በኦሮሚያ ክልል በቀጠለው ግጭት ሰላማዊ ዜጎች 'ከባድ' ቀውስ ውስጥ ናቸው - የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በኦሮሚያ ክልል የቀጠለው ግጭት በሰላማዊ ሰዎች ላይ "አስከፊ ቀውስ" እያደረሰ መሆኑን አስታወቀ።
ኮሚቴው ሐሙስ ሐምሌ 24 /2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኃይሎች እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እያደረጉት ያለው ውጊያ የሰላማዊ ሰዎች ሕይወት ላይ ከባድ ጫና እያስከተለ መሆኑን ገልጿል።
መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ላለፉት ስድስት ዓመታት በክልሉ ውስጥ ከመንግሥት ወታደሮች ጋር እየተዋጋ ይገኛል።
በምዕራብ እና ደቡብ የኦሮሚያ አካባቢዎች በስፋት የሚንቀሳቀሰው ይህ ታጣቂ ቡድን በተለያዩ ጊዜያት በሰላማዊ ሰዎች እና በአካባቢ ባለሥልጣናት ላይ ከሚፈጸሙ ግድያዎች ጋር ስሙ በተደጋጋሚ ይነሳል።
ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የተነጠለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ፈጽሟቸዋል በተባሉ ጥቃቶች ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀ ቡድን ነው።
በኦሮሚያ ክልል በቀጠለው ግጭት የተነሳ ነዋሪዎች እንደ ጤና እና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት መንቀሳቀስ አደገኛ ሆኖባቸዋል ሲል የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በመግለጫው ላይ ገልጿል።
"በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ያለው ግጭት በብዙ ማኅበረሰቦች ላይ በተለይም ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው" ብሏል።
". . . ሰላማዊ ዜጎች በክልሉ በቀጠለው ግጭት ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው ነው። ብዙ ሰዎች ተገድለዋል ወይም ቆስለዋል እንዲሁም አነስተኛ እርዳታ ወደ ክልሉ እየገባ ነው" ሲል አስታውቋል።
ኮሚቴው ምንም እንኳን የሰላማዊ ሰዎች ኑሮ እየተጎዳ ቢሆንም፣ በርካታ ሰዎች እየሞቱ እና እየቆሰሉ ቢሆንም በክልሉ የሚካሄደው ግጭት ትኩረት አላገኘም ማለቱን የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ ዘግቧል።
"ብዙ ማኅበረሰቦች ከውጊያ ቀጠናዎች፣ በሁለቱም በኩል ወይም ተለዋዋጭ በሆኑት የውጊያ ሜዳዎች አቅራቢያ እና ዙሪያ ይኖራሉ። ይህ ማለት ተደጋጋሚ ግጭቶች እንቅስቃሴዎችን ከባድ እና አደገኛ ያደርጉባቸዋል" ሲል በግጭት ቀጠና የሚገኙ ነዋሪዎች የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት መቸገራቸውን በመግለጫው ላይ ገልጿል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2018 የዓለም አቀፍ ታዛቢዎች የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን በጥቂት ሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች እንዳሉት ተናግረው የነበረ ቢሆንም፤ በቅርብ ዓመታት ውስጥ የታጣቂዎቹ ቁጥሩ በከፍተኛ ሁኔታ እንደጨመረ ያምናሉ።
ይህም ሆኖ ግን ቡድኑ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ከፍተኛ ስጋት ለመፍጠር በበቂ ሁኔታ የታጠቀ እና የተደራጀ አይደለም ይላሉ።
በኅዳር ወር የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ፈጽሞታል በተባለ ጥቃት የዞን አስተዳዳሪን ጨምሮ የ48 ሰዎች ሕይወት ማለፉን አስታውቆ ነበር።
በቅርቡ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከ200 በላይ የኢትዮጵያ መከላከያ አባላትን ገድያለሁ ማለቱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንዲሁ በርካታ የታጣቂ ቡድኑ አባላትን መግደሉን ወይም በቁጥጥር ስር ማዋሉን በተለያዩ ጊዜ ተናግሯል።
በሁለቱም ወገኖች የሚወጡትን መረጃ ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ ከባድ ነው።
ከወራት በፊት ከፍተኛ የቡድኑ አዛዥ ከሌሎች አባላት ጋር ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በመውጣት ለመግሥት እጅ ከሰጠ በኋላ በኦሮሚያ ክልል ሥልጣን እንደተሰጣቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በኦሮሚያ ክልል ከሚያካሄደው ውጊያ በተጨማሪ በአማራ ክልልም ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ላለፉት ሁለት ዓመታት ውጊያ እያካሄደ ይገኛል።
እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራውና መንግሥት ሸኔ የሚለው ታጣቂ ቡድን ከጥቂት ዓመታት በፊት ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ተለይቶ የወጣ ታጣቂ ቡድን ነው።
ባለፉት ስድስት ዓመታት በተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎች ውስጥ የሚንቀሳቀሰው፣ መንግሥት በሽብር ቡድንነት የፈረጀው እና 'ሸኔ' የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከክልሉ እና ከፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት ጋር ግጭት ውስጥ ቆይቷል።
በዚህም ሳቢያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው በተለያዩ ጊዜያት የተዘገበ ሲሆን፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ከማጣታቸው ባሻገር ለመፈናቀል መዳረጋቸው ይታወቃል።















