ባለፉት ሁለት ዓመታት በኦሮሚያ 94 ሰዎች በመንግሥት ኃይሎች እና በታጣቂዎች መገደላቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ

ጠመንጃ የያዙ ታጠቂዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት 94 ሰዎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና በታጣቂዎች ከሕግ ውጭ መገደላቸውን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ባለፉት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመንግሥት እና በታጣቂ ላይሎች መካከል እየተካሄደ ባለው ግጭት እና በሚፈጸሙ ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎች ሰለባ መሆናቸውን አመልክቷል።

በዚህም ሁለቱም ወገኖች ነዋሪዎችን ሌላኛውን ወገን በመደገፍ እና አባል በመሆን እንደሚከሱ እና በዚህም ሳቢያ ያለ ሕግ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም ግድያዎችን መፈጸማቸውን በአሃዝ አስደግፎ ይፋ አድርጓል።

ኮሚሽኑ ይህን የገለጸው በክልሉ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና በታጣቂዎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ዛሬ አርብ የካቲት 15/2016 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ሪፖርት ነው።

ኮሚሽኑ ከመስከረም 1/2014 እስከ ጥቅምት 30/2016 ዓ.ም. ባሉት ሁለት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል ዘጠኝ ዞኖች የተጎጂ ቤተሰቦችን ጨምሮ 158 ሰዎችን በማነጋጋር ያሰባሰበውን ግኝት ነው ይፋ ያደረገው።

በኮሚሽኑ ሪፖርት በተጠቀሱት ሁለት ዓመታት በመንግስት የፀጥታ አካላት እና በታጣቂዎች ከሕግ ውጭ የተፈጸሙ ግድያዎችን በዝርዝር አስፍሯል።

በሪፖርቱ መሠረት ባለፉት ሁለት ዓመታት 52 ግለሰቦች በመከላከያ ሠራዊት እና በቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ከሕግ ውጭ ተገድለዋል።

የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ግድያዎቹን የፈጸሙት “ለታጣቂ ቡድኖች መረጃ እና ሎጀስቲክስ ታቀርባላችሁ፣ የቡድኑ አባል ናችሁ” በሚል ምክንያት መሆኑን በኢሰመኮ ሪፖርት ላይ ሰፍሯል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከዚህ በተጨማሪም በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ” የሚባለው የኦሮሞ ነጻነት ጦር “ለመንግሥት መረጃ ትሰጣላችሁ፣ የቤተሰብ አባላችሁ በመንግሥት የፀጥታ ኃይል ውስጥ እያገለገለ ነው ወይም ለእኛ ድጋፍ አላደረጋችሁም” በሚል ምክንያት ሲቪል ሰዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ኢሰመኮ አስታውቋል።

በተመሳሳይ ኢ-መደበኛ የአማራ ታጣቂዎች “ከአማራ ክልል ጋር በሚዋሰኑ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ነዋሪዎችን ‘በኦነግ ሸኔነት በመፈረጅ’” ሲቪል ሰዎች ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት እንደሚፈጸም ኮሚሽኑ አክሏል።

በኢሰመኮ ሪፖርት መሰረት “ኢ-መደበኛ የአማራ ታጣቂዎች” ባለፉት ሁለት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል 29 ሰዎችን ገድለዋል። በተጨማሪም መንግሥት ኦነግ ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነጻነተ ሠራዊት ደግሞ 13 ሰዎች ላይ ግድያ መፈጸሙን ከሪፖርቱ መረዳት ተችሏል።

ከግድያ እና ከአካል ጉዳት በተጨማሪ እገታ እና አስገድዶ መሰወር በክልሉ ነዋሪዎች ላይ መድረሱን መንግሥታዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም አስታውቋል። ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈነቀላቸውንም ኮሚሽኑ አክሏል።

ኮሚሽኑ በሪፖርቱ በግጭት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት፤ “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም በማድረግ ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ በቁርጠኝነት እንዲሰሩ” ጠይቋል።

በታጣቂው ቡድን እና በመንግሥት መካከል በታንዛኒያ ውስጥ በሁለት ዙር የሰላም ንግግር የተደረገ ቢሆንም፤ ሰላም የሚያወርድ ስምምነት ላይ ባለመደረሱ አሁንም ግጭቶች እየተካሄዱ መሆናቸው ይዘገባል።

ኢሰመኮ የፌደራል መንግሥቱ የሰብዓዊ መብቶች እና የሰብዓዊነት ሕጎች ጥሰት የፈጸሙ እና ያስፈጸሙ ኃላፊዎች ላይ የወንጀል ምርመራ እና የክስ ሂደት እንዲጀመር ጥሪ አቅርቧል።

በተጨማሪ “በግጭቱ በሰው ሕይወት፣ በአካል፣ በሥነ ልቦና እና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት በማጣራት ተጎጂዎች እንዲካሱ” ኮሚሽኑ ጠይቋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት በተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎች ውስጥ የሚንቀሳቀሰው፣ መንግሥት በሽብር ቡድንነት የፈረጀው እና ‘ሸኔ’ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ከክልሉ እና ከፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት ጋር ግጭቶች ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በዚህም ሳቢያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው በተለያዩ ጊዜያት የተዘገበ ሲሆን፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ከማጣታቸው ባሻገር ለመፈናቀል መዳረጋቸው ይታወቃል።