ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከኢትዮጵያ ጋር ስላለው ውዝግብ እና ሌሎች ጉዳዮች ምን አሉ?

የፎቶው ባለመብት, shabait.com
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ቅዳሜ ሐምሌ 12/9/2017 ዓ.ም. ለአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት የመጀመሪያ ክፍል ቃለ ምልልስ በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግሥት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ የላከውን ደብዳቤ "አስገራሚ የውሸት ክስ" ሲሉ አጣጣሉ።
ፕሬዝደንቱ 'ይህ ርካሽ ውሸት ነው' ሲሉ ያጣጣሉት የኢትዮጵያ መንግሥት ክስ "የብልጽግና ፓርቲ የሚያደርገውን የጦርነት ዝግጅት ለመሸፈን ያቀረበው ርካሽ ውሸት ነው" ብለዋል።
በቅርቡ ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤርትራ ሠራዊት በኢትዮጵያ ድንበር ያሉ አካባቢዎችን ተቆጣጥሮ እንደሚገኝ እና አስከፊ ጥሰቶችን መፈጸም መቀጠሉን በመጥቀስ ከስሳለች።
በዚህ ሁለት ሰዓት በፈጀው ቃለ ምልልስ ላይ ፕሬዘዳንት ኢሳይያስ ስለ ኢትዮጵያ እና የወደብ ጉዳይ፣ ስለ ዓለም አቀፉ የፖለቲካ ሁኔታ፣ በፕሬዝዳንት ትራምፕ የመጀመሪያው የሥልጣን ዘመን የኤርትራ እና የአሜሪካ ግንኙነት መሻሻል፣የጎረቤት አገራት እና ተያያዥ ጉዳዮችን አንስተዋል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በዚህ የመጀመሪያ ክፍል ቃለ ምልልሳቸው ስለ ኤርትራውያን እና የአገር ውስጥ ጉዳይን በተመለከተ ምንም ያነሱት ነገር የለም።
ፕሬዝደንት ኢሳያስ በቃለ ምልልሳቸው ላይ ኢትዮጵያ በብዙ የውስጥ ግጭቶች እና ቀውሶች እየታመሰች ነው ያሉ ሲሆን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ውስጥ የነበረው ብሩህ ተስፋ፣ በግድየለሽነት በንኖ ጠፍቷል ብለዋል።
ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ የተፈጠረውን ነገር ለመረዳት አስቸጋሪ ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ "ለምን በቅን ልቦና አልተተገበረም። በፋኖ ላይ በግድየለሽነት ጦርነት ለምን ተከፈተ?" ሲሉ ጠይቀዋል።
ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የምናየው ግርግር በእውነት ታይቶ የማይታወቅ ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፣ የብልጽግና ፓርቲ በአገር ውስጥ ችግሮቹን ላይ ከማተኮር እና ከመፍታት ይልቅ በኤርትራ ላይ ጦርነት የሚቀሰቅሰው ለምንድን ነው? ሲሉ ጠይቀዋል።
ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "ኢትዮጵያ ለቀይ ባሕር ስትል ኤርትራን የመውጋት ፍላጎት የላትም" ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት የሕልውና ጉዳይ ነው ሲሉ ከተናገሩ በኋላ በሁለቱ አገራት መካከል ውጥረት ሰፍኖ ቆይቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ኢትዮጵያ "ያላት ፍላጎት እንነጋገር ነው" ያሉ ሲሆን፣ "በሰጥቶ መቀበል መርህ፣ ሕዝቦች በሚጠቀሙበት መርህ፣ በገበያ መርህ እንወያይ. . . ውጊያ አያስፈልግም" ብለው ነበር።
በዚህ ወቅት የኤርትራ ሕዝብ የሚያስፈልገው ልማት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ተባብረን መልማት እና መስራት እንጂ አንዱ አንዱን መውጋት የእኛ ፍላጎት አይደለም" ብለው ነበር።
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በትናንትናው ቃለ ምልልሳቸው ላይ ራዕያችን መልካም የሁለትዮሽ ትብብርን እና ጠንካራ ትስስር መፍጠር ነበር ብለው፣ ነገር ግን በተግባር የኢትዮጵያ መንግሥት ጦርነትን በቀስቃሽ ንግግር አውጇል ሲሉ ወንጅለዋል።
ለጦርነት አጀንዳቸው የፈረንሳይ፣ የአሜሪካ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ይሁንታ እንዳላቸው ይናገራሉ ይህ ግን ሙሉ በሙሉ እውነት አይደለም ሲሉ አስተባብለዋል።
የጦር መሳሪያ የሚገዛ እና ዕለት ተዕለት በጦር ኃይል የሚያስፈራራ ኤርትራን እንዴት ይወነጅላል? ሲሉም ጠይቀዋል።
ከመንግሥት ተስፋ መቁረጥ የመነጨው ነው ያሉት ይህ "አደገኛ አካሄድ" መቆም አለበት በማለት "በእኛ በኩል መጨነቅ የለብንም" ሲሉ ለሕዝባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
"ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝቦች እና መላው ጎረቤቶቻችን ጉዳዩን በጥንቃቄ ሊመለከቱት ይገባል" ሲሉ አሳስበዋል።
"ሉዓላዊ የባሕር በር" ማግኘት የሚለው ትኩረት መሳቢያ ሌላ ጂኦፖለቲካዊ ገጽታዎች አሉት። ከዚህ ግድየለሽ ጀብደኝነት ጀርባ ሌሎች ኃይሎች እንዳሉ ግልጽ ነው ብለዋል ፕሬዚደንት ኢሳያስ።
አክለውም በ1940ዎቹ ከቅኝ ግዛት ነጻ የመውጣት መብታችን የተነፈግነው በተመሳሳይ ሰበብ እንደነበር ማስታወስ አለብን።
የብልጽግና ፓርቲ የጂቡቲ ወደብን በመተው ወደ 4 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ምርቶችን ወደ አሰብ ለማዞር በአንድ ወቅት አሳብ አንስቶ ነበር ያሉት ፕሬዚደንት ኢሳያስ፣ ጎረቤት አገርን ለመጉዳት እንዲህ ዓይነት ዕቅድ እንደሌለን ነገርናቸው ብለዋል።
በሶማሌላንድ በኩልም ወደብ እና የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር ለማግኘት ያደረጉት ከፋፋይ እና ጠብ ጫሪ ጥረትም ተመሳሳይ የግድየለሽነት ድርጊት ነው ሲሉ ወንጅለዋል።
እንደ እውነቱ ከሆነ እነዚህ የብልጽግና አጀንዳዎች አይደሉም፣ ነገር ግን የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት በመላው ቀጣናው በቁጥጥሩ ስር ያሉ ወደቦችን የመፍጠር ቅዠት ነው ብለዋል።
'ዘ ሴንትሪ' የተባለው የአሜሪካ የመብቶች ተከታታይ መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት ባወጣው ሪፖርት ኤርትራ ተጥሎባት የነበረው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ከሰባት ዓመት በፊት ከተነሳ በኋላ ሠራዊቷን መልሳ በመገንባት እና በማጠናከር "በጎረቤቶቿ በተለይም በኢትዮጵያ ውስጥ አለመረጋጋት እየፈጠረች ነው" ማለቱ ይታወሳል።
ለጦርነት ምንም ፍላጎት የለንም የሚሉት የኤርትራው ፕሬዚደንት ደግሞ፣ የተጫኑብንን ጦርነቶችን ግን ተፋልመናል ብለዋል።
"በጎረቤቶቻችን ላይ ምንም ዓይነት የግዛት ይገባኛል ጥያቄም ሆነ ምኞት የለንም። ነገር ግን ታሪክ እንደሚመሰክረው ጥቃት ሲደርስ እና ስንጠቃ እንዴት አገራችንን እንደምንጠብቅ እናውቃለን።"
"ብልጽግና ስለገዛቸው ድሮኖች እና የረጅም ርቀት ሚሳዔሎች፣ታንኮች ወዘተ እና በኤርትራ ላይ ስለሚያደርሰው ግዙፍ የጥቃት ማዕበል እየፎከረ ነው" ያሉት የኤርትራው ፕሬዝዳንት "ይህ የሚገርም እና ታሪክን በማያውቁ ሰዎች ዘንድ ብቻ ሊወራ ይችላል" ብለዋል።
"ምክራችን የኢትዮጵያን ሕዝብ ወደ ከንቱ ጦርነት ውስጥ አታስገቡ የሚል ነው" ያሉት ፕሬዝዳንቱ እውነተኛ ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት ይስጡ ሲሉ ተናግረዋል።
ጨምረውም "ዛቻውን ሙሉ በሙሉ ችላ እንላለን ማለት አይደለም" ካሉ በኋላም "አንድ ሰው የሞኝነት ድርጊቶችን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ስለማይችል አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ አለብን።"
በዚሁ ቃለ ምልልስ ላይ የኤርትራ እና የአሜሪካን የሁለትዮሽ ግንኙነትን በተመለከተ የተናገሩት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፣ ኤርትራ ላለፉት ሀምሳ ዓመታት በዋሽንግተን ሲደርስባት የነበረውን በደሎች ሁሉ ነፃነቷን ካገኘች በኋላ ወዲያውኑ "ለመርሳት እና ይቅር ለማለት" መወሰኗን ተናግረዋል።
ምንም እንኳ አሜሪካ በኤርትራ ላይ ያላት ፖለሲ ባይስተካከልም በፕሬዚዳንት ትራምፕ የመጀመርያው የስልጣን ዘመን ግን ዳግም ግንኙነታቸውን ለማደስ መወሰናቸውን አስታውሰዋል።
ይህ ግን በባይደን አስተዳደር እንቅፋት እንደገጠመው በመግለጽ አሁን ዳግም ከትራምፕ አስተዳደር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማደስ ማሰባቸውን ተናግረዋል።
የትራምፕ አስተዳደር በቅርቡ የጉዞ እገዳ ከጣለባቸው የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ኤርትራ ናት።















