"የቀይ ባሕር ስህተት. . . ነገ ይታረማል" - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

የፎቶው ባለመብት, PM Office/fb

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቀይ ባሕር ከሰላሳ ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ እጅ እንደነበረ እና "ስህተቱ ነገ ይታረማል" ሲሉ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ላይ በተላለፈ ውይይታቸው ላይ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ ከማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪያቸው ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ እንደተናገሩት በቀይ ባሕር ላይ የተፈጸመው ስህተት እንደሚታረም አመልክተዋል።

"ቀይ ባሕር እኮ የዛሬ 30 ዓመት እኛ እጅ ነበር። ቀይ ባሕር የዛሬ 30 ዓመት የትናንት ታሪክ ነው። የተፈጠረው ስህተት ትናንትና ነው። ነገ ይታረማል፤ ብዙ ከባድ አይደለም" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጳጉሜ 4/2017 ዓ.ም. በሚመረቀውን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ግንባታ ዙሪያ ባደረጉት ውይይት ላይ የሺህ ዓመታት የአባይ ታሪክ እንደተቀየረው ሁሉ ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችበት ሁኔታም እንደሚስተካከል አመልክተዋል።

ኤርትራ ነጻነቷን ስታገኝ ከቀይ ባሕር የተነጠለችው ኢትዮጵያ ከጥቂት ዓመታት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር በኩል የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት እንዳላት ይፋ ካደረጉ በኋላ በኤርትራ በኩል ስጋት ተፈጥሯል።

ይህም ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በሕዳሴ ግድብ ውዝግብ ውስጥ ከምትገኘው ግብፅ ጋር ትብብር መፍጠሯን ተከትሎ ውጥረቱ ተባብሷል።

የሁለቱን አገራት ግንኙነት የበለጠ ያሻከረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "የባሕር በር ለኢትዮጵያ የኅልውና ጉዳይ ነው" ማለታቸውን ተከትሎ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ስለባሕር በር እና ስለወደብ ያደረጉት ንግግር እና ያሳዩት ፍላጎት የኤርትራ ባለሥልጣናትን አላስደሰተም።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን የወደብ ፍላጎትን በተመለከተ "የቀይ ባሕርን ጉዳይ ሳናነሳ በሰላም ቆይተናል እና አሁን ለምን ዝም አንልም? ከኤርትራ ጋር እንዳንጋጭ ቢቀርብንስ? ከጂቡቲ ጋር ብንጋጭስ የሚል ስጋት ያላቸው ሰዎች አሉ" ብለው ነበር።

ለዚህ ጥያቄ መነሳት እንደ ምክንያት የጠቀሱት እየጨመረ የመጣው የኢትዮጵያ የሕዝብ ብዛት የባሕር መተላለፊያ ስለሌለው "የመልክዓ ምድር እስረኛ" ሆኖ መቀጠሉን አመልክተው ነበር።

በቅርቡ ፕራይም ሚዲያ ከተባለ ዩቲዩብ ቻናል ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት በኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር የውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል ተሾመ ገመቹ፣ ኢትዯጵያ የባሕር በር የምትጠይቅበት አራት አሳማኝ ምክንያቶች እንዳሏት ተናግረው ነበር።

ከእነዚህ ምክንያቶች አንዱ ከቀይ ባሕር ጋር ያላት ታሪካዊ ትስስር መሆኑን ያነሱት ጄነራሉ "የታሪክ ትስስር አለን ስንል ይህ ባሕር እኛ ጋር ነበረ። ቀይ ባሕር አሰብ ነው የነበረው። አሰብ ደግሞ እንደምታውቁት ራስ ገዝ ነበረ" ብለዋል።

ጄነራሉ አክለውም ታሪክ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ሕግም ያግዘናል በማለት ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ያላትን ርቀት በአስረጅነት ጠቅሰዋል።

ጄነራሉ ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር በቅርብ ርቀት እንደመገኘቷ የዓለም አቀፍ ሕግም እንደሚደግፋት አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ የባሕር በር ጉዳይ የኅልውና ጉዳይ ነው ያሉትንም በመድገም ጄነራሉ "አሁን ባለው ሁኔታ የኅልውና ጉዳይ ሆኗል" ሲሉ ተናግረዋል።

"ለኩራት ሳይሆን፣ የባሕር በር አለን ብለን ከመናፈቅ ሳይሆን አሁን የኅልውና ጉዳይ ሆኗል።. . . ኅልውና ደግሞ ማንኛውንም ዋጋ የምትከፍልበት ብሔራዊ ፍላጎት ነው" ካሉ በኋላ ይህንን ለማሳካት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የአገር መከላከያ ሠራዊት ጥረት እያደረገ መሆኑን ዘርዝረዋል።

ጄነራሉ በዚሁ ንግግራቸው በሦስተኛነት የጠቀሱት ኢትዮጵያ ያሉባትን ስጋቶች ነው።

"ስጋቶቻችንን በቅርበት ለመቀልበስ ይህ የባሕር በር ያስፈልገናል" ያሉት ሜጀር ጄነራል ተሾመ ገመቹ "ስጋት ሲባል ከውሃ ላይ የሚተኮስ፣ የሚወነጨፍ፣ ረዣዥም ርቀት መሄድ የሚችሉ ከተሞቻችንን፣ ዋና ከተማችንን ሊያሰጉ የሚችሉ" መሆናቸውን በመጥቀስ ይህንን ለመመከት የባሕር በር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቋ ግን የባሕር በር የሌላት አገር የሆነችው ከ30 ዓመት በፊት ኤርትራ ነጻ መውጣቷን ተከትሎ ነው።

ከዚያ በኋላ አገሪቱ ለገቢ እና ለወጪ ንግዷ የትንሿን ጎረቤት አገር ጂቡቲን ወደብ በመጠቀም ላይ ትገኛለች።

የአሰብ ወደብ ኤርትራ ነጻነቷን ስታገኝ የሄደበትን መንገድ የጠቀሱት ጄነራሉ በወቅቱ የነበረው የሽግግር መንግሥት ነው ሲሉ የባሕር በርን ያክል ለመስጠት ሕጋዊ ውክልና እንዳልነበረው ተናግረዋል።

"የሽግግር መንግሥት በሕዝብ ያልተመረጠ መንግሥት የባሕር በር አሳልፎ የመስጠት ማንዴት የለውም።"

ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "ኢትዮጵያ ለቀይ ባሕር ስትል ኤርትራን የመውጋት ፍላጎት የላትም" ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት የኅልውና ጉዳይ ነው ሲሉ ከተናገሩ በኋላ በሁለቱ አገራት መካከል ውጥረት ሰፍኖ ቆይቷል።

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ኢትዮጵያ "ያላት ፍላጎት እንነጋገር ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ "በሰጥቶ መቀበል፣ ሕዝቦች በሚጠቀሙበት እና በገበያ መርኅ እንወያይ. . . ውጊያ አያስፈልግም" ብለው ነበር።

ኤርትራ ግን በተቃራኒው ኢትዮጵያን በጠብ አጫሪነት የወነጀለች ሲሆን፣ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ "ሉዓላዊ የባሕር በር" ማግኘት የሚለው ትኩረት መሳቢያ ሌላ ጂኦፖለቲካዊ ገጽታዎች አሉት በማለት ከዚህ ግድየለሽ ጀብደኝነት ጀርባ ሌሎች ኃይሎች አሉ በማለት ከሰው ነበር።