ ያመርታል።

ከሦስት ዓመታት በኋላ የጎዴው ማዳበሪያ ፋብሪካ ሥራውን ሲጀምር ኢትዮጵያ በአፍሪካ ማዳበሪያ ከሚያመርቱት ናይጄሪያ፣ ታንዛኒያ፣ ሞሮኮ፣ ግብፅ፣ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ ጋር የምትመደብ ትሆናለች።

በተጨማሪም አዲሱ ፋብሪካ ያለው የማምረት አቅም ከፍተኛ ከመሆኑ በተጨማሪ እየተስፋፋ የሚሄድ በመሆኑ በአህጉሪቱ ካሉና በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ሦስት ግዙፍ የማዳበሪያ ፋብሪካዎች መካከል አንዱ ይሆናል።