'የተራዘመ ጦርነት የተጨናገፈባቸው ጠላቶች' ግጭት ለመቀሰቀስ እየሞከሩ ነው - ብልጽግና

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(መሀል)፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ (በስተግራ) እንዲሁም የብልጽግና ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አህመድ ፋራህ (በስተቀኝ) የፓርቲውን ምክር ቤት ስብሰባን ሲመሩ

የፎቶው ባለመብት, EBC

የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት "የተራዘመ ጦርነት የተጨናገፈባቸው ጠላቶች" ሲል የገለጻቸው ኃይሎች የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭትን ለመቀስቀስ እየሞከሩ ነው ሲል ከሰሰ።

ምክር ቤቱ "ጠላቶች" ሲል የገለፃቸውን በስም ባይጠቅስም፣ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ "ጽንፈኞችን" በመጠቀም የሕዝብን እና የመንግሥትን አንድነት ለመከፋፈል ጥረት እያደረጉ ነው ብሏል።

የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት ከሐምሌ 30 እስከ ነሐሴ 2/2017 ዓ.ም. ድረስ ሲያካሄድ የነበረውን መደበኛ ስብሰባ ሲያጠናቅቅ ባወጣው መግለጫ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መወያየቱን አስታውቋል።

ምክር ቤቱ የሰሜን ኢትዮጵያ ደም አፋሳሽ ጦርነት "በአሸናፊነት" መወጣቱን እና የተገኘውን "ወታደራዊ ድል" በደቡብ አፍሪካ በተፈረመው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መቋጨቱን አስታውሷል።

በስሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን ተሰልፎ የተዋጋው የኤርትራ መንግሥት ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ የሁለቱ መንግሥታት ወዳጅነት ተቀዛቅዞ በአሁኑ ወቅት ለጦርነት በመዘጋጀት እየተካሰሱ ነው።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ በቅርቡ ለአገራቸው ብሔራዊ የቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ኢትዮጵያ ዕለት ተዕለት በጦር ኃይል እያስፈራራች እንዲሁም የጦር መሳሪያ እየገዛች ነው በማለት መክሰሳቸው ይታወቃል።

በትግራይ የተካሄደው ጦርነት ካበቃ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የባሕር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ የኅልውና ጉዳይ ነው በማለት ከተናገሩ እና ይህንንም በተመለከተ የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስዱ ኤርትራ ከሌሎች የኢትዮጵያ ባለንጣዎች ጋር የጋራ ትብብር ፈጥራለች።

ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ዋነኛ ክልሎች ውስጥ በአማራ እና በኦሮሚያ ውስጥ ታጣቂዎች ከመንግሥት ኃይሎች ጋር እየተዋጉ ሲሆን፣ በትግራይ ውስጥም ሕገ ወጥ የተባለው የህወሓት አንደኛው ወገን ከፌደራሉ መንግሥት ጋር እየተወዛገበ ይገኛል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ከህወሓት የተለዩት የቡድኑ የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮች ህወሓት ከኤርትራ መንግሥት ጋር ግንባር መፍጠሩን በመጥቀስ ሲከስሱት ቆይተዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት በመግለጫው በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን በመደገፍ "ታሪካዊ ጠላቶች" ያላቸው አካላት "በመሪነት እና በአስተባባሪነት" ወንጅሏል።

እነዚህ በብልጽግና ፓርቲ "በታሪካዊ ጠላትነት" እንዲሁም በ"ጠላትነት" የተፈረጁ ኃይሎች "ባንዳ ጽንፈኞችን" በመጠቀም ጦርነት ለማካሄድ እንደሚፈልጉ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

"ኢትዮጵያን በሁከት ውስጥ ማቆየት" ይፈልጋሉ ያላቸው እነዚህ ኃይሎች፣ ሌሎች የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም የሕዝብ አንድነትን እና የመንግሥትን ኃይልን ለመከፋፈል ይሠራሉ ብሏቸዋል።

ምክር ቤቱ በመግለጫው ባለፉት ሁለት ዓመታት እነዚህ አካላት የሕዝብን እና የመንግሥትን አንድነት ለመፈታተን በየአካባቢው ግጭትን ማበራከት እና በዲጂታል ሚዲያ መንግሥትን ማሳጣትን እንደ ስልት ተጠቅመው እንደነበር ጠቅሷል።

የፓርቲው ምክር ቤት ያደረገውን የሦስት ቀን ስብሰባ ሲያጠናቅቅ ባወጣው መግለጫ በአገሪቱ ግጭትን ሊያስቀሩ የሚችሉ ሰላማዊ አማራጮችን ለመሞከር መወሰኑን አስታውቋል።

ከዚህ በፊት ከነበሩ "ታሪኮች" እንዲሁም "ከዓለም ነባራዊ እውነታ" መማሩን የገለፀው ፓርቲው፤ "ሰላማዊ የፖለቲካ ዕድሎችን አሟጥጦ" የመጠቀም ስልትን መምረጡን በመግለጫው ላይ አስፍሯል።

ምክር ቤቱ እነዚህን ኃይሎች ለመታገል በሚል ካስቀመጣቸው ዝርዝሮች ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ለሚወስኑ ታጣቂዎች አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ መወሰኑን ገልጿል።

ፓርቲው የሰላምን አማራጭ በማይቀበሉ እና በሕዝብ እንዲሁም በአገር ንብረት ላይ ችግር የሚፈጥሩ ኃይሎች ላይ "በተጠናከረ መንገድ ሕግ ለማስከበር" መወሰኑን በዚሁ መግለጫው ላይ አስታውቋል።

በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት ላለፉት ሁለት ዓመታት የቀጠለ ሲሆን፣ በኦሮሚያ ደግሞ ላለፉት ስድስት ዓመታት መንግሥት ሸኔ እያለ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከመንግሥት ኃይሎች ጋር እየተዋጋ ይገኛል።

የመንግሥት ኃይሎች በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች ጋር በሚያደርጉት ግጭት በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ ከመሆኑ በተጨማሪ የሕዝብ መደበኛ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስተጓጎለ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ከወራት በፊት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከፍተኛ አዛዥ ከሌሎች አባላት ጋር ለመንግሥት እጅ ከሰጠ በኋላ በኦሮሚያ ክልል ሥልጣን እንደተሰጣቸው ይታወሳል።

ምክር ቤቱ "በየደረጃው የሚነሡ የሕዝብ የመልካም አስተዳደር፣ የፍትሕ እና የኢኮኖሚ ጥያቄዎችን" ለመመለስ እንደሚሠራም በመግለጫው ላይ አስታውቋል።

"ሕዝባዊ እና ብሔራዊ ለሆነው ዓላማችን ውስጣዊ እንቅፋት የሆነው ሠርጎ ገብነትን እናጠራለን" ያለው የብልጽግና ፓርቲ፤ ምክር ቤት "ብሔርተኝነትን እንገራለን፤ ሌብነትን እና ሕዝበኝነትን ለማጥፋት እንታገላለን" ሲልም አክሏል።

ከዚህም በተጨማሪ መጪው ሰባተኛ አገራዊ ምርጫ"ዴሞክራሲያዊ፣ ሕጋዊ እና የሕዝቡ ምልዐተ ተሳትፎ የሚንጸባረቅበት እንዲሆን" በንቃት እንደሚሳተፍ አስታውቋል።