ኢሰመኮ በዚህ ዓመት የድሮን ጥቃቶች መፈፀማቸውን 'አጠራጣሪ ነው' አለ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲያቀርቡ
የምስሉ መግለጫ, የኢሰመኮ ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ

የ2017 ዓመት ዓመታዊ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሪፖርቱን ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የድሮን ጥቃቶች መፈፀማቸውን 'ግራ የሚያጋባ' ነው ብሏል።

152 ገፆች ያሉት እና ከሰኔ 2016 እስከ ሰኔ 2017 ዓ.ም. ያለውን የአገሪቱን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ የሚገልፀው ሪፖርቱ "የአየር/የድሮን ጥቃት" የሚል አገላለፅ አልተጠቀመም።

በሪፖርቱ "ወታደራዊ ዒላማውን ያልጠበቀ መሣሪያ" በማለት በደፈናው ተገልጿል።

ጥር 2017 ዓ.ም. የተሾሙት እና የመጀመሪያ ዓመታዊ ሪፖርታቸውን ያወጡት ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ሰኞ ሐምሌ 28/2017 ዓ.ም. በአገሪቱ ስለሚፈፀሙ የድሮን ጥቃቶች ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

ኮሚሽነሩ በ2017 ዓ.ም. ሁለት የድሮን ጥቃቶች ብቻ ለኮሚሽኑ መቅረባቸውን እና አጠራጣሪ ሆነው መገኘታቸውን ተናግረዋል።

"በሪፖርታችን ያገኘናቸው የተወሰኑ [የድሮን ጥቃት] ክሶች አሉ። የከባድ መሳሪያ ጥቃቶች ናቸው። ግራ የሚያጋቡ ነገሮች አሉ። 'በሰማይ እየጮኸ ይመጣል፤ አንዱ ቀድሞ ይመጣል፤ አንዱ ይከተላል' በሚል የሚነግሩ አሉ" ሲሉ ስለ አጠራጣሪነቱ ገልፀዋል።

ቢቢሲ በተለይም ግጭት በቀጠለበት አማራ ክልል ስለተፈፀሙ የድሮን ጥቃቶች በርካታ ዘገባዎችን የሠራ ሲሆን፤ የዓይን እማኞች "አሞራ መሳይ" የቅኝት እና ጥቃት አድራሽ ሁለት በራሪዎች ጥቃት ስለመፈጸማቸው ተናግረዋል።

"ከመከላከያ ጋር ባደረግነው ውይይት ይሄ ክስ አለ ብለን አንስተንላቸዋል። የእኛ ምርመራ ሳይሆን የሚዲያ ክስ ነው። ሁለት የመጡ ኬዞች አሉ። ወደ ጥርጣሬ የሚወስዱ ስለሆነ የከባድ መሳሪያ ጥቃት አድርገን ወስደናቸዋል። ተፅዕኖውንም አይተናል" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአካባቢ ባለሥልጣናትም ስለ ተፈጸሙ ጥቃቶች ሲጠየቁ ንፁሃን ሰዎች አለመገደላቸውን እንጂ ስለ መሳሪያው ዓይነት ማስተባባያ ሲሰጡ አይደመጡም።

". . .መከላከያ አሁንም እያለን ያለው የቁጥጥር ማዕከል (ስችዌሽን ሩም) እናሳያችኋለን [ነው]። ትክክለኛ ዒላማ የመምታት እንዴት ነው? እንዴት ነው የሚተኩሱት? ቴክኖሎጂውን እኛ አናውቅም። እና እነዚህን በመረጃ ላይ ተደግፈን ክስተቶች ካሉ [ሪፖርት] የማናወጣበት ምንም ምክንያት የለም" ሲሉ ኮሚሽነሩ ምላሽ ሰጥተዋል።

ዓለም አቀፍ የትጥቅ ግጭቶችን የሚከታተለው አክሌድ የተባለው ገለልተኛ ተቋም ከሰኔ 2016 እስከ ሰኔ 2017 ዓ.ም. ድረስ ከጂቡቲ ተነስተው አፋር ክልል ውስጥ ተፈፀሙ የተባሉ ሁለት የድሮን ጥቃቶችን ጨምሮ 53 የድሮን ጥቃቶችን መዝግቧል።

ከእነዚህም ውስጥ 82 በመቶው በአማራ ክልል እና 15 በመቶው በኦሮሚያ ክልል የተፈፀሙ መሆናቸውን አመለክቷል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ለሰብዓዊ መብቶች መስፋፋት፣ መከበር እና ጥበቃ የሚሠራ ተጠሪነቱም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነ ተቋም ነው።

ባለፈው ዓመት ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርቱ በትጥቅ ግጭት ወቅት "የመለየትን፣ የጥብቅ አስፈላጊነትን እና የተመጣጣኝነት መርሖችን" ባልጠበቁ የአየር ድብደባዎች (በአብዛኛው በሰው አልባ በራሪዎች ወይም ድሮን) ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሲቪል ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል ብሏል።

በዚህ ዓመት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሕይወት የመኖር መብት "አሳሳቢ" ሆኖ መቀጠሉን የገለፀው የኢሰመኮ ሪፖርት፤ ኮሚሽኑ በሚያቀርባቸው ምክረ ሐሳቦች እና ውትወታዎች ውጤት እያመጣ መሆኑን ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ አስረጂ እያነሱ አቅርበዋል።

ኮሚሽነሩ ላለፉት አስርት ዓመታት የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ላይ የተለመደው ስም ጠርቶ በይፋ ሪፖርት እና መግለጫ መውጣት (በእሳቸው አጠራር Naming and Shaming) ይልቅ የራሳቸውን አካሄድ እየተከተሉ መሆኑን ጠቁመዋል።

"እኛ ቦሌ መንገድ ቁጭ ብለን የምንጮህ ከሆነ ሌላው ተጠያቂነትን የማያረጋግጥ ከሆነ እና ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ ውጤት አናመጣም" ያሉት ኮሚሽነሩ፤ 'ድንበራቸውን' አስጠብቀው ከመንግሥት ጋር ተቀራርበው (Constructive Engagement) እየሠሩ እና አዎንታዊ ለውጦችን እያዩ መሆኑን ገልፀዋል።

ከወራት በፊት ከብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያው ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኮሚሽኑ የተዛባ ሪፖርት ሲያወጣ ነበር በሚል ወቀሳ ሰንዝረውበታል።

ኢሰመኮ "የፈረንጅ ጉዳይ አስፈፃሚ ነው" የሚል ሀሳብ ከመንግሥት ሹማምት እንደሚቀርብባቸው የተናገሩት ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ይህንም "በበጎነት" እንደሚወስዱት ስለ ጣልቃ ገብነት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምልሽ ሲሰጡ ተናግረዋል።

"እነዚህ አስተሳሰቦች ሲገለፁ በመረጃ ላይ ተንተርሰን እንሞግታለን። ደግሞ ቆም ብለን ለዚህ አይደል የምንታገለው [እንላለን]? እነዚህ በነፃነት የሚገለፁ ሀሳቦች ገንቢ ናቸው ብለን ነው የምንወስደው" ብለዋል።

ከሰኔ 2016 እስከ ሰኔ 2017 ዓ.ም. የሸፈነው የኢሰመኮ ሪፖርት በአገሪቱ የቀጠሉት የትጥቅ ግጭቶች እና የፀጥታ ችግሮች ለአገሪቱ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር ቀዳሚውን ስፍራ መያዙን አስምሯል።

ሆኖም ኢሰመኮ በፀጥታ እና በሌሎች ችግሮች ምክንያት እንደ አስፈላጊነቱ ተንቀሳቅሶ ሥራውን መከወን አለመቻሉን ጠቅሶ፤ በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች ያለውን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ መመርመር እና መከታተል እንዳልቻለ አመልክቷል።